Get Mystery Box with random crypto!

የእግዚአብሔር አካል በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ እጅግ በጣም አዛኝ በሆነው። 42፥11 | ወሒድ የንጽጽር ማኅደር

የእግዚአብሔር አካል

በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ እጅግ በጣም አዛኝ በሆነው።

42፥11 የሚመስለው ምንም "ነገር" የለም፡፡ እርሱም ሰሚው ተመልካቹ ነው፡፡ لَيْسَ كَمِثْلِهِ شَيْءٌ ۖ وَهُوَ السَّمِيعُ الْبَصِيرُ

አምላካችን አሏህ ከፍጡራኑ ጋር የማይመሳሰል የራሱ ባሕርያት አሉት፥ እርሱን የሚመስል ምንም ነገር የለም፦
42፥11 የሚመስለው ምንም "ነገር" የለም፡፡ እርሱም ሰሚው ተመልካቹ ነው፡፡ لَيْسَ كَمِثْلِهِ شَيْءٌ ۖ وَهُوَ السَّمِيعُ الْبَصِيرُ

እዚህ አንቀጽ ላይ "ሚስል" مِثْل በሚለው ቃል ላይ መነሻ ቅጥያ ሆኖ የገባው "ከ" كَ የሚል መስተዋድድ "በጭራሽ" ማለት ነው፥ "ነገር" በሚለው ቃል ውስጥ ሁሉም ፍጡራን የሚካተቱ ሲሆኑ ከፍጡራን መካከል እርሱን የሚመስል ብጤ በጭራሽ የለም። እዚሁ አንቀጽ ላይ አሏህ "ሰሚ እና ተመልካች" እንደሆነ ተገልጿል፥ ሰውም "ሰሚ እና ተመልካች" እንደሆነ ሌላ አንቀጽ ላይ ተገልጿል፦
76፥2 እኛ ሰውን በሕግ ግዳጅ የምንፈትነው ስንኾን ቅልቅሎች ከኾኑ የፍትወት ጠብታ ፈጠርነው፡፡ ሰሚ ተመልካችም አደረግነው*፡፡ إِنَّا خَلَقْنَا الْإِنسَانَ مِن نُّطْفَةٍ أَمْشَاجٍ نَّبْتَلِيهِ فَجَعَلْنَاهُ سَمِيعًا بَصِيرًا

የአሏህ መስማት እና ማየት ከፍጡራን ጋር እንደማይመሳሰል እና እንደማይነጻጸር ሁሉ የፈጣሪ ባሕርዮት ከፍጡራን ባሕርዮት ጋር አይመሳሰለም አይነጻጸርም።
በኢሥላም ያለውን የአሏህ ሲፋት በመጠኑ እዚህ ድረስ ካየን ዘንዳ በባይብል እግዚአብሔር የአካል ክፍል የሆኑት ከንፈር እና ምላስ አለው፦
ኢሳይያስ 30፥27 "ከንፈሮቹም" ቍጣን የሞሉ ናቸው፥ "ምላሱም" እንደምትበላ እሳት ናት።

"ከንፈሮች" የሚለው "ከንፈር" ለሚል ብዙ ቁጥር ሲሆን የላይኛው ከንፈር እና የታችኛው ከንፈር ያመለክታል፥ ምላስ ግን በነጠላ ስለሆነ አንድ ብቻ ይመስላል። "ባት" ሲባል ደንግጠህ "የግድ ሥጋ መሆን አለበት" ካልክ ከንፈር እና ምላስ የግድ ሥጋ መሆን አለበት ብዬ እሞግትካለው፥ በሰፈሩት ቁና መሰፈር ግድ ነውና። እግዚአብሔር የአካል ክፍሎች የሆኑት ዓይኖች፣ ቅንድቦች እና ጆሮዎች አሉት፦
መዝሙር 11፥4 "ዓይኖቹ" ወደ ድሃ ይመለከታሉ፥ "ቅንድቦቹም" የሰው ልጆችን ይመረምራሉ።
1 ጴጥሮስ 3፥12 የጌታ ዓይኖች ወደ ጻድቃን ናቸውና፥ "ጆሮዎቹም" ለጸሎታቸው ተከፍተዋል።

