Get Mystery Box with random crypto!

ጥር ፮ የአስማት ቀን ነው! ━━✦༒ ༒✦━━ ቸር አላችሁ? እንኳን አደረሳችሁ! አስማት የሚ | ሳሙኤል ተመስጌን ወ/ሃና

ጥር ፮ የአስማት ቀን ነው!
━━✦༒ ༒✦━━

ቸር አላችሁ? እንኳን አደረሳችሁ!

አስማት የሚለውን ቃል ስንሰማ ቀድሞ ወደ አእምሯችን ዓይኖች ምትሀት የሚለው ትርጉም ድቅን ይል ይሆናል።

በእርግጥ ስያሜው ከኅቡእ መለያዎች (magic spells) እየተጠጋ አስማት (incantation) የሚባለውንም ይገልጣል፤

በእኛም ዘንድ አንድ ሰው አስማታዊ/አስማታም ነው ከተባለ ባለኅቡእ ስም ፣ አስማት ያሚደግም ፣ የሚጥፍና የሚያነግት የሚያስነግት ፣ ስም የሚጠይቅ በስም የሚያሟርት ጠንቋይ መሠሪ ኮከብ ቈጣሪ ነው ማለትም ይሆናል። (ኪዳነ ወልድ እንዳመለከቱት)

"በሸንጎ ቢረታ ከቤት ሚስቱን መታ" ሆኖብን የውጪዎችንስ «ምናምን» ለእኛ ምሥጢር ማርከሻ እንዳናውል እየተጠነቀቅን አስማት የሚባለው ስም ለሚለው አብዢ ቁጥር ሆኖ የሚያገለግል ስያሜ ነው የሚለውን ለዛሬው እንያዝ። (የአምላካችንን በእጅጉ የከበሩ ስሞች ለመግለጥ አስማተ መለኮት እንዲል)

ከዕለቱ ጋር የሚገናኘውም ይህ ነው!

ዛሬ ጌታችን ከተወለደ ሳምኒት ዕለት (ስምንተኛው ቀን) ነው! ዕለተ ግዝረት ኢየሱስ የሚለው ስም በእናቱ በኩል የወጣለት ዛሬ ነው። አንድ ወልዳ ስሙን አበዛችው እንዳለ ዘማሪው። ነቢዩ "አማኑኤል ትለዋለች ሲል መልአኩ ኢየሱስ ትዪዋለሽ ብሏታልና)
ብርሃነ ብርሃናት ሠረቀ እማርያም ድንግል
ዘይነብር ቀትረ መልእልተ ጌልጌል
ሰመየቶ አማኑኤል
ጥር ፮ የአስማት ቀን ነው መባሉም የእርሱ ስም መድኃኒትነት ለዲያቢሎስ መርዝ ማርከሻ በ፵ ቀኑም ለአረጋዊው ስምኦን መታደሻ ሆኖታል። ለእኛም «ለስምንተኛው ሺህ ጉዶች» ስምንተኛውን ቀን ከኃጢዓት ሸለፈት በንስሐ የምንገዘርበት ያድርግልን። በከበረው ስሙ መድኃኒት ይሁነንማ።

“እርሱ ሕዝቡን ከኃጢአታቸው ያድናቸዋልና ስሙን ኢየሱስ ትለዋለህ።” (ማቴ ፩፥፳፩)

በግእዙ ስም “ሰመየ፤ ስም አወጣ፣ ጠራ፣ ለየ” ከሚለው ግስ ይወጣና መጠሪያ መለያ የሚለውን ይገልጣል፡፡ በልሳነ ዐረብ ኢስም ism (اسم) በእብራይስጡም ሼም shame (שֵׁם) ከሚለው ተቀራራቢ ቃል ጋር አቻ ፍቺ ያለው ነው።

