Get Mystery Box with random crypto!

ማሞ ፦ ይኽኛው ደግሞ ከቀደሙት በእጅጉ ይለያል በሰው ስም ከመታወቁ ውጪ «ማሞ ሌላ መታወቂያው ሌላ | ሳሙኤል ተመስጌን ወ/ሃና

ማሞ ፦ ይኽኛው ደግሞ ከቀደሙት በእጅጉ ይለያል በሰው ስም ከመታወቁ ውጪ «ማሞ ሌላ መታወቂያው ሌላ» ፣ «ማሞ ቂሎ»… በሚሉት አገባቦች ስንሰማው የኖርን መጠሪያ ነው። ስለመነሻው ሳስስ ይህ መጠሪያ ሀገርኛ እንዳልሆነ ባውቅ የበለጠ ደንቆኛል። ታዲያ ከምን ተገኘ? አትሉም ፤ ማሞ ከልሳነ ጽርእ (ግሪኩ) ማሞን (μαμμωνᾶς) ከሚለው የተገኘ ነው፤ ለዚህ አስረጂዬ ደግሞ መጽሐፍ ቅዱስ ነው። ክርስቶስ ጌታችን ለሁለት ጌቶች መገዛት እንደማይቻላቸው በቃሉ ላፌዙት ገንዘብ ወዳጅ ፈሪሳውያን ሲያስተምር "ለእግዚአብሔርና ለገንዘብ መገዛት አትችሉም" ይላቸዋል ‘Ye cannot serve God and mammon.’ ወለንዋይ ባለው ወለማሞን ይላል የእኛም ግእዝ፡፡ ኪዳነ ወልድም በቃላቱ መዝገብ ሕፃናትን ማሞ ማሚት ማለት ከዚህ የወጣ ስም ሊሆን እንደሚችል አስረድተዋል።

✧ አማርኛው አቻ ትርጉም ሴቷን ገንዘቤ (ማሚት) ወንዱን ንዋይ (ማሞ) ብሎ ይጠራዋል።

ምንዳዬ ፦ ይህን ደግሞ ቢዘገይም ባክልበት ነው።
ለዚህ መነሻው ነዲእ / ነዲኦት የሚለው ነው መንዳት መውሰድ መሸኘት ማጀብ መከተል ማድረስ ማለት ነው፤
አንድ ሰው ነዳኢ ነው ከተባለ የሚነዳ ነጂ እረኛ ሹም ነው የሚለውን ይገልጣል። ይህን ይዘን ምንዳእ ላይ ስንደርስ መንጃ ፣ መነጃ ፣ በትር ፣ ጅራፍ መንገድ ወደሚል ትርጉም ያደርሰናል። በቁሙ ደግሞ ምንዳ የእረኛ ዋጋ ደመወዝ ዐስበ ኖላዊ (ለገበሬም ይኾናል ሲያርስ በሮች እየነዳ ነውና) ማለት ይሆናል።
አሁን ምንዳዬ ላይ ደርሰናል። (ምንዳእየ⇨ ምንዳዬ) በአማርኛው ደሞዜ ገንዘቤ ዋጋዬ በትርየ ፍኖቴ ማለት ይሆናል የፍቺው አገባብ ከላይ ነሲቡ በሚል ከተገለጠው ጋር ይወራረሳል።

ተኰላ/ተኮላ ፦ በአጠራሩ ኒኮላ (ኒቆላዎስ) እንደሚለው የውጪ ስም ይመስላል። ተኰላ ማለት ግን ቀጥታ ተወለወለ፣ ተሰነገለ ፣ ጠራ ፣ ነጠረ ጥሩ ኾነ የሚለውን ይገልጣል።

ተምትም፦ አስማማ አጣጥም አስታርቅ አግባባ (መተምተም ማጣጣም… ቁራሽ በብትን ድቁስ ተምትሞ አጥቅሶ መብላት)

መርድ ፦ በሁለት መንገድ ሊታይ ይችላል (መርዕድ፣ መርድእ) ብሎ ፤ መርዕድ ካለ መራድ መፍራትን ይዞ የሚያስፈራ የሚያስደነግጥ ባለ ግርማ ሞገስ የሚለውን ይገልጠል፣ መርድእ ካለ ደግሞ ረድእ የሚለውን መነሻው በማድረግ ተማሪ ደቀ መዝሙር የሚውን ይተካል።

