Get Mystery Box with random crypto!

ታላቁ ስም በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ እጅግ በጣም አዛኝ በሆነው፡፡ 3፥2 አላህ ከእርሱ | ወሒድ የንጽጽር ማኅደር

ታላቁ ስም

በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ እጅግ በጣም አዛኝ በሆነው፡፡

3፥2 አላህ ከእርሱ በስተቀር ሌላ አምላክ የለም፡፡ እርሱ "ሕያው" ሁሉን ነገር አስተናባሪ ነው፡፡ اللَّهُ لَا إِلَـٰهَ إِلَّا هُوَ الْحَيُّ الْقَيُّومُ

በአንድ ወቅት ሙሴ አምላክን፦ "እነሆ እኔ ወደ እስራኤል ልጆች በመጣሁ ጊዜ፦ "የአባቶቻችሁ አምላክ ወደ እናንተ ላከኝ" ባልሁም ጊዜ፦ "ስሙስ ማን ነው? ባሉኝ ጊዜ፥ ምን እላቸዋለሁ? አለው፦
ዘጸአት 3፥13 ሙሴም ኤሎሂምን፦ "እነሆ እኔ ወደ እስራኤል ልጆች በመጣሁ ጊዜ፦ "የአባቶቻችሁ አምላክ ወደ እናንተ ላከኝ" ባልሁም ጊዜ፦ "ስሙስ ማን ነው? ባሉኝ ጊዜ፥ ምን እላቸዋለሁ? አለው። ויאמר משה אל־האלהים הנה אנכי בא אל־בני ישראל ואמרתי להם אלהי אבותיכם שלחני אליכם ואמרו־לי מה־שמו מה אמר אלהם׃

አምላክም ሙሴን፦ «ኤህዬህ አሼር ኤህዬህ» አለው፥ እንዲህ ለእስራኤል ልጆች፦ «ኤህዬህ» ወደ እናንተ ላከኝ" ትላለህ" አለው፦
ዘጸአት 3፥14 ኤሎሂምም ሙሴን፦ «ኤህዬህ አሼር ኤህዬህ» አለው፤ እንዲህ ለእስራኤል ልጆች፦ «ኤህዬህ» ወደ እናንተ ላከኝ ትላለህ" አለው። וַיֹּ֤אמֶר אֱלֹהִים֙ אֶל־מֹשֶׁ֔ה אֶֽהְיֶ֖ה אֲשֶׁ֣ר אֶֽהְיֶ֑ה וַיֹּ֗אמֶר כֹּ֤ה תֹאמַר֙ לִבְנֵ֣י יִשְׂרָאֵ֔ל אֶֽהְיֶ֖ה שְׁלָחַ֥נִי אֲלֵיכֶֽם׃

በዚህ ዐውድ መሠረት "ኤህዬህ" אֶֽהְיֶ֖ה የአምላክ ስም ነው፥ "ኤህዬህ" אֶֽהְיֶ֖ה ማለት "እሆናለው" "እኖራለው" "እኔ ነኝ" ማለት ነው፦
ዘጸአት 3፥12 በእውነት እኔ ከአንተ ጋር "እሆናለሁ"። וַיֹּ֙אמֶר֙ כִּֽי־אֶֽהְיֶ֣ה עִמָּ֔ךְ

እዚህ አንቀጽ ላይ "እሆናለሁ" ለሚለው የገባው የግሥ መደብ "ኤህዬህ" אֶֽהְיֶ֖ה ነው፥ "ኤህዬህ አሼር ኤህዬህ" אֶֽהְיֶ֖ה אֲשֶׁ֣ר אֶֽהְיֶ֑ה ማለት "እኔ ነኝ ማን እኔ ነኝ"I am who i am" ማለት ነው። በግዕዝ ንባባት ውስጥ "አህያ ሸራህያ" "ዘሀሎ ወይሄሉ" "እሄሉ ዘይሄሉ" "እከውን ዘእከውን" ይሉታል። በብሉይ ከተገለጹ ሌላው ስሙ "የህ" ወይም "ያህ" ነው፦
መዝሙረ ዳዊት 68፥4 ወደ ደመናዎች ለወጣም መንገድ አድርጉ! ስሙ "ያህ" ነው። סֹ֡לּוּ לָרֹכֵ֣ב בָּ֭עֲרָבֹות בְּיָ֥הּ שְׁמֹ֗ו וְעִלְז֥וּ לְפָנָֽיו׃

