Get Mystery Box with random crypto!

ዛፍ ይናገራልን? በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ እጅግ በጣም አዛኝ በሆነው። 55፥6 ሐረግ እ | ወሒድ የንጽጽር ማኅደር

ዛፍ ይናገራልን?

በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ እጅግ በጣም አዛኝ በሆነው።

55፥6 ሐረግ እና ዛፍ ለእርሱ ይሰግዳሉ፡፡ وَالنَّجْمُ وَالشَّجَرُ يَسْجُدَانِ

ከጂን የኾኑ ጭፈሮች ቁርኣንን አዳምጠው "እኛ አስደናቂ የኾነን ቁርኣን ሰማንም" ማለታቸው ወደ ተወዳጁ ነቢያችን"ﷺ" ተወርዷል፦
72፥1 በል «እነሆ ከጂን የኾኑ ጭፈሮች ቁርኣንን አዳመጡ፡፡‹እኛ አስደናቂ የኾነን ቁርኣን ሰማንም› አሉ ማለት ወደ እኔ ተወረደ፡፡ قُلْ أُوحِيَ إِلَيَّ أَنَّهُ اسْتَمَعَ نَفَرٌ مِّنَ الْجِنِّ فَقَالُوا إِنَّا سَمِعْنَا قُرْآنًا عَجَبًا

"ተወረደ" ለሚለው የገባው የግሥ መደብ "ኡሒየ" أُوحِيَ ሲሆን "ወሕይ" وَحْي ማለት እራሱ "ግልጠተ መለኮት"Divine revelation" ማለት ነው፥ ከጂኒ የኾኑን ጭፍሮች ቁርኣንን የሚያዳምጡ ሆነው ወደ ነቢያችን"ﷺ" ዞረዋል፦
46፥29 ከጂኒ የኾኑን ጭፍሮች ቁርኣንን የሚያዳምጡ ሲኾኑ ወደ አንተ ባዞርን ጊዜም አስታውስ! በተጣዱትም ጊዜ "ዝም ብላችሁ አዳምጡ" ተባባሉ፡፡ በተጨረሰም ጊዜ አስጠንቃቂዎች ኾነው ወደ ሕዝቦቻቸው ተመለሱ፡፡ وَإِذْ صَرَفْنَا إِلَيْكَ نَفَرًا مِّنَ الْجِنِّ يَسْتَمِعُونَ الْقُرْآنَ فَلَمَّا حَضَرُوهُ قَالُوا أَنصِتُوا ۖ فَلَمَّا قُضِيَ وَلَّوْا إِلَىٰ قَوْمِهِم مُّنذِرِينَ

በተጨረሰም ጊዜ አስጠንቃቂዎች ኾነው ወደ ሕዝቦቻቸው ተመለሱ፥ በሌሊት ጂኒዎች ቁርኣንን መስማታቸውን ለነቢዩ"ﷺ" የተናገረው ዛፍ ነው፦
ኢማም ቡኻርይ መጽሐፍ 63 ሐዲስ 85
ዐብዱ ራሕማን እንደተረከው፦ "እኔም መሥሩቅን፦ "በሌሊት ጂኒዎች ቁርኣንን መስማታቸውን ለነቢዩ"ﷺ" ማን ነገራቸው? ብዬ ጠየኩት፥ እርሱም፦ "አባትህ ዐብደሏህ፦ "ለነቢዩ"ﷺ" ስለ እነርሱ የተናገረው ዛፍ ነው" አለኝ። حَدَّثَنِي عُبَيْدُ اللَّهِ بْنُ سَعِيدٍ، حَدَّثَنَا أَبُو أُسَامَةَ، حَدَّثَنَا مِسْعَرٌ، عَنْ مَعْنِ بْنِ عَبْدِ الرَّحْمَنِ، قَالَ سَمِعْتُ أَبِي قَالَ، سَأَلْتُ مَسْرُوقًا مَنْ آذَنَ النَّبِيَّ صلى الله عليه وسلم بِالْجِنِّ لَيْلَةَ اسْتَمَعُوا الْقُرْآنَ‏.‏ فَقَالَ حَدَّثَنِي أَبُوكَ ـ يَعْنِي عَبْدَ اللَّهِ ـ أَنَّهُ آذَنَتْ بِهِمْ شَجَرَةٌ‏.‏

ዛፍ በራሱ የሚናገር እና የሚሰማ ማንነት አይደለም፥ አምላካችን አሏህ ግን ዛፉን ጂኒዎች ቁርኣንን መስማታቸውን ለነቢዩ"ﷺ" እንዲናገር ካረገው በኃላ በቁርኣን ግልጠተ መለኮት ጂኒዎች "እኛ አስደናቂ የኾነን ቁርኣን ሰማንም" ማለታቸውን ወደ ነቢያችን"ﷺ" ወሕይ አድርጎ አወረደ እንጂ እናንተ እንደምትቀጥፉት ዛፉ አሏህ ሆኖ አይደለም። ዛፍ እራሱ ፍጡር ሆኖ ለአሏህ የሚሰግድ ተክል ነው፦
55፥6 ሐረግ እና ዛፍ ለእርሱ ይሰግዳሉ፡፡ وَالنَّجْمُ وَالشَّجَرُ يَسْجُدَانِ

