Get Mystery Box with random crypto!

ማዛጋት በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ እጅግ በጣም አዛኝ በሆነው፡፡ 24፥21 እርሱ በመጥፎ | ወሒድ የንጽጽር ማኅደር

ማዛጋት

በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ እጅግ በጣም አዛኝ በሆነው፡፡

24፥21 እርሱ በመጥፎ እና በሚጠላ ነገር ያዛልና፡፡ فَإِنَّهُ يَأْمُرُ بِالْفَحْشَاءِ وَالْمُنكَرِ

አምላካችን አሏህ መጥፎ ነገር እንድናደርግ አያዝም፥ ከዚያ ይልቅ በመልካም ነገር ያዛል። በተቃራኒው ከፈሕሻእ እና ከሙንከር ይከለክላል፦
7፥28 «አላህ በመጥፎ ነገር አያዝም፡፡ በአላህ ላይ የማታውቁትን ትናገራላችሁን» በላቸው፡፡ قُلْ إِنَّ اللَّهَ لَا يَأْمُرُ بِالْفَحْشَاءِ ۖ أَتَقُولُونَ عَلَى اللَّهِ مَا لَا تَعْلَمُونَ
16፥90 አላህ በማስተካከል፣ በማሳመርም እና ለዝምድና ባለቤት በመስጠትም ያዛል፡፡ ከመጥፎ እና ከሚጠላም ነገር ሁሉ፣ ከመበደልም ይከለክላል፡፡ إِنَّ اللَّهَ يَأْمُرُ بِالْعَدْلِ وَالْإِحْسَانِ وَإِيتَاءِ ذِي الْقُرْبَىٰ وَيَنْهَىٰ عَنِ الْفَحْشَاءِ وَالْمُنكَرِ وَالْبَغْيِ

"ፈሕሻእ" فَحْشَاء ማለት "መጥፎ" ማለት ሲሆን "ሙንከር" مُنكَر ደግሞ "የሚጠላ" ማለት ነው፥ ፈሕሻእ እና ሙንከር የሸይጧን እርምጃዎች ናቸው። ሸይጧን በፈሕሻእ እና በሙንከር ያዛልና፦
24፥21 እናንተ ያመናችሁ ሆይ! የሰይጣንን እርምጃዎች አትከተሉ፡፡ የሰይጣንንም እርምጃዎች የሚከተል ሰው ኀጢአትን ተሸከመ፡፡ እርሱ(ሰይጣን) በመጥፎ እና በሚጠላ ነገር ያዛልና፡፡ يَا أَيُّهَا الَّذِينَ آمَنُوا لَا تَتَّبِعُوا خُطُوَاتِ الشَّيْطَانِ ۚ وَمَن يَتَّبِعْ خُطُوَاتِ الشَّيْطَانِ فَإِنَّهُ يَأْمُرُ بِالْفَحْشَاءِ وَالْمُنكَرِ ۚ

ስለዚህ አንድ ድርጊት "ከአሏህ ነው" ማለት "ሐላል ነው" ማለት ሲሆን "ከሸይጧን ነው" ማለት ደግሞ "ሐራም ነው" ማለት ነው። እዚህ ድረስ ከተግባባን ማስነጠስ ከአሏህ ነው፥ ማዛጋት ደግሞ ግን ከሸይጧን ነው፦
ጃሚዒ አት-ተርሚዚይ መጽሐፍ 43, ሐዲስ 16
አቢ ሁረይራህ እንደተረከው፦ "የአሏህ መልእክተኛም"ﷺ" እንዲህ ሲሉ አሉ፦ "ማስነጠስ ከአሏህ ነው፥ ማዛጋት ግን ከሸይጧን ነው"። عَنْ أَبِي هُرَيْرَةَ، أَنَّ رَسُولَ اللَّهِ صلى الله عليه وسلم قَالَ ‏ "‏ الْعُطَاسُ مِنَ اللَّهِ وَالتَّثَاؤُبُ مِنَ الشَّيْطَانِ

