Get Mystery Box with random crypto!

ከእኔ በፊት በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ እጅግ በጣም አዛኝ በሆነው፡፡ 17፥55 ከፊሉንም | ወሒድ የንጽጽር ማኅደር

ከእኔ በፊት

በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ እጅግ በጣም አዛኝ በሆነው፡፡

17፥55 ከፊሉንም ነቢያት በከፊሉ ላይ በእርግጥ አበለጥን፡፡ وَلَقَدْ فَضَّلْنَا بَعْضَ النَّبِيِّينَ عَلَىٰ بَعْضٍ

"ፈድል" فَضْل የሚለው ቃል "ፈዶለ" فَضَّلَ ማለትም" ሰጠ" "ቸረ" ከሚል ሥርወ ቃል የመጣ ሲሆን "ስጦታ" "ችሮታ" "ጸጋ"Bounty” ማለት ነው፥ አምላካችን አሏህ በሚያወርደው ፈድል ነቢያትን ከፊላቸውን በከፊሉ ላይ አብልጧል፦
17፥55 ከፊሉንም ነቢያት በከፊሉ ላይ በእርግጥ አበለጥን፡፡ وَلَقَدْ فَضَّلْنَا بَعْضَ النَّبِيِّينَ عَلَىٰ بَعْضٍ

እነዚህ አናቅጽ ላይ "አበለጥን" ለሚለው የገባ ቃል "ፈዶልና" فَضَّلْنَا መሆኑን ልብ ብለካልን? በተመሳሳይ በባይብል ነቢዩ ዮሐንስ እና ነቢዩ ኢየሱስ ሁለቱም ነቢይ ናቸው፦
ሉቃስ 1፥76 ደግሞም አንተ ሕፃን ሆይ፥ የልዑል "ነቢይ" ትባላለህ፥ መንገዱን ልትጠርግ በጌታ ፊት ትሄዳለህና።
ማቴዎስ 21፥11 ሕዝቡም፦ "ይህ ከገሊላ ናዝሬት የመጣ "ነቢዩ" ኢየሱስ ነው" አሉ።

ነገር ግን ነቢዩ ዮሐንስ ከነቢዩ ኢየሱስ በደረጃ የሚያንስ እና ነቢዩ ኢየሱስ ከነቢዩ ዮሐንስ በደረጃ እንደሚልቅ ነቢዩ ዮሐንስ ተናግሯል፦
ዮሐንስ 1፥30 አንድ "ሰው" ከእኔ በኋላ ይመጣል፥ "ከእኔም በፊት ነበርና" ከእኔ ይልቅ የከበረ ሆኖአል። οὗτός ἐστιν ὑπὲρ οὗ ἐγὼ εἶπον Ὀπίσω μου ἔρχεται ἀνὴρ ὃς ἔμπροσθέν μου γέγονεν, ὅτι πρῶτός μου ἦν.

"አነር" ἀνὴρ ማለት "ወንድ ሰው" ማለት ሲሆን የፆታ መደቡ ወንድ ነው፥ ይህ ወንድ የተራክቦ ማድረጊያ በስምንተኛው ቀን የተገረዘ ሰው ነው። ይህ ሰው ማኅፀን ውስጥ ተፈጥሮ እና የተለያየ እድገት አርጎ የመጣ ሲሆን ከዮሐንስ በደረጃ የከበረ ነው፥ በክብር ስለሚበልጥ "ከእኔም በፊት ነበር" በማለት ዮሐንስ ስለ ኢየሱስ ተናግሯል። ቅሉ ግን ዮሐንስ "አንድ ሰው" ያለው ሰው ኢየሱስ ከዮሐንስ በፊት በሰውነት አልነበረም፥ ነገር ግን በክብር መላቅን አመላካች ነው። ለምሳሌ፦ ምናሴ የኤፍሬፍ ታላቅ ወንድም ነው፥ በዕድሜ ምናሴ የዮሴፍ የበኵር ልጅ ሆኖ ኤፍሬምን ይቀድመዋል፦
ዘፍጥረት 41፥51-52 ዮሴፍም የበኵር ልጁን ስም ምናሴ ብሎ ጠራው፥ እንዲህ ሲል፦ "አምላክ መከራዬን ሁሉ የአባቴንም ቤት አስረሳኝ፤ የሁለተኛውንም ስም ኤፍሬም ብሎ ጠራው፥ እንዲህ ሲል፦ "አምላክ በመከራዬ አገር አፈራኝ"።

