Get Mystery Box with random crypto!

ለወላጆች እና ተማሪዎች ... በአዲስ አበባ ከተማ ካሉ የመንግስት ትምህርት ቤቶች ጋር በተያያዘ | TIKVAH-MAGAZINE

ለወላጆች እና ተማሪዎች ...

በአዲስ አበባ ከተማ ካሉ የመንግስት ትምህርት ቤቶች ጋር በተያያዘ ባለፈው ዓመት የነበረው ሁኔታ ዘንድሮ በተለይም ከሰሞኑን ተባብሶ ነበር።

ይኸውም ችግር በተለያዩ ወገኖች እና በመንግስት አካላት የተለያየ ማባራሪያ እየተሰጠበት ነው።

አንዳንድ ነዋሪዎች ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ፣ በሀገር ውስጥ እና በውጭ ሀገር ያሉ ግለሰቦች፣ የማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ የሚፅፉ ግለሰቦች ፤ የከተማው አስተዳደር ምንም በማያውቁ ተማሪዎች ላይ ያለፍላጎታቸው ጫና በማድረግ የኦሮሚያ ክልል መዝሙር እንዲዘምሩ፣ ባንዲራም እንዲሰቀል እና  የበላይነትን ለማስፈን እየሰራ ነው ፤ በአዲስ አበባ የሁሉም መቀመጫ ከሆነች ለምን የሌላው ቋንቋ አይሰጥም ? የሌላው ባንዲራ አይሰቀልም ? መንግስት በተለይም የኦሮሚያ ብልፅግና ሆን ብሎ አቅዶ የሚሰራው ስራ ዛሬ በግልፅ ካልተቃወምን ነገ መዘዙ አደገኛ ነው የሚል ሀሳብ ይሰነዝራሉ። ለሚፈጠረው ቀውስ ሁሉ መንግስትን ተጠያቂ በማድረግም ከድርጊቱ እንዲታቀብ ተማሪዎችን እንዲዘምሩ እና የክልል ባንዲራ ያለፍላጎት እንዲሰቀል ማስገደድ ማቆም አለበት ይላሉ።

በሌላ በኩል ፤ የከተማው አስተዳደር ፣ አስተዳደሩንም የሚደግፉ አንዳንድ አካላት ይኸው በአ/አ ትምህርት ቤቶች በአፋን ኦሮሞ የማስተማር ስራ አዲስ እንዳልሆነ ፣ በኢህአዴግ ጊዜ እንደጀመረ ፣ በተወሰኑ ትምህርት ቤቶች ተጀምሮ ፍላጎት በመጨመሩ መስፋፋቱ ፣ ባንዲራው እና መዝሙሩም የአ/አ ከተማ አስተዳደር የራሱ የአፋን ኦሮሞ ማስተማሪያ ስርዓተ ትምህርት ስለሌለው ከኦሮሚያ ክልል እንደተዋሰና እሱኑ እያስፈፀመ እንደሆነ፣ አሁን ለመፅደቅ በሂደት ላይ ባለ ስርዓተ ትምህርት ውስጥ ሌሎችም ቋንቋዎች እንዲሰጡ እየተሰራ መሆኑን ይገልጻሉ። ይህ እየታወቀ፣ በቀጣይም ሌሎች ቋንቋዎችን ፣ ተማሪዎች በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው እንዲማሩ ለማድረግ ስራ እየተሰራ እንዳለ እየታወቀ ሆን ብሎ አጀንዳ በመፍጠር ከተማውን ለመበጥበጥ፣ በግጭት ገንዘብ ለማግኘት የሚፈልጉ አካላት ተማሪዎችን እያነሳሱ ፣ በብሄር እየከፋፈሉ ፣ እንደሆነ በዚህም ጉዳት እየደረሰ እንደሚገኝ ይገልጻሉ።

ይህ ጉዳይ በቀጥታ የሚመለከታችሁ የተማሪ ወላጆች እና ተማሪዎች (ስለጉዳዩ በቂ ግንዛቤ ያላችሁ) ሁኔታውን እንዴት ነው እየተከታተላችሁ ያላችሁት ? እናተ በጉዳዩ ላይ ቀጥታ ባለቤት እንደመሆናችሁ  ምንድነው የምታውቁትና የተፈጠረው ?

የመንግስት አካላትን ፤ ከዛ በተቃራኒ ደግሞ የመንግስት ተቃዋሚ ኃይሎችን ሃሳብ በስፋት ተሰምቷል ሚዲያዎችንም ተቆጣጥሯል ወላጆች ምን ይላሉ ? ተማሪዎችስ ?

እባክዎትን እዚህ መልዕክት ማስቀመጫ ላይ ፤ የጉዳዩ ቀጥተኛ ባለቤት ካልሆናችሁ (የተማሪ ወላጅ ወይም ተማሪ) መልዕክት ባትልኩ ስንል በትህትና እንጠይቃለን።

@tikvahethiopia