Get Mystery Box with random crypto!

⚀ ክፍል አራት ⚀ የጅማ መድሃኒያለም ሰፈር በነጭ ጋቢ ተደርቶ የሚቆዝም ሽማግ | የኔው ታሪክ 8315

⚀ ክፍል አራት ⚀



የጅማ መድሃኒያለም ሰፈር በነጭ ጋቢ ተደርቶ የሚቆዝም ሽማግሌ ይመስል የጉም ጢስ ተከናንቦ ፀሀይ መውጣት፤ወገግ ማለትን ዳባ ልበስ ያለ ይመስላል።
ከፍሌም ጋር ምንም ሳናወራ ረጅም መንገድ ተጓዝን በጅማ መድሃኒያያለም የመቃብር ስፍራ በኩል ባለው ወደ ዲፖ ቀበሌ ሶስት መታጠፊያ ቅያስ ጋር ስንደርስ ፍሌም ቆም አለች "በዚህ ነኝ "አለችኝ መታጠፊያውን በግራ እጇ እየጠቆመችኝ በገሚሱ መሬቱን በገሚሱ እኔን ገርመም አድርጋ እያየችኝ።
"እሺ ቻዎ " አልኳት እና ወደ ኃላ ተመልሼ ጥቂት እርምጃዎችን እንደተራመድኩ "ግሩም" አለችኝ
ዞር ስል ድብስብስ ባለ ጎህ በሚመስል የንጋት ወሰን ላይ የፈነጠቀች ፈዘዝ ያለች የፀሀይ ብርሃን የፈካባት ትንሽዬ ከተማ የመሰለች ደስታን በክብ ፊቷ ላይ አስተዋልኩ ፤ ለዘብ ባለ ድምፀት "ወዬ "አልኳት
"አመሰግናለሁ " ብላኝ ይበልጥ ፈገግ ብላ፤ በአጭሩ ፈገግታዋን መግባኝ ምላሼን ሳትጠብቅ ፍሌም ነጎደች ....ሄደች .......ራቀች.....ታጠፈች.....ጠፋች።
ቀኑ መሽቶ ነጋ አባቴ ባመጣሁት ውጤት ደስ ብሎት አደረ። ቤታችን ውስጥ ያለነው ሶስት ልጆች ነን።
ትንሹ ወንድሜ ቅዱስ፣ታናሽ እህቴ ትርሃስ እና እኔ ነን።የቤቱ ታላቅ እኔ መሆኔ ነው። አባቴ በአስራ አምስት ቀናት ውስጥ ለሽልማት ላውቶፕ ኮምፒውተር እንደሚሸልመኝ ቃል ገባልኝ።ደስም አለኝ!!
ጠዋት ላይ ፍሌም መጥታ ከእኛ ጋር ስትጫወት ዋለች።ፍሌምን እኔ በአንድ አመት በትምህርት እበልጣታለሁ። የምትኖረው ድሬዳዋ ነበር።ያውም ከዚራ ውስጥ እዚህ ጂማ መድሃኒያለም ሰፈር አጎት አላት። የህንፃ ተቋራጭ ሀላፊ ነው።
እኔ ከምምጣቷ ይልቅ ስትሄድ መሸኘቱ ነው የልቤን የሚያደርሰው። ልክ አመሻሽ ላይ ልሸኛት ተዘጋጅቼ እየጠበቅኳት እያለሁ ትርሃስ "ፍሌሜ ነይ እንሂድ በዛውም ካርድ ገዝቼ ልመለስ!" አለቻት። ይሄኔ ትርሃስን ማነቅ ዳዳኝ፣ ተቃጠልኩኝ። ተሰናብቻት ክፍሌ ገብቼ የአልጋው ጫፍ ላይ ተቀምጬ በሃሳብ እብከነከን ገባሁ። በዚህ ፍጥነት ለዚህች ልጅ ያለኝ ምልከታ ግራ አጋባኝ።
አይኗን፣ ከንፈሯን ይበልጥ ደግሞ ዲምፕሏን እያሰብኩ እንቅልፍ ይዞኝ ጭልጥ አለ። ይሄ ከሆነ ከሁለት ሳምንት በኃላ የሆነ ቀን አመሻሽ ላይ ሀሳብ ጭንቅንቅ ሲያደርገኝ አየር ለመቀበል ብዬ ኮት ደርቤ ኤርፎኔን ከስልኬ ጋር ይዤ ወጣሁኝ። በመድሃኒአለም ቤተክርስቲያኑ አድርጌ ሽቅብ ወደ መንደራ ትምህርት ቤት አቅጣጫ አቀናሁ።
በስልኬ በሻሸመኔ እና በሀዋሳ ከተማ መካከል ጥቁር ውኃ ተብላ በምትጠራበት ቦታ የበቀለውን ተወዳጁን የሙዚቃ ንጉስ የድምፃዊ ታምራት ደስታን ውብ ትዝታ እየሰማሁ ወደ መናፈሻው ተቃረብኩ።.....


ክፍል አምስት ይቀጥላል.....

▃▅▆█ 웃 ፍሌም 웃 █▆▅▃

ቶሎቶሎ እንዲለቀቅ ሼር teztash
https://t.me/teztash
https://t.me/teztash

@rediy21