Get Mystery Box with random crypto!

#የዛሬ_1 (ግንቦት 22/2014) የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ የጊዜ ቀ | TIKVAH-MAGAZINE

#የዛሬ_1 (ግንቦት 22/2014)

የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ የጊዜ ቀጠሮ ችሎት ፤ " ሁከት እና ብጥብጥ በማነሳሳት " ወንጀል ተጠርጥሮ በእስር ላይ በሚገኘው በጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ላይ የ10 ቀናት የምርመራ ጊዜ ፈቅዷል። የጊዜ ቀጠሮ ችሎቱ የምርምራ ጊዜውን የፈቀደው የተከሳሽ ጠበቃ ያቀረቡትን መከራከሪያ እና የዋስትና ጥያቄ ውድቅ በማድረግ ነው።

የ "ፊንፊኔ ኢንተግሬትድ ብሮድካስቲንግ " የቴሌቪዥን ጣቢያ ጋዜጠኛ ሰቦንቱ አህመድ ዛሬ ረፋዱን ከቢሾፍቱ ከተማ ከሚገኝ ፖሊስ ጣቢያ የተለቀቀች ሲሆን ጋዜጠኛዋ ከእስር ከተለቀቀች በኋላ በስልክ እንዳነጋገሯት የገለጹት የቴሌቪዥን ጣቢያው ዋና ዳይሬክተር ፖሊስ " ስንፈልግሽ ትመጫለሽ " በሚል መፈታቷን እንደነገረቻቸው አስታውቀዋል።

ባሳለፍነው ቅዳሜ በፀጥታ ሃይሎች የተያዘችው መዓዛ መሃመድ ዛሬ በፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ችሎት ቀርባለች። ፖሊስ በመዓዛ መሃመድ ላይ " ሁከትና ብጥብጥ ማስነሳት " የሚል ክስ አቅርቦባታል። የጋዜጠኛዋ ጠበቆች ጋዜጠኛዋ ሰራች የተባለው ወንጀል ተፈፅሞ ቢሆን እንኳን ጉዳዩ ሊታይ የሚገባው በመገናኛ ብዙሀን አዋጅ ነው ፤ በእስር እንድትቆይ ህጉ አይፈቅድም ሲሉ ተከራክረዋል። ፍርድ ቤቱ የግራ ቀኙን ክርክር አዳምጦ የ7 ቀናት የምርመራ ጊዜ ፈቅዷል።

የመብቶች ዴሞክራሲ ዕድገት ማዕከል (ካርድ) እና 7 የተለያዩ ማህበራት በጋራ ባወጡት አጭር መግለጫ በጋዜጠኞች ላይ የዘፈቀደ እስር እየተፈፀመ መሆኑን በመግለፅ ድርጊቱን እንደሚቃወሙ ገልፀዋል።

የአብክመ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዛሬ ግንቦት 22/2014 ዓ/ም በዋለው ችሎት የብርጋዴል ጀኔራል ተፈራ ማሞን ጉዳይ ተመልክቷል። የመርማሪ ቡድኑ ምርመራዬን ስላልጨረስኩ የተለያዩ ማስረጃዎችን ከባንክ፣ ከብሔራዊ መረጃና ደህንነት፣ ከኢንሳ እና ከሌሎች ተቋማት የምንሰበስባቸው መረጃዎች ስላሉ የ14 ቀናት ተጨማሪ የጊዜ ቀጠሮ እንዲሰጠው ጠይቋል። ፍርድ ቤቱ የግራ ቀኙን ክርክር ሰምቶ የጊዜ ቀጠሮ መስጠቱን ስላመነበት የምርመራ ቡድኑ ከጠየቀው የ14 ቀን ውስጥ 4 ቀን ቀንሶ 10 ቀናት ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ በመፍቀድ ለሰኔ 2/2014 ዓ/ም ቀጠሮ ሰጥቷል።

#ቲክቫህኢትዮጵያ

@tikvahethmagazine @tikvahmagbot