Get Mystery Box with random crypto!

አንድ የታሪክ ተመራማሪ በመቅደላ ጦርነት የተሰረቁት የአፄ ቴዎድሮስ አልባሳት የት እንዳሉ ለማወቅ | TIKVAH-MAGAZINE

አንድ የታሪክ ተመራማሪ በመቅደላ ጦርነት የተሰረቁት የአፄ ቴዎድሮስ አልባሳት የት እንዳሉ ለማወቅ እየጣሩ ነው ተባለ

በእንግሊዝ አንድ የታሪክ ተመራማሪ ከ156 ዓመታት በፊት የተሰረቁት የዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ አልባሳት የት እንዳሉ ለማወቅ እየጣሩ መሆኑን ቢቢሲ ዘግቧል።

ዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ በእንግሊዝ ወረራ ወቅት እጅ አልሰጥም ብለው መቅደላ ላይ የራሳቸውን ሽጉጥ ጠጥተው ከሞቱ በኋላ ለብሰውት የነበረው የክብር ካባ እና የአንገት ልብስ ከአስክሬናቸው ላይ ተገፍፎ ተወስዷል።

አልባሳቱ ወደ እንግሊዝ ከተወሰዱ በኋላም በስታሊይብሪጅ፣ ስታምፎርድ ፓርክ ሙዚየም ውስጥ ተቀምጠው እንደነበር ሲገለፅ ሙዚየሙ በ1950ዎቹ ከፈረሰ በኋላ ግን እነዚህ ጥንታዊ ቅርሶች የት እንዳሉ አይታወቅም ተብሏል።

በጉዳዩ ላይ መጽሐፍ የጻፉት ሔቨንስ የተባሉት የታሪክ ተመራማሪ እንደሚሉት በመቅደላ ጦርነት ወቅት የተወሰዱ ቅርሶች ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በአገሪቷ ውስጥ ይገኛሉ። ከሐር የተሠራው የንጉሡ ትንሽ የአንገት ልብስም ስታሊይብሪጅ ውስጥ በሚገኘው ሰታምፎርድ ፓርክ ሙዚየም ውስጥ ተቀምጦ ነበር።

ሙዚየሙ በ1950ዎቹ ከፈረሰ በኋላ የንጉሡ የአንገት ልብስ ወይም የካባው ክፍል በሆነ ሰው ቤት ውስጥ እንደሚገኝ ሔቨንስ እምነት እንዳላቸው እና የተረፉት ሌሎች ቅርሶችም ወደ ሌሎች የአካባቢው ሙዚየሞች መሰራጨታቸውን ገልፀዋል።

ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የታሪክ ምሁሩ ለታሜሳይድ የአካባቢ ጥናት ተቋም፣ ለመዘክሮች እና ለማንቸስተር ሙዚየም ጥያቄ ሲያቀርቡ ቆይተዋል። የከተማዋ ነዋሪዎች የጥንታዊ ዕቃዎች ማስቀመጫዎቻቸውን እንዲፈትሹ እያሳሰቡም ነው ተብሏል።

@TikvahethMagazine