"ያህ" יָהּ የሚለው ስም "ያህዌህ" יְהוָ֔ה ለሚለው ስም ምጻረ-ቃል ነው፥ "ያህ" יָהּ በተለይ በሰዎች የተጸውዖ ስም ላይ በመነሻ ቅጥያ አሊያም በመድረሻ ቅጥያ ይመጣል። ለምሳሌ፦ "ኤል-ያህ" אֵלִיָּה በግዕዝ "ኤል-ያስ" በዐረቢኛ "ኢል-ያሥ" إِلْيَاس ሲሆን በመድረሻ ቅጥያ ላይ አለ፥ "ያህ-ሁ" יֵהוּא በግዕዝ "ኢዩ" በዐረቢኛ "ያ-ሁወ" يَاهُو ሲሆን በመነሻ ቅጥያ ላይ አለ። ቁርኣን ውስጥ "ያሥ" يَاس ወይም "ያ" يَّا ይህንኑ ምጻረ ቃል የሚያሳይ ነው፦
137፥123 ኢልያስም በእርግጥ ከመልክተኞቹ ነው፡፡ وَإِنَّ إِلْيَاسَ لَمِنَ الْمُرْسَلِينَ
19፥2 ይህ ጌታህ ባሪያውን ዘከሪያን በችሮታው ያወሳበት ነው፡፡ ذِكْرُ رَحْمَتِ رَبِّكَ عَبْدَهُ زَكَرِيَّا

"ኢል-ያሥ" إِلْيَاس ማለት "ያህ አምላክ ነው" ማለት ሲሆን "ዘከሪ-ያ" زَكَرِيَّا ማለት ደግሞ "ያህ ያወሳው" ማለት ነው። ያህ ምጻረ-ቃል የሆነበት ስም "ቴትራግራማተን" ወይም "ቴትራግራማቶን" τετραγράμματος ይባላል፥ "ቴትራስ" τέτταρες ማለት "አራት" ማለት ሲሆን "ግራማ" γράμμα ደግሞ "ፊደል" ማለት ነው። ከቀኝ ወደ ግራ የሚነበቡ አራቱ ተነባቢ ፊደላት "ዮድ" י‎ "ሔ" ה‎ "ዋው" ו‎ "ሔ" ה ወይም "የሐዋሐ" ሲሆኑ የፈጣሪ ታላቅ ስም ነው፦
ኢሳይያስ 42፥8 እኔ ያህዌህ ነኝ፥ ስሜ ይህ ነው። אֲנִ֥י יְהוָ֖ה ה֣וּא שְׁמִ֑י
ኤርምያስ 44፥26 "እነሆ በታላቅ ስሜ ምያለሁ" ይላል ያህዌህ፡፡הִנְנִ֨י נִשְׁבַּ֜עְתִּי בִּשְׁמִ֤י הַגָּדֹול֙ אָמַ֣ר יְהוָ֔ה

"ሃሼም" השם‌‎ ማለት "ስሙ" ማለት ሲሆን ይህ ታላቅ ስም በማሶሬት ጽሑፍ ውስጥ 6,518 ቦታ ተጠቅሷል፥ ቅሉ ግን አይሁዳውያን ይህንን ታላቅ ስም በከንቱ ላለመጥራት "አዶናይ" אֲדֹנָ֥י የሚለውን ስም ይጠቀሙ ነበር። "አዶናይ" אֲדֹנָ֥י ከሚለው ቃል "አታፍ ባታህን" א "ኦላም" o "ቃሜጽ" o‌ የሚባቡትን አናባቢ ፊደላት በ "ዮድ-ሄ-ዋው-ሄ" י‎ה‎ו‎ה ላይ ሲደቅሉት "ያህዌህ" יְהוָ֔ה የሚባል ስም ተፈጠረ፥ ይህንን የተለያዩ መድብለ ዕውቀቶች ያትታሉ፦
፨"ያህዌህ፦ ባዕድ ከሆነ ድምጽ ሰጪ ፊደላት ተዋቅሮ ያህዌህ በመባል በስህተት የተነበበ ነው"። Encyclopedia international volume 9, 1974 Edition.
፨"ያህዌህ፦ የቴትራግራማቶን የተሳሳተ አነባነብ ነው"። The universal jewish encyclopedia volume 6, 1948 Edition.
፨"ያህዌህ፦ ለእስራኤል አምላክ የተሳሳተ ስም ነው"። Encyclopedia Americana volume 16, 1976 Edition.

ላቲኖቹ ደግሞ "የ" የሚለውን "ጀ" እንዲሁ "ወ" የሚለውን "ቨ" በመጠቀም "ጆሆቫህ" በማለት ይጠቀማሉ። ከመነሻው ነቢያት ሲጠቀሙበት የነበረው ዕብራይስጥ ፓሌዎ ዕብራይስጥ እንጂ ማሶሬት ዕብራይስጥ አይደለም፥ ስለዚህ በፓሌዎ ዕብራይስጥ የተቀመጠው "ዮድ-ሄ-ዋው-ሄ" 𐤉𐤄𐤅𐤄 አጠራሩ በትክክል አይታወቅም። ሆነም ቀረ "ዮድ-ሄ-ዋው-ሄ" י‎ה‎ו‎ה የሚለው ቃል "ሀ-ወ-ሀ" הוה ማለትም "ኖረ" ከሚል ሥርወ-ቃል የመጣ ሲሆን "ሐዋሕ" חַוָּה ማለትም "ሕያው"the living one" ማለት ነው።