Get Mystery Box with random crypto!

የባሕርይ እናት በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ እጅግ በጣም አዛኝ በሆነው፡፡ 3፥36 «እኔም | ወሒድ የንጽጽር ማኅደር

የባሕርይ እናት

በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ እጅግ በጣም አዛኝ በሆነው፡፡

3፥36 «እኔም እርስዋን እና ዝርያዋን ከተረገመው ሰይጣን በአንተ እጠብቃቸዋለሁ» وَإِنِّي أُعِيذُهَا بِكَ وَذُرِّيَّتَهَا مِنَ الشَّيْطَانِ الرَّجِيمِ

የመርየም እናት፦ "እርስዋን እና ዝርያዋን" በማለቷ ዒሣ የመርየም ዘር እንደሆነ ቁርኣን አስረግጦ እና ረግጦ ያሳያል፦
3፥36 «እኔም እርስዋን እና ዝርያዋን ከተረገመው ሰይጣን በአንተ እጠብቃቸዋለሁ» وَإِنِّي أُعِيذُهَا بِكَ وَذُرِّيَّتَهَا مِنَ الشَّيْطَانِ الرَّجِيمِ

"ዙሪያህ" ذُرِّيَّة ማለት "ዘር"offspring" ማለት ሲሆን "ዙሪያህ" ذُرِّيَّة በሚለው መድረሻ ቅጥያ ላይ "ሃ" هَا የሚለው አንስታይ አገናዛቢ ተውላጠ ስም መርየምን አመላካች ስለሆነ ዒሣ የመርየም ዘር መሆኑን ቁልጭ እና ፍንትው አርጎ ያሳያል። "ባሕርይ" ማለት "ምንነት" ማለት ሲሆን ለምሳሌ፦ የእኔ እናት ለእኔ የባሕርይ እናት ናት፥ ምክንያቱም የእኔ መገኛ እናቴ ስለሆነች እና እርሷን አህዬ እና መስዬ ከማንነቷ ማንነት ከምንነቷ ምንነት ወስጃለው፥ በተመሳሳይ የኢየሱስ መገኛው እናቱ ማርያም ስለሆነች ከእርሷ ምንነት ምንነት ወስዶ እና ከእርሷ ማንነት ማንነት ወስዶ ሰው ሆኗል።
ይህ ሆኖ ሳለ በዐበይት ክርስትና ኢየሱስ "ከአብ ባሕርይ ባሕርይን እንዲሁ ከአካሉ አካልን ወስዶ የተገኘ አምላክ" ተብሎ ይታመናል፦
ሃይማኖተ አበው 74፥8 "ከባሕርይ አምላክ የተገኘ የባሕርይ አምላክ"።
ሃይማኖተ አበው 70፥17 "ከአብ ባሕርይ የተገኘ አምላክ"።
ሃይማኖተ አበው 78፥8 "አካል ዘእምአካል ባሕርይ ዘእምባሕርይ የተወለደው ልደት የማይመረመር ነው"።
ሃይማኖተ አበው 121፥10 "ከአብ አካል ዘእምአካል ባሕርይ ዘእምባሕርይ ተወልዶ የመጣ አምላክ"።

ኢየሱስ ከአብ ተገኘ ሲባል ምን ማለት ነው? የሚለውን ጥያቄ ርዕስ እንዳያስቀይስ ሙግቱን አጥበበነው እውን ማርያም ለመለኮት የባሕርይ እናቱ ናትን? መለኮት ከማርያም ለሁለተኛ ጊዜ ተገኝቷልን? ይህንን ነጥብ እስቲ እንመልከት፦
ሃይማኖተ አበው 74፥13 "የመለኮት መገኘት ከድንግል አይደለም፥ ከአብ ከተወለደ በኃላ ለመለኮት ሁለተኛ ልደት አይሻምና"።

ስለዚህ ከማርያም ተፀንሶ የተወለደው ሰው ብቻ እና ብቻ ነው፥ ማርያም መለኮትን ከወለደች ሁለተኛ ልደት አይሆንምን? መለኮትን ካልወለደች እና መለኮት ከእርሷ ካልተገኘ የአምላክ እናት አይደለችም ማለት ነው። ወይም ማርያም ለመለኮት የጸጋ እናት እንጂ የባሕርይ እናቱ አይደለች ይሆን? ውስብስብ ትምህርት ነው፦
ሰይፈ ሥላሴ ዘእሑድ ምዕራፍ 8 ቁጥር 73
"በመለኮት እናት በድንግል ማርያም"።

