Get Mystery Box with random crypto!

የ7 ዓመት ዕድሜ ያለው ታዳጊ በጅብ ጉዳት ከደረሰበት በኃላ ሕይወቱ አለፈ። ሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ግ | TIKVAH-MAGAZINE

የ7 ዓመት ዕድሜ ያለው ታዳጊ በጅብ ጉዳት ከደረሰበት በኃላ ሕይወቱ አለፈ።

ሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ግቢ ውስጥ ትናንት ሚያዝያ 19/2015 ዓ.ም ከቀኑ 11:00 ሰዓት አካባቢ በዩኒቨርሲቲው የሚገኘውን ራሬ የእርሻ ምርምር ቦታ በማቋረጥ ላይ ያለ የ7 ዓመት ታዳጊ በጅብ በደረሰበት ጥቃት ህይወቱ ማለፉ ተገልጿል።

ታዳጊው፥ ከጅቡ ለማምለጥ ሙከራ ቢያደርግም ማምለጥ ባለመቻሉ ሆዱ እና ጭንቅላቱ ላይ ከባድ ጉዳት ደርሶበታል። ድርጊቱን ከርቀት የተመለከቱ የዩኒቨርሲቲው የጥበቃ አባላት ጅቡ ጉዳት ያደረሰበትን ልጅ ወደ ሚኖርበት ጉድጓድ ይዞት በመሄድ ላይ ሳለ ደርሰው ማስጣል ችለው ነበር።

ጥበቃዎቹ፥ ልጁን በሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ከፍተኛ ጤና ጣቢያ አድርሰውት የነበር ቢሆንም የደረሰበት ጉዳት ከፍተኛ ስለነበር የተሻለ ሕክምና እንዲያገኝ ሀረር ወደሚገኘው የሕይወት ፋና ስፔሻላይዝድ አጠቃላይ ሪፈራል ሆስፒታል ተወስዶ ሕይወቱን ለማትረፍ የህክምና ሲደረግለት ቆይቶ ህይወቱን ማትረፍ ሳይቻል ቀርቷል።

በሆስፒታሉ፥ ከታዳጊው የፈሰሰውን ደም ለመተካት ደም በመስጠት ሕይወቱን ለማትረፍ ርብርብ ቢደረግም ጅቡ በታዳጊው ላይ ያደረሰው ጉዳት ከባድ በመሆኑ ከምሽቱ 3፡30 አካባቢ የታዳጊው ሕይወት ማለፉን በሐረማያ ዩኒቨርሲቲ የሕይወት ፋና ስፔሻላይዝድ አጠቃላይ ሪፈራል ሆስፒታል የድንገተኛና አደጋዎች ህክምና ማዕከል ተረኛ የህክምና ባለሙያዎች ተናግረዋል፡፡

የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ የጥበቃና ደህንነት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ኮማንደር አባድር ዩያ ከዚህ ቀደም በዩኒቨርሲቲው ግቢ ውስጥ እንደዚህ አይነት መሰል አደጋ እንዳልደረሰ ኮማንደር አባድር ዩያ አስረድተዋል።

የታዳጊ ህፃን ኢፋ አባድር አደም የቀብር ስነስርዓት ዛሬ ሚያዚያ 20/2015 ዓ.ም ረፋድ ላይ ሐረማያ ባቴ ቀበሌ ተፈፅሟል ሲል ለሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብ ሬዲዮ ኤፍ ኤም 91.5 ዘግቧል።

@tikvahethmagazine