"ዓይኖች" "ቅንድቦች" እና "ጆሮዎች" የተባሉት "ዓይን" "ቅንድብ" "ጆሮ" ለሚሉት ብዙ ቁጥር ስለሆነ ቢያንስ ከአንድ በላይ ዓይኖች፣ ቅንድቦች እና ጆሮዎች አሉት፥ ሰው ላይ ያየሁት ዓይኖች፣ ቅንድቦች እና ጆሮዎች ሥጋ ስለሆኑ "የእግዚአብሔር ዓይኖች፣ ቅንድቦች እና ጆሮዎች ሥጋ ናቸው" ብዬ ደረቅ ንትርክ መነታረክ አላቃተኝም። እግዚአብሔር የአካል ክፍሎች የሆኑት አፍንጫ እና አፍ አሉት፦
ዘጸአት 15፥8 "በአፍንጫህ" እስትንፋስ ውኆች ተከመሩ።
መዝሙር 33፥6 ሠራዊታቸውም ሁሉ "በአፉ" እስትንፋስ።

ሰው የሚተነፍስበት አፍንጫ እና አፍ ሥጋ ስለሆነ "እግዚአብሔር የሚተነፍስበት አፍንጫ እና አፍ ሥጋ ነው" ብዬ ጉንጭ አልፋ ንትርክ መነታረክ አላቃተኝም። እግዚአብሔር የአካል ክፍሎች የሆኑት ክንድ፣ ብብት፣ እግሮች፣ እጆች፣ ጣቶች አሉት፦
ኢሳይያስ 40፥11 ጠቦቶቹን "በክንዱ" ሰብስቦ "በብብቱ" ይሸከማል።
መዝሙር 132፥7 "እግሮቹ" በሚቆሙበት ስፍራ እንሰግዳለን።
መዝሙር 119፥73 "እጆችህ" ሠሩኝ አበጃጁኝም።
መዝሙር 8፥3 "የጣቶችህን" ሥራ ሰማዮችን ባየሁ ጊዜ፥

ባሻዬ እኔ የማውቀው ክንድ፣ ብብት፣ እግሮች፣ እጆች፣ ጣቶች ሥጋ ናቸው፥ እና እግዚአብሔር ልክ እንደ ሰው ክንድ፣ ብብት፣ እግሮች፣ እጆች፣ ጣቶች አሉትን? "አይ ክንድ፣ ብብት፣ እግሮች፣ እጆች፣ ጣቶች፣ አፍንጫ፣ አፍ፣ ዓይኖች፣ ቅንድቦች፣ ጆሮዎች፣ ምላስ፣ ከንፈሮች ትርጉም አላቸው" ካላችሁ በጥቅስ መሞገት እንጂ ከኪስ እየመዘዙ እንቶ ፈንቶ ማውራት ውኃ የማያነሳ እና የማይቋጥር ሙግት ነው። ምክንያቱም እነዚህ የአካል ክፍሎች ትርጉም መስጠት ሠለስቱ ምዕት ከልክለዋል፦
ሃይማኖተ አበው ምዕራፍ 19 ቁጥር 33
“ለእግዚአብሔር ዓይኖች እና ጆሮዎች እንዳሉት መጽሐፍት የተናገሩት እና የቀሩት እንዳሉት ስለ እግዚአብሔር የተነገረው ሁሉ የታመነ እውነተኛ እንደሆነ እናምናለን፥ ነገር ግን አይመረመርም አይታሰብም”።

"ሠለስቱ ምዕት" ማለት በ 325 ድኅረ ልደት በኒቂያ ጉባኤ የተሰበሰቡት 318 ሊቃውንት ናቸው፥ እነርሱ፦ "የቀሩት" ያሉት ከዓይኖች እና ከጆሮዎች ሌላ የተገለጹትን የአካል ክፍሎች ነው፦
ሃይማኖተ አበው ምዕራፍ 28 ቁጥር 30
“ለእግዚአብሔር ዓይን፣ ጆሮ፣ እጅ፣ እግር እንዳለው የተነገረው ሁሉ ስለ እግዚአብሔር በከበሩ መጻሕፍት የተጻፈ ሁሉ የታመነ የተረዳ ነው፥ የተናገርነው ሁሉ አለው። ነገር ግን አይመረመርም አይታወቅም”።

እርማችሁን አውጡ! ጆሮ፣ እጅ፣ እግር እንዳለ እንቅጩን ፍርጥ አርገው ተናግረዋል። ለእግዚአብሔር እጅ፣ ጥፍር፣ እግር እንዳለው አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ በመጽሐፈ ምሥጢር ተናግሯል፦
መጽሐፈ ምሥጢር ምዕራፍ 1 ቁጥር 62
“እግዚአብሔር እጆች እና ክንድ፣ ጥፍር እንዳለው ዕወቁ”።