"ማዛጋት ግን ከሸይጧን ነው" ማለት "ማዛጋት ሐራም ነው" ማለት ሲሆን ማዛጋት ክልክልነቱ ኢሥቲስናእ ሆኖ የመጣ ነው፥ ኢሥቲስናእ" اِسْتِثْنَاء‏ ማለት "ፍትቅታ"exceptional" ማለት ሲሆን ማዛጋት ክልክልነቱ በሶላት ውስጥ ነው፦
ጃሚዒ አት-ተርሚዚይ መጽሐፍ 2, ሐዲስ 222
አቢ ሁረይራህ እንደተረከው፦ "ነቢዩ"ﷺ" እንዲህ ሲሉ አሉ፦ "ማዛጋት በሶላት ውስጥ ከሸይጧን ነው፥ ከእናንተ አንደኛችሁ የሚያዛጋ በተቻለ መጠን ያፍነው"። عَنْ أَبِي هُرَيْرَةَ، أَنَّ النَّبِيَّ صلى الله عليه وسلم قَالَ ‏ "‏ التَّثَاؤُبُ فِي الصَّلاَةِ مِنَ الشَّيْطَانِ فَإِذَا تَثَاءَبَ أَحَدُكُمْ فَلْيَكْظِمْ مَا اسْتَطَاعَ ‏"‏ ‏

ሶላት ክቡር እና ክቡድ ሲሆን በሶላት ውስጥ የሚረብሽ ነገር መቆጣጠር አለብን፥ ማዛጋት በማፈን የምንጎዳን የጤና እክል ስለሌለው እና በሶላት ውስጥ ማፈን ለሶላታችን ጥቅም አለው። በሶላት ውስጥ ማዛጋትን ማፈን ሲቻል ማስነጠስን ማፈን ግን ፈጽሞ ከባድ ነው፥ ማስነጠስን ማፈን ከጤና አንጻር ወደ ታምቡር ስብራት ሊያመራ ይችላል። ምክንያቱም ማስነጠስን ማፈን ኃይለኛ የአየር ፍሰት በአፍንጫው በኩል አይወጣም፣ ወደ ውጭ ያልወጡ በሽታ አምጪ ተህዋሲያን ማይክሮቦች ወደ ጆሮው ክፍል ውስጥ ይገባሉ፣ የደም ሥሮች መሰባበር እና አልፎ አልፎም ዓይነ ስውርነትን ያስከትላል። ይህ ጉዳት ስላለው በሶላት ውስጥ ማስነጠስ እና "አል-ሓምዱ ሊሏህ" ማለት ሐላል ነው፥ ዋቢ ማስረጃዎች ይመልከቱ፦
ኢማም ሙሥሊም መጽሐፍ 5, ሐዲስ 192
ሡነን አቢ ዳውድ መጽሐፍ 15, ሐዲስ 126

እንግዲህ ኢሥልምና ዱር ሙሥሊሙ ሐሩር እንዲሆን ቀን ከሌሊት ደፋ ቀና እና ጠብ እርግፍ የሚሉት አግድም አደግ ዕውቀት ያላቸው ሚሽነሪዎች በኢሥላም ላይ ለሚቀጥፉት ቅጥፈት እኛ ዐቃቢያነ እሥልምና የኢሥላምን መሠረትና ውቅር፣ ዋልታና ማገር፣ ጥልቀትና ስፋት፣ ድርና ማግ በቅጡ ተረድተን ለሚቀጥፉት ቀጣፊዎች በምንተ አፍረት ሳይሆን በምንተ እዳ እንዲህ መልስ መስጠት እና የታሪክ ምፀት ከዐሊሞቻችን ለሚቀጥለው ትውልድ የሚሆን ሰፊ ምዕላድ ትተን መሄድ ግድ ይለናል።
አሏህ ሂዳያህ ይስጣቸው! ለእኛም ጽናቱን ይስጠን! አሚን።

ከዐቃቤ እሥልምና ወሒድ
https://t.me/Wahidcom

ወሠላሙ ዐለይኩም