አሏህ ዛፍን እንዲናገር ማድረጉ ከገረማችሁ እና የሐዲሱን አሳብ ማጣመም ከፈለጋችሁ እንግዲያውስ "እባቡ ሰይጣን ነው" ማለት ነው፦
ዘፍጥረት 3፥1 እባብም ያህዌህ አምላክ ከፈጠረው ከምድር አውሬ ሁሉ ይልቅ "ብልህ" ነበረ። וְהַנָּחָשׁ֙ הָיָ֣ה עָר֔וּם מִכֹּל֙ חַיַּ֣ת הַשָּׂדֶ֔ה אֲשֶׁ֥ר עָשָׂ֖ה יְהוָ֣ה אֱלֹהִ֑ים

በዐማርኛ ትርጉም ላይ "ተንኮለኛ" ብለው ያስቀመጡት የዕብራይስጡ ቃል "አሩም" עָרוּם ሲሆን "ብልህ"prudent" ማለት ነው፥ ምሳሌ 12፥23 ተመልከት! እባቡ የምድር አውሬ ነው። ሴቲቱን ሲያነጋግር የነበረውም ይህ የምድር አውሬ ነው፥ ሴቲቱን ስላሳሳተ ተብሎ የተረገመው ይህ እባብ ነው፦
ዘፍጥረት 3፥14 ያህዌ አምላክም እባቡን አለው፦ "ይህን ስላደረግህ ከእንስሳት ከምድር አራዊትም ሁሉ ተለይተህ አንተ የተረገምህ ትሆናለህ፤ በሆድህም ትሄዳለህ፥ አፈርንም በሕይወትህ ዘመን ሁሉ ትበላለህ"።

የዘፍጥረት ዐውደ ንባቡን"contextual passage" ውስጥ ስለ ሰይጣን የሚናገር ምንም ሽታው የለው። ስድሳ ስድስቱ መጽሐፍ ላይ ዲያብሎስ አዳምን እና ሔዋንን እንዳሳሳተ የሚናገር ምንም ጥቅስ የለም፥ ነገር ግን መቃቢያን ላይ ዲያብሎስ አዳምን እና ሔዋንን ሸንግሎ እንዳሳሳታቸው ይናገራል፦
1ኛ መቃብያን 19፥6 ዲያብሎስም “እንደ ፈጣሪያችሁ እንደ እግዚአብሔር ትሆናላችሁ” ብሎ ሸንግሎ አባታችን አዳምን እና እናታችንን ሔዋንን ወደ እርሱ ስሕተት ወሰዳቸው።

ዲያብሎስ የምድር አውሬ የሆነው እባብ ነውን? ዲያብሎስ ጥንተ ተፈጥሮው ከጂን ወይም እንደ እናንተ እምነት ከመላእክት አይደለምን? መልሱ፦ "እባቡ ዲያብሎስ ሳይሆን ዲያብሎስ በእባቡ ተጠቅሞ አሳሳታቸው" ከሆነ እንግዲያውስ ዛፉ አሏህ ሆኖ ሳይሆን አሏህ ዛፉን እንዲናገር ማድረግ ምን ያቅተዋል? በባይብል እኮ ፈጣሪ አህያ እና ድንጋይ እንዲናገሩ የሚያደርግ ነው፦
2 ጴጥሮስ 2፥16 ቃል የሌለው "አህያ" በሰው ቃል ተናግሮ የነቢዩን እብድነት አገደ።
ኢያሱ 24፥27 እነሆ የተናገረንን የያህዌን ቃል ሁሉ ሰምቶአልና "ይህ ድንጋይ" ይመሰክርብናል።

ድንጋይ በጥንተ ተፈጥሮው የሚሰማ እና የሚናገር እንዳልሆነ ቅቡል ቢሆንም ቅሉ ግን በተአምር የያህዌን ቃል ሰምቶ መናገሩ እሙን ነው። አሏህ በትንሳኤ ቀን እኮ መስማት እና መናገር የማይችለውን የሰውን ቆዳ እንዲሰማ እና እንዲናገር ያደርጋል፦
41፥21 ለቆዳዎቻቸውም «በእኛ ላይ ለምን መሰከራችሁብን?» ይላሉ፡፡ «ያ አንዳቹን ነገር ሁሉ ያናገረው አላህ አናገረን፡፡ እርሱም በመጀመሪያ ጊዜ ፈጠራችሁ፡፡ ወደእርሱም ትመለሳላችሁ» ይሏቸዋል፡፡ وَقَالُوا لِجُلُودِهِمْ لِمَ شَهِدتُّمْ عَلَيْنَا ۖ قَالُوا أَنطَقَنَا اللَّهُ الَّذِي أَنطَقَ كُلَّ شَيْءٍ وَهُوَ خَلَقَكُمْ أَوَّلَ مَرَّةٍ وَإِلَيْهِ تُرْجَعُونَ

ስለዚህ "ዛፍ እንዴት ይናገራል" ተብሎ መታመስ እና መተራመስ አስፈላጊ አይደለም። አምላካችን አሏህ ሂዳያህ ይስጣችሁ! ለእኛም ጽናቱን ይስጠን! አሚን።

ከዐቃቢ ኢሥላም ወሒድ
https://t.me/Wahidcom

ወሠላሙ ዐለይኩም