ነገር ግን ዮሴፍ ኤፍሬምንም ከምናሴ "በፊት" አደረገው፥ ያ ማለት ኤፍሬም ከምናሴ በፊት በአካል ደረጃ ነበረ ማለት ሳይሆን በክብር እና በደረጃ ከምናሴ ይበልጣል ማለት ነው፦
ዘፍጥረት 48፥20 ኤፍሬምንም ከምናሴ "በፊት" አደረገው።
ሰፕቱአጀንት፦ καὶ ἔθηκε τὸν ᾿Εφραΐμ ἔμπροσθεν τοῦ Μανασσῆ.
ማሶሬት፦ וַיָּ֥שֶׂם אֶת־אֶפְרַ֖יִם לִפְנֵ֥י מְנַשֶּֽׁה׃

"ሊፕነ" לִפְנֵ֥י ማለት "በፊት" ማለት ነው። ኤፍሬም ምናሴን በደረጃ እና በክብር ስለበለጠው ምናሴ ከኤፍሬም "በፊት" እንደሆነ ከተነገረ በተመሳሳይም ነቢዩ ኢየሱስ ከነቢዩ ዮሐንስ በክብር ስለበለጠ "ከእኔ በፊት" በማለት ተናግሯል፥ ጉዳዩ የክብር እንጂ የዕድሜ ስላልሆነ እዛው ዐውድ ላይ "ከእኔ ይልቅ የከበረ ሆኖአል" በማለት ተናግሯል። "እኔ" የሚለው ባለቤት ተውላጠ ስም ማንነትን የሚያሳይ ሲሆን ከኢየሱስ ማንነት መፈጠር በፊት የመጡ ሐሰተኛ ነቢያት መምጣታቸውን ኢየሱስ መናገሩ በራሱ የኢየሱስ ማንነት ከዮሐንስ በኃላ የተፈጠረ መሆኑን ቁልጭ አርጎ ያሳያል፦
ዮሐንስ 10፥8 "ከ-"እኔ በፊት" የመጡ ሁሉ ሌቦች እና ወንበዴዎች ናቸው። πάντες ὅσοι ἦλθον πρὸ ἐμοῦ κλέπται εἰσὶν καὶ λῃσταί·

"ከ-"እኔ በፊት" የሚለው ይሰመርበት! "በፊት" የሚለው መስተዋድድ "እኔ" ከሚለው ህልውና አስቀድሞ በኑባሬ ቀድመው የመጡ ፍጡራን እንዳሉ አመላካች ነው። ኢየሱስ ከድንግል ማርያም ከመፈጠሩ በፊት ቴዎዳስ እና የገሊላው ይሁዳ ሐሰተኛ ነቢያት ሆነው ተነስተው ነበር፦
የሐዋርያት ሥራ 5፥36 ከዚህ ወራት አስቀድሞ ቴዎዳስ፦ "እኔ ታላቅ ነኝ" ብሎ ተነሥቶ ነበርና፥ አራት መቶ የሚያህሉ ሰዎችም ከእርሱ ጋር ተባበሩ፤ እርሱም ጠፋ የሰሙትም ሁሉ ተበተኑ እንደ ምናምንም ሆኑ።
የሐዋርያት ሥራ 5፥37 ከዚህ በኋላ ሰዎች በተጻፉበት ዘመን የገሊላው ይሁዳ ተነሣ ብዙ ሰዎችንም አሸፍቶ አስከተለ፤ እርሱም ጠፋ የሰሙትም ሁሉ ተበታተኑ።

በታሪክ ቴዎዳስ ከኢየሱስ ልደት አርባ አራት ዓመት በፊት "መሢሕ ነኝ" ብሎ ተነስቶ ብዙ ተከታዮችን አፍርቶ ነበር። ከእርሱ በኃላ ሰዎች የተጻፉበት ዘመን ከኢየሱስ ልደት ስድስት ዓመት ቀደም ብሎ የተካሄደ ሲሆን በዚያን ጊዜ የገሊላው ይሁዳ "መሢሕ ነኝ" ብሎ የተነሳው ኢየሱስ ከመፈጠሩ በፊት ነው።
ኢየሱስ "ከ-እኔ በፊት" ሲል "እኔ" የሚለው "እኔነቱን" ወደ ህልውና ከመምጣቱ በፊት ቴዎዳስ እና የገሊላው ይሁዳ በህልውና ይቀድሙት ነበር ማለት ነው። ህልውናው ጅማሮ እና መነሾ ያለው ኢየሱስ ከዮሐንስ በፊት በአካል አልነበረም፥ ከዚያ ይልቅ ዮሐንስ ኢየሱስን በአካል በስድስት ወር ይበልጠዋል።
አሏህ ሂዳያህ ይስጣችሁ! ለእኛም ጽናቱን ይስጠን! አሚን።

ከዐቃቢ ኢሥላም ወሒድ
https://t.me/Wahidcom

ወሠላሙ ዐለይኩም