በአጠቃላይ ስም ቦታነትና አካልነት ህላዌና ሕይወት ላለው ሁሉ መገለጫ ሆኖ የሚያገለግል መጠሪያ ነው።

የስም የትመጣነትን አጉልቶ የሚገልጠው ቅዱስ መጽሐፋችን በመጀመሪያው ሰው በአዳም በኩል ለገዛ አጋሩ ቀድሞ ሴት ኋላ ሔዋን የሚለውን መጠሪያ በመሰየም ጭምር ቀዳሚ ስም አውጪ እርሱ እንደነበር ተጽፎልናል።

መላእክቱ በሁለተኛው ሱባኤ በ፮ኛው ቀን በእግዚአብሔር ታዘን ፍጥረቱን በየወገኑና በየመልኩ ወደ አዳመቅ አመጣን "ወአምጻእነ በቃለ እግዚአብሔር ኀበ አዳም …" ይላሉ።

አዳምም እኒህን ፍጥረታት በየስማቸው ጠራቸው ስማቸውም እርሱ እንዳወጣላቸው ሆነ " ወሰመዮሙ አዳም ለኵሎሙ በበ አስማቲሆሙ ወበከመ ጸውዖሙ ከማሁ ኮነ ስሞሙ፡፡" [ኩፋ ፬፥፪ ]

ቅዱስ ቀሌምንጦስም ይህን ሲያጸና እንዲህ አለ “ወሰመዮሙ ለኵሎሙ በበአስማቲሆሙ ወተአዘዙ ሎቱ ኵሉ ፍጥረት ወዓቀቡ ቃሎ፤ አዳም ለሁሉም በየስማቸው ሰየማቸው፣ ስም አወጣላቸው፤ ፍጥረት ሁሉ ለአዳም ይታዘዝና ቃሉንም ይጠብቅ ነበር” (ቀሌ ፩፥፵፪)

በዘልደት መጽሐፍም እንዲህ የሚል ይገኛል “እግዚአብሔር አምላክም የምድር አራዊትንና የሰማይ ወፎችን ሁሉ ደግሞ ከምድር ፈጠረ፤በምን ስም እንደሚጠራቸውም ያይ ዘንድ ወደ አዳም አመጣቸው፤ አዳምም ሕያው ነፍስ ላለው ሁሉ በስሙ እንደጠራው ስሙ ያው ሆነ፡፡ አዳምም ለእንስሳት ሁሉ ለሰማይ ወፎችም ሁሉ ለምድር አራዊትም ሁሉ ስም አወጣለቸው” (ዘፍ፪፥፲፱-፳)

የሰዋስው ምሁራን የስም ዓይነቶችን ከአገልግሎታቸው አንጻር ስመ ባሕርይ ፣ ስመ ተቀብዖ ፣ ስመ ግብር ፣ ስመ ተጸውኦ፣ ስመ ተውላጥ (መራሕያን) እያሉ በአምሥት ከፍለው ያጠኑታል። (በመጽሐፈ ሰዋስው መጽሔተ አእምሮ እንደተብራራው)

መጠሪያ ስም (ስመ ተጸውዖ) አስቀድሞ ፍጥረቱ ኹሉ ከፈጣሪውና ከጌታው ከአዳም እንደ ተሰየመ እንዲሁ ደግሞ ከአባት ከእናት ከጌታ ከእመቤት ከካህናት ከቤተ ክርስቲያን ተሰይሞ የሚጠራበት መገለጫው ነው። በዚህ ላይ የሹመትና የማዕረግ ስሞችም አሉ ስመ ተቀብዖ ይባላል። ይህም ከተጸውዖ ስም በኋላ በሹመት ጊዜ ከቀቢ ከሿሚ የሚሰጥ የማዕርግ ስም ነው ጳጳስ ቄስ ንጉሥ ራስ ይህን የመሰለ፡፡

ዕለቱ ካገናኘን አይቀር አንዳንድ ሀገርኛ ስሞች ትርጉማቸውን ሳናውቅ ምንጫቸውንም ሳንጠይቅ በመጠሪያነት ስንጠቀማቸው ይስተዋላል (ተሸካሚና ተጠቃሚ ቢለያይም )