አርማሕና ሐርቤ ፦ እነዚህ ከሀገራችን ነገሥታት ወገን የነበሩ ስሞች ናቸው፤ የሁለቱም መነሻ ሐርብ የሚለው ቃል ነው ጦርነት ውጊያ ሰልፍ ባለው የሚተካ ነው። ዐ(ሐ)ርበኛ የምንለው ዐማርኛው ከዚህ ወጥቷል

☞ አንዱ ንጉሥ በሙሐመድ ዘመን የነበረ ሰላማዊና ጀግና የኢትዮጵያ ንጉሥ መጠሪያ መሆኑን ታሪከ ነገሥት ይናገራል ፦ ንጉሥ አርማሕ ትርጉሙ ጦረኛ ሐርበኛ (አርበኛ) ማለት ነው።

☞ ሁለተኛው በላስታው ታሪክ ውስጥ በዛግዌ ሥርወ መንግሥት ከተነሱ 11 ነገሥታት መካከል የሚጠራና ከከበሩ አራቱ ቅዱሳን ነገሥታት (ሐርቤ ፣ ላሊበላ ፣ ነአኩቶ ለአብ እና ይትባረክ ) መካከል የሚደመር የታላቅ ሰው ስም ነው [ቅዱሱ ንጉሥ ሐርቤ (ገብረ ማርያም)] ሐርቤ ማለት ሐርብየ አርበኛዬ ጀግናዬ ማለት ነው።

ሙና /ሙናዬ ፦ ሴት እናት እህቶቻችን በዚህ መጠርያ ሲሰየሙ አልፎ አልፎ እሰማለሁ። መነሻ መጠሪያው ሙናሕ/ሙናኅ የሚል ነው፤ ትርጉሙ ማረፊያ ምዕራፍ ማለት ነው፤ ነዊኅ፣ ኖኅ የሚለው የዚህ አቻ ነው። በፍትሐት ጸሎታችን አምላካችን የሚያሳርፍ የሚያረጋጋ ብሎ ሲማጸን «መናህይ ወመናዝዝ» ይላል። በመጽሐፈ ግንዘት ሃባ ናህየ ወዕረፍተ ላዛቲ ነፍስ እንዲል።

ከዚህም ጋር በተወዳጀ ስያሜ አንዳንድ ተመሳሳይ ትርጉም ያነገቡ ስሞችም በአንድ ቤት ለእህት ለወንድም ሲሰጡም አይቻለሁ ለምሳሌ ዕሌኒ እና ሔለን ፣ ሐመልማል እና ለምለም ፣ ኂሩት እና ቸርነት ተመሳሳይ ትርጉም ያላቸው ስሞች ቢሆኑም ልዩነት ያላቸው መስለው ለተለያዩ ግለሰቦች ሲታደሉ ይታያል።

ይህን ይዘን እግረ መንገድ ጥቂት ለማለት ወደ ወል መጠሪያዎች ደግሞ እንለፍ።

አቶ ፦ ዛሬ አንድ ወጣት ወንድ እድሜው ሲገፋና ሕግ ሲገባ (ትዳር ሲይዝ) በክብር የሚጠራበት ስሙ ነው ይህ አቶ የሚለው። በቀድሞውስ ዝክረ ሊቃውንቱ እንደሚነግረን ‘የአዋቆች’ የሊቃውንቱ መጠሪያ ማዕረግ ሁሉ ነበር (ለዚህ ሊቁ አለቃ አስረስ የኔሰው አቶ አስረስ ስለመባላቸው የገለጹትን ማየት!) ለፍቺው መነሻ አተወ/አቶ ነው በፍቺው ገባ ተመለሰ መጣ ይላል፤ እትወት [አቶነት] መግባት መመለስ መምጣት ነውና (ዲያቆን በቅዳሴው ማብቂያ እትዉ በሰላም እንዲል) አቶ ማለት ባለ ሕግ ፣ ትዳር የያዘ ፣ ወደ ልቡ የተመለሰ ፣ ከሰው ቁጥር የገባ ፣ ከሚስት ከባልንጀራ አቻ ኾኖ የተካከለ ማለት ነው።

