Get Mystery Box with random crypto!

አውሎ ነፋስ የቀላቀለ ከባድ ዝናብ ከ150 በላይ ቤቶች ላይ ጉዳት አደረሰ። በምዕራብ ጎንደር ዞን | TIKVAH-MAGAZINE

አውሎ ነፋስ የቀላቀለ ከባድ ዝናብ ከ150 በላይ ቤቶች ላይ ጉዳት አደረሰ።

በምዕራብ ጎንደር ዞን መተማ ዮሐንስ ከተማ አስተዳደር ሰኔ 1/2014 ዓ.ም ከቀኑ 11:00 ገደማ በተከሰተ አውሎ ነፋስ የቀላቀለ ከባድ ዝናብ ከ150 በላይ ቤቶች ላይ ጉዳት ማድረሱን የመተማ ዮሐንስ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጽሕፈት ቤት ኅላፊ አቶ ሲሳይ ጌትሽ ገልጸዋል።

እንደ ኅላፊው ገለጻ በተከሰተው የዝናብ አደጋ የመንግሥት አገልግሎት ሠጭ ተቋማትን ጨምሮ 105 የመኖሪያ ቤቶች ሙሉ በሙሉ የተጎዱ ሲሆን 45 ቤቶች ደግሞ በከፊል ጉዳት ደርሶባቸዋል። በሰውና በእንስሳት ላይ ጉዳት እንዳልደረሰ ኅላፊው ተናግረዋል።

በመኖሪያ ቤቶች በመንግሥት እና መንግሥታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች ላይ የደረሰው ውድመት በጥሬ ገንዘብ ሲገመት ከ40 ሚሊዮን ብር በላይ እንደሆነ ነው የተጠቆመው። ጉዳት ከደረሰባቸው የመንግሥት ተቋማት መካከል የመተማ ዮሐንስ አጠቃላይ አንደኛ ደረጃ ትምሕርት ቤት አንዱ ነው።

ስምንት የመማሪያ ክፍሎች ሙሉ በሙሉ መውደማቸውንና ስምንት ደግሞ በከፊል ጉዳት እንደደረሰባቸው የትምሕርት ቤቱ ርዕሰ መምህር አቶ አበበ እንዳለው ገልጸዋል።

የመብራት ፖሎች በመውደቃቸው እና የተዘረጉ ገመዶች በመበጣጠሳቸው የመብራት አገልግሎት ተቋርጧል። የወደሙ የመንግሥት ተቋማትን መልሶ ለመገንባት ከመንግሥት ባሻገር ባለሀብቶችና ረጅ ድርጅቶች ድጋፍ እንዲያደርጉም አቶ ሲሳይ ጥሪ አቅርበዋል። (አሚኮ)

@tikvahethmagazine @tikvahmagbot