በግሌ ሰዎች ስማቸውን ሲነግሩኝ "ምን ማለት ነው?" ብዬ እጠይቃለሁ ካላወቁት እንኳ ትርጉሙን በማሰስ የደረስኩበት እንደሆነ አስታውሼ እንዲያውቁት ለማድረግ እጥራለሁ።

ለዛሬው «ሀገርኛ» መጠሪያ ይዘው ትርጉሙን ግን ሳይረዱ ከሚጠሩበት አንዳንድ ግለሰቦች ያገኘሁትን ስም በደረስኩበት ደረጃ በትርጉም ላመላክት እና ላጋራችሁ ወደድኩ።

#በጥቂቱ
☞ ነሲቡ፣ አባተ ፣ ዘበነ ፣ ማሞ ፣ ምንዳዬ፣ ተኮላ፣ ተምትም ፣ መርድ፣ አርማሕ፣ ሐርቤ ሙናዬ…
☞ አቶ ፣ ወይዘሮ ፣ እመጫት፣ ነፍሰጡር … የሚባሉቱ መጠርያዎች መነሻ ግንዳቸው የትርጉም ዐውዳቸው ምን ይሆን?

ነሲቡ፦ በዚህ ስም የሚጠሩ ጥቂት ግለሰቦች በግል አውቃለሁ። መነሻው ነሲብ ነው ይህም ግምት ድርሻ፣ እድል ፈንታው ማለት ነው፤ ዐንሰበ ይላል ገመተ ሲል። ከዚህ ስም ጀርባ አንድ አስደናቂ ክስተት ይነገራል፦
ወላጆች ልጅ ወልደው በተደጋጋሚ በሞት ሲነጠቁ "የሰጠ ቢነሳ የለበት ወቀሳ" ይሉና «እባክህ ይህንንስ ተውልኝ ለእኔ ድርሻ እድል ፈንታዬ ይሁነኝ» ብለው ብፅዐት ገብተው ይወልዱና ስሙን ነሲቡ ብለው ይሰይሙታል እንዳሉትም ይሆንላቸዋል፤ በተለይ በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል ግደይ እየተባሉ ከተጠሩ ሰዎች ጀርባ ይህ ሐቅ ይገኛል።

✧ ነሲቡ በአማርኛው ድርሻዬ ፣ በትግሪኛው ግደይ የሚለውን የሚተካ ነው።

ዘበነ ፦ ይህ እንኳን የበርካቶች መጠሪያ የሆነና ለብዙዎችም ከነ ትርጉሙ እንግዳ እንደማይሆን ባውቅም አንዱ ወንድሜ «መጠሪያው ጸያፍ ነው» ብሎ ሲነቅፍ ስላየሁ ለእርማት አካትቼዋለሁ። ዘበነ የዘባን መነሻ ግንድ ነው ፤ ዘባን ደግሞ ጀርባ ነው የደረትና የሆድ ጓሮ ጎረቤት ነው ፤ ጀርባ ደግሞ በዘይቤ መከታ ደጀን የሚለውን ያመለክታል። በዚህ መነሻ ዘበነ መከታ ሆነ፣ ጋሻ ሆነ፣ ደጀን ደራሽ ሆነ ማለት ነው፤

✧ በአማርኛው ደጀኔ (ደጀንየ) የሚለውን ይተካል።

አባተ፦ ይህም በማኅበረሰባችን ውስጥ የተለመደ ስም ይመስለኛል። አጠራሩ አብሐተ የሚል ሲሆን ከመነሻው ብሒት ማለት መሰልጠን፣ መሾም፣ ከበላይ መሆን የሚለውን ይይዛል። አባተ ማለት አሰለጠነ ሾመ (ባለስልጣን ፣ ሥዩም አደረገ) ማለት ነው።

✧ በአማርኛው አባተ ስዩም ፣ ተሾመ ፣ በላይ በሚለው ተተክቶ ሊነገር ይችላል።
በመባህተ መኑ ትገብር ዘንተ
አብሀነ በመንፈስ ንኪድ ኵሎ ኃይሎ ለጸላኢ