ወይዘሮ ፦ ይህም እንደቀድሞው ለሴት አንቀጽ ተቀጽላ ሆኖ ለሴት እመቤት ላገቡ የሚዛረፍ የባለትዳሮቹ የክብር መጠሪያ ነው። መርዓዊት (ሙሽሪትን) ሲያስጌጧት ሲሸልሟት ሲያንቆጠቁጧት አወየዘረ ወይዘሮ አደረገ አስወየዘረ ወይዘሮ አስደረገ ይላል። የተጌጤች የተሸለመች የተሞሸረች ናትና ወይዘሮ ትባላለት፤ ገና ያልተሞሸረችዋን ተወዛሪት ወይዘሪት ማለት በዚህ ልማድ ነው ገና የምትሞሸር ናትና።
በእርግጥ አወየዘረ ማለት ሾመ አከበረ ራስ ቢትወደድ አደረገ ማለትም ነው፤ ለሚስትነት የወደዳት ባል ያገኘችውን ሴት ሞገስና ባለሟልነት ያላት ናትና ክብርት ወይዘሮ ብሎ ይገልጣታል። (ዘረከበ ብእሲተ ኄርተ ረከበ ሞገሰ ወበረከተ)

እመጫት ፦ ይህ ደግሞ የጨቅላ እናት በክብር የምትጠራበት ስም ነው። በተረት «እመጫት ሆዷ ቅርጫት» ሲባልም እንሰማለን፤ ቃል በቃል እንፍታው ብለን ከታገልን የአደንዛዡ እጽ (የጫት) እናት ወደማለት ያወርደናል። (ለእናቴስ ላቲ ክብር) አማርኛችን ከእናቱ ግእዝ ቃላትን ሲዋስ እንደየ (አ)ከባቢው የሚለውጣቸው ሆሄያት አሉ፤ ከከባቢ ከባቢ (አካባቢ) እንኳ ቀ እና ኧ የሚተካኩበት (መኧነት፣ ባዔላ … መቀነት ባቄላ) መኖራቸውን በብዙ ምሳሌ ማስረዳት ይቻላል። በተጨማሪ ጸ/ፀ፣ ጠ እና ጨ ሲወራረሱ ይታያል።
ትልቅ ምሳሌ ለዚህ እንጥቀስማ "ጤናዳም" ሲባል የማያውቅ የለም "ጤና አዳም" በሚል ፍቺ ከገነት እጽዋትና ከአዳም ኑሮ ጋር የሚያገናኘው ጉዳይ ስለመኖሩ ማስረጃ አልተገኘለትም።

ይሁንና እንደነ ኪዳነ ወልድ ገለጻ ከሆነ ጤናዳም የሚለው " "ጼና አዳም" ባለበጎ ሽታ (ጼናሁ አዳም ሽታው መልካም) የሆነውን ቅጠል ይዞ የተሰጠ ስም መሆኑ ተጽፏል። በልሳነ ትግሪኛውም "ጨና አዳም" የሚለው የበለጠ ይህን ገላጭ ነው። በዚህ መነሻ ጸ/ፀ በጠ መተካቱን ልብ ይሏል። ጠሃይ እንዲል ፀሐይን፣ ንግሥት ጣይቱ ይላል የእምዬ ምኒሊክን እምዬ ፀሐይቱን!

ወደያዝነው ጉዳይ ስንመለስ እመጫት የሚለውን የጨ፣ የፀ እና የጠ መተካካት ከእኛ ቢያርቀው ትርጉሙን ሳንይዘው ቀረን። ፃት ፦ ማለት ጣት ማለት ነው ፤ የእጅና የእግር ቅጥይ ነው። ሕፃን ጨቅላ ፣ ርጥብ ለጋ ፣ ቀንበጥ ዐራስ ወጣት ልጅ ጻጹት/ጫጩት ሁሉ ፃት ይባላል የተክል ጫፍ የዛፍ ቅርንጫፍ ፃት ተብሎ ይጠራል ዛሬ በእኛ ጣት እምንለውን ሁሉ ማለት ነው። ታዲያ እኛም በዚሁ እመ ፃት ያለውን ነው እመጫት ያልነው፤ ትርጉሙ የጨቅላ እናት፡፡ የዶሮ እመ ጫጩት/ጻጹት የዝንጀሮ እመጫት እያሉ መጥራት በዚህ አገባብ የተለመደ ነው።