Get Mystery Box with random crypto!

የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር የመኖሪያ ቤት መሥሪያ ቦታ አስረከበ። የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደ | TIKVAH-MAGAZINE

የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር የመኖሪያ ቤት መሥሪያ ቦታ አስረከበ።

የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ከተማና መሠረተ ልማት መምሪያ በመሸንቲ ሳይት ተደራጅተው ለቆዩ 196 ማኅበራት የመኖሪያ ቤት መሥሪያ ቦታ አስረክቧል።

በመሸንቲ ሳይት 3 ሺህ 806 አባላትን ያቀፉ 185 ማኅበራት፣ 261 አባላትን ያቀፉ 11 የአርሶ አደር ልጆች ማኅበራት በድምሩ 196 ማኅበራት፣ 4 ሺህ 67 አባላት የመኖሪያ ቤት መሥሪያ ቦታ ተረክበዋል።

የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ከተማና መሠረተ ልማት መምሪያ ሀላፊ ኃይለእየሱስ ፀጋዬ አዲስ ከተማን የመመስረት ተግባር እየተሠራ በመሆኑ ውኃ፣ መብራት፣ መንገድና ሌሎች የመሠረተ ልማት ግንባታዎች እንደሚከናወኑ ተናግረዋል። መንግሥት ለሚያከናውናቸው ሥራዎች ሁሉ ማኅበራትም የበኩላቸውን ድጋፍ እዲያደርጉ ጠይቀዋል።

ለማኅበራት ቦታ መስጠት ብቻ ሳይሆን ከተማ አሥተዳደሩ አስፈላጊውን ማሽነሪና ሌሎች ድጋፎችን እንደሚያደርግ ኀላፊው ቃል ገብተዋል። በተለይ ለግንባታ አስቸጋሪ አካባቢ የገጠማቸው ማኅበራት ከተማ አሥተዳደሩ ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።

በተመሳሳይ ሁኔታ በዘንዘልማ ሳይት ተደራጅተው የመኖሪያ ቤት መሥሪያ ቦታን ለሚጠባበቁ ማኅበራት በበጀት ዓመቱ ምላሽ ለመስጠት እየሠራ መሆኑን ሀላፊው ተናግረዋል።

ለመኖሪያ ቤት መሥሪያ ግንባታ ቦታቸውን የሚለቁ አርሶ አደሮች ልጆቻቸው በማኅበር በመደራጀት ቦታ እንዲሰጣቸው መደረጉን አቶ ኃይለእየሱስ ተናግረዋል ሲል የዘገበው አሚኮ ነው።

@tikvahethmagazine