ማርያም ለመለኮት የባሕርይ እናቱ ናትን? መለኮትስ ለማርያም የባሕርይ ልጇ ነውን? "አዎ" ካላችሁን መለኮትነቱን አስገኝታለችን? እርሱስ መለኮትነቱ ከእርሷ ተገኝቷልን?
እሺ ይሁን እንበልና መለኮት አንድ ከሆነ ማርያም የሥላሴን መለኮት ወልዳለችን? ወይስ የወለደችው የወልድን መለኮት ብቻ ነው? የአብ እና የመንፈስ ቅዱስ መለኮትነት ካልወለደች ስንት መለኮት ሊኖር ነው? ማርያም "ቴዎቶኮስ" ናትን? "ቴዎቶኮስ" Θεοτόκος የሚለው ቃል "ቴዎስ" Θεός እና "ቶኮስ" τόκος ከሚል ሁለት ቃላት የተዋቀረ ሲሆን "ወላዲተ መለኮት" "የመለኮት ወላጅ" ማለት ነው፥ መለኮት ከእሷ ሳይገኝ እንዴት ወልዳ እናቱ ትሆናለች? በነገራችን ላይ "መለኮት" ማለት በቀላሉ "አምላክ" ማለት ነው።

የቁስጥንጥንያው ኤጲስ ቆጶስ ንስጥሮስ "ማርያም የወለደች ሰው ብቻ ነው" ብሎ ኢየሱስን ምንታዌ ከማድረግ ባሻገር ከማርያም ተፀንሶ የተወለደውን ሰው የሥላሴ አራተኛ አባል አርጎ ሲያርፈው ይህንን የሥላሴን ርባቤ "እንፈታለን" ብሎ የእስክንድርያው ኤጲስ ቆጶስ ቄርሎስ ሁለት አካላት የአብ ልጅ መለኮታዊ አካል እና የማርያም ልጅ ሰዋዊ አካል አንድ አካል ሆኑ በማለት ማርያምን "ቴዎቶኮስ" ብሏታል፦
ሃይማኖተ አበው 49፥15 "ቅድስት ሥላሴን እንዴት አራተኛ አካል ያደርጋሉ? እንዲህ ያለ የተነቀፈ ነገር ሊነገር አይገባውም"።

ንስጥሮስ እና ፕሮቴስታንት፣ የይሆዋ ምስክር፣ ሰባተኛው ቀን የመገለጣውያን ቤተክርስቲያን"The Seventh-day Adventist Church" የሚባሉ አንጃዎች "ማርያም "ኽሪስቶቶኮስ" ብቻ ናት" ብለው ያምናሉ፥ "ኽሪስቶቶኮስ" Χριστοτόκος የሚለው ቃል "ኽሪስቶስ" χρῑστός እና "ቶኮስ" τόκος ከሚል ሁለት ቃላት የተዋቀረ ሲሆን "ወላዲተ ክርስቶስ" "የክርስቶስ ወላጅ" ማለት ነው። ክርስቶስ ደግሞ የአምላክ እንጂ አምላክ አይደለም፦
1ኛ ቆሮንቶስ 3፥23 ክርስቶስ የአምላክ ነው። Χριστὸς δὲ Θεοῦ.
ሉቃስ 9፥20 እናንተስ እኔ ማን እንደ ሆንሁ ትላላችሁ? አላቸው። ጴጥሮስም መልሶ፦ "የአምላክ ክርስቶስ ነህ" አለ። εἶπεν δὲ αὐτοῖς Ὑμεῖς δὲ τίνα με λέγετε εἶναι; Πέτρος δὲ ἀποκριθεὶς εἶπεν Τὸν Χριστὸν τοῦ Θεοῦ.

በእርግጥም ማርያም የክርስቶስ ኢየሱስ የባሕርይ እናቱ ናት። መለኮት ግን አስገኝ እንጂ ከፍጡር ሆነ ከመለኮት የሚገኝ አይደለም፥ መለኮት መነሻ፣ ምንጭ እና መገኛ ካለው መለኮት እንዴት ይባላል? መነሻ እና ጅማሮ ያለው እኮ ፍጡር ብቻ ነው።
አምላካችን ሏህ ሂዳያህ ይስጣችሁ! ለእኛም ጽናቱን ይስጠን! አሚን።

ከዐቃቢ ኢሥላም ወሒድ
https://t.me/Wahidcom

ወሠላሙ ዐለይኩም