Get Mystery Box with random crypto!

'ብጤ' ለሚለው የገባው ቃል 'ኩፉው' كُفُو ሲሆን 'አቻ' 'እኩያ' 'ወደር' ማለት ነው፥ለአሏህ | ወሒድ የንጽጽር ማኅደር

"ብጤ" ለሚለው የገባው ቃል "ኩፉው" كُفُو ሲሆን "አቻ" "እኩያ" "ወደር" ማለት ነው፥ለአሏህ አንድም "አቻ" "እኩያ" "ወደር" የለውም። "አንድም" ለሚለው ለሚለው የገባው ቃል "አሐድ" أَحَدٌ ሲሆን "ሸኽስ" شَخْص በሚል የመጣ ነው፦
ኢማም ቡኻርይ መጽሐፍ 67, ሐዲስ 153
ዐብደሏህ እንደተረከው፦ "ነቢዩም"ﷺ" እንዲህ አሉ፦ " "ከአላህ የበለጠ የሚቀና "አንድም" የለም"። عَنْ عَبْدِ اللَّهِ، عَنِ النَّبِيِّ صلى الله عليه وسلم قَالَ ‏ "‏ مَا مِنْ أَحَدٍ أَغْيَرُ مِنَ اللَّهِ،
ኢማም ቡኻርይ መጽሐፍ 97, ሐዲስ 44
ዐብዱል ማሊክ እንደተናገረው፦ "ከአላህ የበለጠ የሚቀና "ማንነት" የለም። عَنْ عَبْدِ الْمَلِكِ ‏"‏ لاَ شَخْصَ أَغْيَرُ مِنَ اللَّهِ ‏"‌‏.‏

"አንድ" ለሚለው የገባው ቃል "አሐድ" أَحَدٌ ሲሆን "ማንነት" ለሚለው የገባው ቃል "ሸኽስ" شَخْص ነው፥ ስለዚህ አሏህ በማንነቱ አንድ ነው። ባል በሚስቱ እንዲሁ ንጉሥ በመንግሥቱ እንደሚቀና የፈጠረን አንድ አምላክ በአምልኮቱ ይቀናል፦
ዘጸአት 20፥6 እኔ ያህዌህ አምላክህ ቀናተኛ አምላክ ነኝና።

ገለቴ ከመንጨርጨር እና ከመንተክተክ ይልቅ መቅናት አውታዊ እንደሆነ ከራስህ መጽሐፍ ተረዳ! ስለዚህ አሏህ በአምልኮቱ መቅናቱ ላይ እርር እና ምርር አትበል። አሏህ፦ "ቁል" قُلْ በሚል ትእዛዛዊ ግሥ በአምልኮው እንዳናጋራ በአጽንዖት እና በአንክሮት ነግሮናል፦
18፥110 "በጌታውም አምልኮ አንድንም አያጋራ"። وَلَا يُشْرِكْ بِعِبَادَةِ رَبِّهِ أَحَدًا

"አንድንም" ሲል በአሏህ አምልኮ "አንድንም ማንነት" ማጋራት እንደሌለብን ያሳያል፥ አምልኮ የአሏህ ሐቅ እና ገንዘብ ብቻ ነው።
ተወዳጁ ነቢያች"ﷺ" አንድ ማንነት ስለነበሩ በቁርኣን "አሐድ" በሐዲስ "ሸኽስ" شَخْص ተብለዋል፦
54፥24 «ከእኛ የኾነን "አንድን" ሰው እንከተለዋለን? እኛ ያን ጊዜ በስህተትና በዕብደት ውስጥ ነን» አሉ፡፡ فَقَالُوا أَبَشَرًا مِّنَّا وَاحِدًا نَّتَّبِعُهُ إِنَّا إِذًا لَّفِي ضَلَالٍ وَسُعُرٍ
ጃምዒ አት-ቲርሚዚይ መጽሐፍ 43, ሐዲስ 24
አነሥ እንደተረከው፦ "በእነርሱ ዘንድ ከአሏህ መልእክተኛ"ﷺ" የበለጠ ተወዳጅ "ማንነት" አልነበረም"። عَنْ أَنَسٍ، قَالَ لَمْ يَكُنْ شَخْصٌ أَحَبَّ إِلَيْهِمْ مِنْ رَسُولِ اللَّهِ صلى الله عليه وسلم

መቼም ነቢያች"ﷺ" አንድ ማንነት ብቻ ነበሩ እንጂ ሥላሴ አልነበሩም። ሌላው ተሰምሮ ሊጤንበት የሚገባው ነጥብ "አለዚ" اَلَّذِي ኢሥሙል መውሱል ሲሆን ሙፍረድ ለሆነ ማንነት የምንጠቀምበት ነው፥ ከአንድ በላይ ለሆኑ ማንነቶች የምንጠቀምበት በሙሰና "አለዘይኒ" اَللَّذَيْنِ በጀምዕ "አለዚነ" اَلَّذِينَ ነው። አሏህ አንድ ማንነት ስለሆነ "አለዚ" اَلَّذِي ብቻ ተብሏል፦
7፥54 ጌታችሁ "ያ" ሰማያትን እና ምድርን በስድስት ቀኖች ውስጥ የፈጠረ አላህ ነው፡፡ إِنَّ رَبَّكُمُ اللَّهُ الَّذِي خَلَقَ السَّمَاوَاتِ وَالْأَرْضَ فِي سِتَّةِ أَيَّامٍ

"ያ" ለሚለው አንጻራዊ ተውላጠ ስም የገባው "አለዚ" اَلَّذِي እንደሆነ አስምርበት! ይህንን የሰዋስው ሙግት አፍጦና አፋጦ፤ አግጦና አንጋጦ ስታነቡ ቆሌ ተገፎ እና ቆሽት አሮ፦ "ሰማይ ተንዶ ሊናጫነኝ ነው፥ ምድር ተከፍቶ ሊውጠኝ ነው" ከምትሉ አውንታዊ መረዳት ይዛችሁ ልባችሁን ብትከፍቱ መልካም ነው። አምላካችን አሏህ ሂዳያህ ይስጣችሁ! ለእኛም ጽናቱን ይስጠን! አሚን።

ከዐቃቢ ኢሥላም ወሒድ
https://t.me/Wahidcom

ወሠላሙ ዐለይኩም