Get Mystery Box with random crypto!

#ቲንክአቢሲኒያ_የቡናቁርስ_መረጃዎች 1፤አምባሳደር ታዬ አጽቀስላሴ ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት | Think Abyssinia

#ቲንክአቢሲኒያ_የቡናቁርስ_መረጃዎች

1፤አምባሳደር ታዬ አጽቀስላሴ ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ጋር ተወያዩ

በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ አምባሳደር ታዬ አጽቀስላሴ ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ክብርት ሀና ሰርዋ ቴቴ ጋር ውጤታማ ውይይት ማድረጋቸውን ተናግረዋል።
አምባሳደር ታዬ በቀጣናው ወቅታዊ የፖለቲካ ጉዳዮች እንዲሁም በኢትዮጵያ የሰብዓዊ እርዳታ ተደራሽ እንዲሆን በተወሰደው የተኩስ ማቆም ውሳኔ እና ወቅታዊ ሁኔታዎች ፤በቀጣናው ባሉ ድንበር ዘለል የፀጥታ ፈተናዎች እና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ውጤታማ ውይይት ማድረጋቸውን በቲዊተር ገጻቸዉ አስፍረዋል።


2፤የሁለቱ አገራት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የበለጠ እንዲሻሻል እንደሚሰሩ አምባሳደር ስለሺ በቀለ ገለጹ።

በአሜሪካ የኢፌዴሪ ልዩ መልዕክተኛ እና ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ሆነው የተሾሙት አምባሳደር ስለሺ በቀለ ከዋሽንግተን ዲሲ ኤምባሲ ዲፕሎማቶችና ሰራተኞች ጋር ትውውቅ አድርገዋል።
የሚሲዮኑ ባልደረቦች ዋና ትኩረት ዘመናትን ያስቆጠረው የሁለቱ አገራት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የበለጠ እንዲሻሻል ሁሉን አቀፍ ጥረት ማድረግ እንደሚያሰፊልግ ተገልጸዋል።
በዳያስፖራ ተሳትፎ፣ ህዝብ ለህዝብ፣ የቴክኖሎጂ ሽግግር፣ ንግድና ኢንቨስትመንት፣ ገጽታ ግንባታ፣ ቱሪዝምና በሌሎች ዘርፎች ያለውን ትብብር ማጎልበት እንደሚገባም ገልጸዋል።

3፤ሁለቱ ኮሚሽኖች ሥራቸውን ለአዲሱ የምክክር ኮሚሽን አስረከቡ።

የአስተዳደር ወሰን እና የማንነት ጉዳዮች እንዲሁም ሀገራዊ የዕርቀ-ሰላም ኮሚሽኖች የሥራ ኃላፊነታቸውንና ሰነዶቻቸውን የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች እና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች አፈ-ጉባዔዎች በተገኙበት ለአዲሱ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን አስረክበዋል።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ አቶ ታገሰ ጫፎ፣ ኮሚሽኖቹ ብዙ ፈተናዎችን መሻገራቸውን ገልጸው፣ በቂ ክትትልና ድጋፍ ቢደረግላቸው ካከናወኗቸው ተግባራት በላይ መሥራት ይችሉ እንደነበር አስታውሰዋል።
በመሆኑም እነርሱ ካለፉበት ሁኔታ ትምህርት በመቅሰም፣ ለአሁኑ የምክክር ኮሚሽን አስፈላጊው ክትትልና ድጋፍ መደረግ እንዳለበት አፈ-ጉባዔው ገልጸዋል።


4፤የሲዳማ ክልል ምክር ቤት መደበኛ ጉባኤውን ማካሄድ ጀምሯል።

የሲዳማ ክልል ምክር ቤት 6 ዙር አንደኛ የስራ ዘመን ሁለተኛ መደበኛ ጉባኤውን ዛሬ በሀዋሳ ከተማ ማካሄድ ጀምሯል፡፡ ለሁለት ቀናት በሚካሄደው ጉባኤ ቃለ ጉባኤ ማፅደቅ፣ ተጨማሪ በጀት ማፅደቅና አዳዲስ ሹመቶችን ያከናወናል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
እንዲሁም የክልሉ የዘጠኝ ወር የስራ አፈፃፀም ሪፖርት ቀርቦ ውይይት የሚደረግበት ሲሆን በታዩ ጠንካራና ደካማ ጎኖች ላይ ውይይት ከተደረገ በኋላ ቀጣይ አቅጣጫ ይቀመጣል ነው የተባለው፡፡

