Get Mystery Box with random crypto!

አሏህ አንድ ነው! በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ እጅግ በጣም አዛኝ በሆነው። 12፥1 በል | ወሒድ የንጽጽር ማኅደር

አሏህ አንድ ነው!

በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ እጅግ በጣም አዛኝ በሆነው።

12፥1 በል «እርሱ አላህ አንድ ነው»። قُلْ هُوَ اللَّهُ أَحَدٌ

"አሏህ አንድ ነው" ስንል ሚሽነሪዎች፦ "በምንድን ነው አንድ? በማንነት ወይስ በምንነት? ብለው ይጠይቃሉ፥ ምክንያቱም በእነርሱ እምነት "አምላክ በማንነት ሥስት በምንነት አንድ ነው" ተብሎ ስለሚታመን "አሏህ አንድ ምንነት እንጂ ስንት ማንነት እንዳለው አይታወቅም" የሚል ባቦሰጥ ንግግር ይናገራሉ።
"ማንነት" ማለት "ማን ነው" ብለን የምንጠይቅበት የምንነት መገለጫ"identity" ሲሆን "ምንነት" ማለት ደግሞ "ምንድን ነው" ብለን የምንጠይቅበት የማንነት መሠረት"being" ነው። እኔ በምንነቴ ሰው ነኝ፥ የፈጠረኝ አሏህ ግን በምንነቱ አምላክ ነው። እርሱም ምንነቱን የማያጋራ አንድ አምላክ ነው፦
2፥163 አምላካችሁም አንድ አምላክ ብቻ ነው፥ ከእርሱ በቀር ሌላ አምላክ የለም፡፡ እርሱ እጅግ በጣም ርኅሩህ አዛኝ ነው፡፡ وَإِلَـٰهُكُمْ إِلَـٰهٌ وَاحِدٌ ۖ لَّا إِلَـٰهَ إِلَّا هُوَ الرَّحْمَـٰنُ الرَّحِيمُ

እዚህ አንቀጽ ላይ "አንድ" ለሚለው የገባው ቃል "ዋሒድ" وَاحِد ሲሆን አምላካች አሏህ አንድ አምላክ እንደሆነ አስረግጦ ያሳያል። እኔ በማንነቴ አንድ ስሆን እራሴን የምገልጽበት "እከሌ" ለምሳሌ፦ "ወሒድ" እባላለው፥ ሁሉን የፈጠረ አንድ አምላክ በማንነቱ አንድ ሲሆን "አሏህ" ይባላል፦
20፥14 እኔ አላህ እኔ ነኝ፥ ከእኔ በቀር አምላክ የለምና አምልከኝ፡፡ ሶላትንም እኔን ለማውሳት ስገድ፡፡ إِنَّنِي أَنَا اللَّهُ لَا إِلَـٰهَ إِلَّا أَنَا فَاعْبُدْنِي وَأَقِمِ الصَّلَاةَ لِذِكْرِي

"አና" أَنَا ማለት "እኔ" ማለት ሲሆን "አና" أَنَا የሚለው ደሚሩ አሽ-ሸኽስ ማንነትን ያሳያል፥ "እኔ" አንድ ነጠላ ማንነትን"one singular person" ታሳቢ እና ዋቢ ያደረገ ነው። ስለዚህ "እኔ" የሚለውን መደብ ተውላጠ ስም"personal pronoun" አሏህ አንድ ማንነት እንደሆነ ቁልጭ አርጎ ያሳያል፥ ይህ አንድ ማንነት ምንነቱ አምላክ ስለሆነ "ከእኔ በቀር አምላክ የለም" በማለት ይናገራል። "አምልኩን" እያሉ የሚናገር አንድ "እኔነት" ነው፦
21፥92 "እኔም" ጌታችሁ ነኝና "አምልኩኝ"፡፡ وَأَنَا رَبُّكُمْ فَاعْبُدُونِ

"ሸኽስ" شَخْص ማለት "ማንነት"person" ማለት ሲሆን በነሕው ሕግ "ሸኽሱል ሙፍረድ" الشَخْص المُفْرَد ማለትም "ነጠላ ማንነት"singular person" ለመጠቀም በሙተከለም "አና" أَنَا ነው፥ ስለዚህ አሏህ "አና" ስላለ በማንነት አንድ ነው። "ሁወ" هُوَ በጋኢብ ለአንድ ነጠላ ማንነት የሚውል ደሚሩ አሽ ሸኽስ ከሆነ አሏህ ስለ ራሱ "ቁል" قُلْ በሚል ትእዛዛዊ ግሥ "ሁወ" هُوَ ብሏል፦
12፥1 በል «እርሱ አላህ አንድ ነው»። قُلْ هُوَ اللَّهُ أَحَدٌ

እዚህ አንቀጽ ላይ "አንድ" ለሚለው የገባው ቃል "አሐድ" أَحَدٌ ሲሆን ምንም መፈናፈኛ እንዳይኖር አርጎ ከርችሞታል፥ ምክንያቱም "አሐድ" አንድ ማንነትን ለማሳየት ብዙ ቦታ መጥቷል፦
72፥22 «እኔ ከአላህ ቅጣት አንድም አያድነኝም፡፡ ከእርሱም ሌላ መጠጊያን አላገኝም» በላቸው፡፡ قُلْ إِنِّي لَن يُجِيرَنِي مِنَ اللَّهِ أَحَدٌ وَلَنْ أَجِدَ مِن دُونِهِ مُلْتَحَدًا
72፥20 «እኔ የማመልከው ጌታዬን ብቻ ነው፡፡ በእርሱም አንድንም አላጋራም» በል፡፡ قُلْ إِنَّمَا أَدْعُو رَبِّي وَلَا أُشْرِكُ بِهِ أَحَدًا

"ከአላህ ቅጣት አንድም አያድነኝም" ሲል ከአሏህ ጋር የሚያድን አንድ ማንነት እንደሌለ የሚያሳይ ሲሆን "በእርሱም አንድንም አላጋራም" ሲል ከአሏህ ጋር አምልኮትን የሚጋራ አንድ ማንነት እንደሌለ ያሳያል። አሏህን በማንነት የሚመስል ማንም ማንነት የለም፦
112፥4 ለእርሱም አንድም ብጤ የለውም፡፡ وَلَمْ يَكُن لَّهُ كُفُوًا أَحَدٌ