Get Mystery Box with random crypto!

#MadingoAfework የተወዳጁ ድምጻዊ ማዲንጎ አፈወርቅ የቀብር ሥነ ስርዓት የፊታችን ሐሙስ | TIKVAH ETHIOPIA

#MadingoAfework

የተወዳጁ ድምጻዊ ማዲንጎ አፈወርቅ የቀብር ሥነ ስርዓት የፊታችን ሐሙስ እንደሚፈጸም ተገለጸ

ዕረቡ መስከረም 18 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) የተወዳጁ ድምጻዊ ማዲንጎ አፈወርቅ የቀብር ሥነ ስርዓት የፊታችን ሐሙስ መስከረም 19 ቀን 2015 አራት ኪሎ በሚገኘው ቅድስተ ሥላሴ ካቴድራል እንደሚፈጸም ተገልጿል።

ለዚሁ የቀብር ሥነ ስርዓት የተቋቋመው ኮሚቴ ቃል አቀባይ እና የቴሌቪዥን ፕሮግራም አዘጋጅ ሰይፉ ፋንታሁን ለአሜሪካ ድምፅ ሬድዮ (ቪ ኦ ኤ) እንደገለጸው ከሆነ፤ የድምጻዊው የቀብር ሥነ ስርዓት የፊታችን ሐሙስ በቅድስተ ሥላሴ ካቴድራል የሚፈጸም ይሆናል። ከቀብር ሥነ ስርዓቱ አስቀድሞም የሽኝት ፕሮግራም እንደሚካሄድ የተገለጸ ሲሆን፤ ይህን በተመለከተም ዝርዝሩን ኮሚቴው በቀጣይ እንደሚያሳውቅ ተጠቅሷል።

ማዲንጎ አፈወርቅ ትናንት ማክሰኞ መስከረም 17 ቀን 2015 ጠዋት 1፡30 አካባቢ፤ ለሐኪሙ ስልክ በመደወል ወደ ክሊኒክ እንደሄደና ለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ በሚገኝ አንድ የግል ክሊኒክ የህመም ማስታገሻዎችን እና ሌሎች መድኃኒቶችን ወስዶ እንደነበር የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ያስታወቀ ሲሆን፤ ማዲንጎ ከረፋዱ 3፡00 ሰዓት አካባቢ ህይወቱ ማለፉን ገልጿል።

የድምጻዊው አስክሬን ሕይወቱ ካለፈበት የግል ክሊኒክ ወደ አቤት ሆስፒታል ተወስዶ ምርመራ እየተካሄደ መሆኑን የገለጸው ፖሊስ በቀረበለት አቤቱታ መሠረት የድምጻዊውን ሞት መንስኤ ለማወቅ የአስክሬን ምርመራ ውጤቱን እየተጠባበቀ እንደሚገኝ አስታውቋል።

በደብረታቦር ከተማ የተወለደውና ከ 1980ዎቹ አጋማሽ አንስቶ የኢትዮጵያን የሙዚቃ ጉዞ ከተቀላቀሉ ድምፃውያን መካከል በቀዳሚኒት የሚጠቀሰው ማዲንጎ አፈወርቅ፤ በ1987 “ስያሜ አጣሁላት” በተሰኘው ቀዳሚ የአልበም ሥራው ከሙዚቃ አፍቃሪያን የተዋወቀ ሲሆን፤ በ1990ዎቹ ‹‹አይደረግም›› እንዲሁም ከቅርብ ዓመታት በፊት ‹‹ስወድላት›› የተሰኙ ተወዳጅ የሙዚቃ አልበሞችን ወደ አድማጮች አድርሷል።

በተጨማሪም በበርካታ ነጠላ ዜማዎቹ በመስራት በሙዚቃ አፍቃሪዎች ዘንድ ተወዳጅነትን ያተረፈው ድምጻዊ ማዲንጎ፤ አራተኛ አልበሙን ለአድማጮች ለማድረስ በመስራት ላይ እንደነበርም አዲስ ማለዳ ለማወቅ ችላለች።