Get Mystery Box with random crypto!

ኢብሊሥ ከጂን ስለሆነ አሏህን የማመጽ እና የመታዘዝ ነጻ ፈቃድ ስላለው በጌታው ላይ አምጾ ኮራ፥ መ | ወሒድ የንጽጽር ማኅደር

ኢብሊሥ ከጂን ስለሆነ አሏህን የማመጽ እና የመታዘዝ ነጻ ፈቃድ ስላለው በጌታው ላይ አምጾ ኮራ፥ መላእክት ግን የማመጽ እና የመታዘዝ ነጻ ፈቃድ ስለሌላቸው በባሕያቸው ውስጥ ኩራትና አመጽ የለም። አሏህ ያዘዛቸውን ነገር በመጣስ አያምጹም፥ የሚታዘዙትንም ሁሉ ይሠራሉ፦
38፥74 ኢብሊሥ ብቻ ሲቀር፡፡ "ኮራ"፤ ከከሓዲዎቹም ሆነ፡፡ إِلَّا إِبْلِيسَ اسْتَكْبَرَ وَكَانَ مِنَ الْكَافِرِينَ
16፥49 "እነርሱም አይኮሩም" وَهُمْ لَا يَسْتَكْبِرُونَ
21፥19 እርሱ ዘንድ ያሉትም መላእክት እርሱን ከመገዛት አይኮሩም፡፡ አይሰለቹምም፡፡ وَمَنْ عِندَهُ لَا يَسْتَكْبِرُونَ عَنْ عِبَادَتِهِ وَلَا يَسْتَحْسِرُونَ
66፥6 አላህ ያዘዛቸውን ነገር በመጣስ አያምጹም፤ የሚታዘዙትንም ሁሉ ይሠራሉ፡፡ لَّا يَعْصُونَ اللَّهَ مَا أَمَرَهُمْ وَيَفْعَلُونَ مَا يُؤْمَرُونَ

፨ሲያረብብ መላእክት በአሏህ ላይ አምጸው የሚገቡበት ጀሀነም ሆነ ታዘው የሚገቡበት ጀነት የለም። ጂኒዎች ግን በምርጫቸው አምነው ጀነት ወይም ክደው ጀሀነም መግባት ይችላሉ፦
11፥119 የጌታህም ቃል፦ "ገሀነምን ከጂኒዎ እና ከሰዎች ሁሉ በእርግጥ እሞላታለሁ" በማለት ተፈጸመች። وَتَمَّتْ كَلِمَةُ رَبِّكَ لَأَمْلَأَنَّ جَهَنَّمَ مِنَ الْجِنَّةِ وَالنَّاسِ أَجْمَعِينَ
55፥45 ከጌታችሁም ጸጋዎች በየትኛው ታስተባብላላችሁ? فَبِأَيِّ آلَاءِ رَبِّكُمَا تُكَذِّبَان
55፥46 በጌታውም ፊት መቆምን ለፈራ ሁለት ገነቶች አሉት፡፡ وَلِمَنْ خَافَ مَقَامَ رَبِّهِ جَنَّتَانِ

ሱረቱር ረሕማን ዐውዱ ላይ ያሉት ሰው እና ጃን ናቸው፥ "ጌታችሁ" የሚለው ቃል "ረቢኩማ" رَبِّكُمَا ሲሆን ሁለተኛ መደብ ሙሰና ሰውን እና ጃንን ያመለክታል። “ታስተባብላላችሁ” የሚለው ቃል “ቱከዚባኒ” تُكَذِّبَانِ ሲሆን ሁለተኛ መደብ ሙሰና ሰውን እና ጃንን ያመለክታል፦
55፥14 ሰውን እንደ ሸክላ ከሚቅጨለጨል ደረቅ ጭቃ ፈጠረው፡፡ خَلَقَ الْإِنسَانَ مِن صَلْصَالٍ كَالْفَخَّارِ
55፥15 "ጃንንም ከእሳት ከኾነ ነበልባል ፈጠረው"፡፡ وَخَلَقَ الْجَانَّ مِن مَّارِجٍ مِّن نَّارٍ

የትንሳኤ ቀን ለሁለቱም የተቀጠረ ቀጠሮ ነው፥ የዚያን ቀን የተውበት በር ስለተዘጋ ሰው ሆነ ጂን ከኃጢኣቱ አሏህን ይቅርታ እንዲጠይቅ አይጠየቅም። ከዛ ይልቅ "የዚህንም ቀናችሁን ቅጣት ማግኘትን የሚያስጠነቅቋችሁ ከእናንተው የኾኑ መልእክተኞች አልመጧችሁምን" በመባል ፍርድ ያገኛሉ፦
44፥40 የመለያው ቀን ለሁሉም ቀጠሯቸው ነው፡፡ إِنَّ يَوْمَ الْفَصْلِ مِيقَاتُهُمْ أَجْمَعِينَ
55፥39 በዚያም ቀን ሰው እና ጃን ከኃጢኣቱ ገና አይጠየቅም፡፡ فَيَوْمَئِذٍ لَّا يُسْأَلُ عَن ذَنبِهِ إِنسٌ وَلَا جَانٌّ
6፥130 የጂኒዎች እና የሰዎች ጭፍሮች ሆይ! አንቀጾቼን በእናንተ ላይ የሚተርኩ የዚህንም ቀናችሁን ቅጣት ማግኘትን የሚያስጠነቅቋችሁ ከእናንተው የኾኑ መልእክተኞች አልመጧችሁምን? ይባላሉ፡፡ يَا مَعْشَرَ الْجِنِّ وَالْإِنسِ أَلَمْ يَأْتِكُمْ رُسُلٌ مِّنكُمْ يَقُصُّونَ عَلَيْكُمْ آيَاتِي وَيُنذِرُونَكُمْ لِقَاءَ يَوْمِكُمْ هَـٰذَا

ለጂኒዎች ጀነት እና ጀሃነም እንዲሁ የትንሳኤ ቀን ቀጠሮ እንዳላቸው እና የተፈጠሩበት አላማ ካየን ዘንዳ በነጻ ምርጫቸው አምነው ሙሥሊም አልያም ክደው ኩፋር የመሆን ምርጫ አላቸው፦
72፥14 «እኛም ከእኛ ውስጥ ሙሥሊሞች አሉ፡፡ ከእኛም ውስጥ በዳዮች አሉ፡፡ የሠለሙም ሰዎች እነዚያ ቅንን መንገድ መረጡ፡፡» وَأَنَّا مِنَّا الْمُسْلِمُونَ وَمِنَّا الْقَاسِطُونَ ۖ فَمَنْ أَسْلَمَ فَأُولَـٰئِكَ تَحَرَّوْا رَشَدًا

ስለዚህ "ኢብሊሥ መልአክ ነበር" የሚለው ትርክት ቁርኣን ላይ ሆነ ሐዲስ ላይ የለም። አሏህ ሂዳያህ ይስጣችሁ! ለእኛም ጽናቱን ይስጠን! አሚን።

ከዐቃቢ ኢሥላም ወሒድ
https://t.me/Wahidcom

ወሠላሙ ዐለይኩም