5፤አልሸባብ 170 የአፍሪካ ህብረት ወታደሮችን መግደሉን አስታወቀ።

የአልሸባብ ታጣቂዎች በማዕከላዊ ሶማሊያ የብሩንዲ ወታደሮች በሚገኙበት የአፍሪካ ህብረት ጦር ሰፈር ላይ ኢላማ በማድረግ በሰነዘሩት ጥቃት ከ170 በላይ የብሩንዲ ወታደሮችን መግደላቸውን አስታውቋል። ከሶማሊያ ዋና ከተማ ሞቃዲሾ በሰሜን ምስራቅ 130 ኪ.ሜ ርቀት ላይ በሚገኘው የጦር ሰፈር ከባድ ውጊያ እንደነበር የዜና ኤጀንሲዎች የዓይን እማኞችን ጠቅሰዉ ዘግበዋል።
የአፍሪካ ህብረት ጦር እየተባለ የሚጠራው እና ከተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት ማለትም ከኡጋንዳ፣ ቡሩንዲ፣ ጅቡቲ፣ ኬንያ እና ኢትዮጵያ የተውጣጡ ወታደሮችን ያቀፈ ስብስብ ነው።የሞቃዲሾን መንግስት ከአልሸባብ ታጣቂዎች ጋር የሚያደርገውን ውጊያ የአፍሪካ ህብረት ጦር እየደገፈ ሲሆን በአልሻባብ ታጣቂዎች ከዚህ ቀደምም የጥቃት ኢላማ እንደነበር ይታወሳል፡፡


6፤ የሮማው ጳጳስ አባ ፍራሴስ ከፕሬዝዳንት ፑቲን ጋር ለመገናኘት ያቀረቡት ጥያቄ እስከሁን ምላሽ እንዳላገኘ ተገለፀ።

ከሩሲያ ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር በሞስኮ ተገናኝቶ ለመምከር ጥያቄ ማቅረባቸውን የሮማ ጳጳስ እና የዓለም ካቶሊካውያን አባት ተናግረዋል።
ከጣሊያኑ ኮሬ ዴላ ሴራ ጋዜጣ ጋር ቆይታ ያደረጉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ወደ ሞስኮው መምጣት እፈልጋለሁ ሲሉ ለፑቲን መልዕክት መላካቸውን ተናግረዋል። ሆኖም እስካሁን ለጥያቄው ምላሽ አላገኘንም ብለዋል፤ አሁንም እየሞከሩ መሆናቸውን ጠቁመዋም።

7፤ሊቨርፑል የፍፃሜ ተፋላሚ መሆኑን አረጋግጧል።

የአውሮፓ ሻምፒየንስ ሊግ የግማሽ ፍፃሜ የመልስ ጨዋታ በስታዲዮ ዴ ላ ሴራሚካ ቀጥሎ ሲካሄድ ሊቨርፑል 3-2 ሲያሸንፍ በድምር ውጤት ቪያሪያልን 5 - 2 በሆነ ውጤት በማሸነፍ የፍፃሜ ተፋላሚ መሆኑን አረጋግጧል ።
የሊቨርፑልን የማሸነፊያ ግቦች ፋቢኒሆ ፣ ሊዊስ ዲያዝ እና ሳዲዮ ማኔ አስቆጥረዋል ።
ሊቨርፑል የማንችስተር ሲቲ እና ሪያል ማድሪድን አሸናፊ በአውሮፓ ሻምፒየንስ ሊግ የፍፃሜ ጨዋታ ይገጥማል ።
የአውሮፓ ሻምፒየንስ ሊግ የፍፃሜ ጨዋታ ግንቦት 20 በፈረንሳይ ርዕሰ መዲና ፓሪስ የሚካሄድ ይሆናል ።


• @ThinkAbyssinia •