የቀጠለ ምስኪኒቷ እናቴ! በሞላ ጎዳና ባልጠበበ ድንበር ፥ በዘር ገመድ ታግዳ ነጻ ነኝ ትላለች መንጋነት ያሰረው ፥ ባሪያ ትውልድ ወልዳ፡፡ የጀግንነት እብሪት ልባችንን ደፍኖት ፥ ማሰብ እየከዳን እንዴት ነው ነጻነት እንዳበደ ፈረስ ፥ ስሜት እየነዳን፡፡ ገድሎ የመንገስ ጥማት ጩኀት ላገነነ ፥ አመጽ ላጀገነው ለዚህ ምስኪን ትውልድ በጅምላ እየነዱት በመንጋ እያሰበ ፥ ነጻነት እንዴት ነው? ነጻነት ምርጫ ነው! አምሮ ቢደላደል ጥፋት ያመነነው ፥ የመንጋዎች መንገድ እንቅፋቱን ወዶ ለኖሩለት እውነት ፥ ለብቻ መራመድ! ነጻነት ማመን ነው ቀን ወዶ ቢያጀግን ፥ ቀን ጠልቶ ቢከዳም ቢቆሽሹም ቢደምቁም እራስን መቀበል ራስን መምሰል ነው ፥ የነጻነት ገዳም! ነጻነት ማሰብ ነው በአንድነት መለምለም የኔነትን አረም ፥ ከህሊና ማጥፋት ዘር ሆኖ ከማነስ ሀገር ሆኖ ማበብ ፥ ዓለም ሆኖ መስፋት። ንገሯት ለሀገሬ ... በጀግኖቿ ትግል ድንበር ባታስደፍር ፥ ከእጀ ገዥ ብትወጣ ነጻ ነኝ እንዳትል በገዛ ልጆቿ ፥ በእጅ አዙር ተሸጣ ፡፡ ስሩን ካልሸመነው በመዋሃድ ጥለት ፥ በማስተዋል ሸማ ታሪክ አናደምቅም በጭብጨባ ድግስ ፥ በሆይ ሆይታ ዜማ፡፡ ምን ብናቀነቅን በየሰልፉ ሜዳ ፥ ወኔ ብንደግስም በፈረሰ አይምሮ በደቀቀ አንድነት ፥ ሀገር አናድስም፡፡ በጭፍን ከመሮጥ አስቦ ማዝገም ነው ፥ የመራመድ ውሉ ሁሉም እንቅፋቶች እስኪጥሉን ድረስ ፥ ምርኩዝ ይመስላሉ፡፡ በድፍን ግልብ እሚያጋድል ህዝብ የመሆን ፥ መንጋ አይንዳን በማሰብ ስር እንፈወስ ፥ በሰውነት ፀበል እንዳን፡፡ ከእግዜር ልንወዳጅ ለምህረቱ ጥላ ፥ እምባ ብንደግስም ልብን ሳይመልሱ ለንስሃ መሮጥ ፥ ከጽድቅ አያደርስም፡፡ ውብ ነገን እናውርስ ትላንትን አክመን ፥ በይቅርታ ፀበል ትውልድ ይጨርሳል ያረገዝነው እምባ ፥ የቋጠርነው በቀል ከመስጠት አንጉደል ከቀማኞች ገደል ፥ ተረግጠን ብንጣል ካሸከሙን በቀል ምናወርሰው ፍቅር ፥ ሀገር ይለውጣል፡፡ ከዕድሏ ጣሪያ ላይ ዘር የቀዳደው ፥ ሽንቁሯ ቢበዛም ያ ከንቱ ፎካሪ ባፈጀ ቀረርቶ ፥ ሺህ ጉራ ቢነዛም ሚሊዮን ዘር ቢሸጥ ፥ አንድ ሀገር አይገዛም፡፡ ኢትዮጵያዊነት ነው የትርታችን ልክ ፥ የነፍሳችን ግጥም መልስ ቤት በራቀው በከረመ ፀሎት ፥ ሰርክ ብታንጋጥም አጎንብሳ ድሃ ባፀናችው ጉልበት ፥ ብትረጋገጥም ነፍሷን አደህይታ ባሻረችው ቁስል ፥ ብትገሸለጥም ሀገር ሆና ገዝፋ በየ ጎጣጎጡ ፥ አትርመጠመጥም፡፡ የዘመን እውነት ነን ከደግነት ሰማይ ፥ በጥበብ የኖርን ትዕግስትም ልክ አለው ፈርተን እንዳይመስለው ፥ ስላቀረቀርን፡፡ ማተብ አስሮን እንጂ ተጣልተን እንዳንቀር ፥ በክፍፍል ገደል ከሀገር ክብር በልጦ ፥ ሞት ብርቃችን አይደል፡፡ ንገሩት ለዛ ሰው ከዓለም ጫፍ እስከ ጫፍ ኃይል እንደ ተራራ ፥ ገዝፎ ቢከመርም ክንዱን አፈርጥሞ እልፍ የሰገደለት ፥ ጀግና ቢሰድርም ዓለም የሞተበት የጠላት ማርከሻ ፥ ጦር ቢደረድርም በአንድ ዓይናችን ሰላም በኢትዮጵያችን ክብር፥ አንደራደርም !!! ┈┈┈┈•◦●◉❖◉●••┈┈ ┈ ሕሊና ደሳለኝ ╰══•••┈ ┈ ┈•◦●◉❖◉●••┈┈ ┈ ፳፻፲፪ ዓ.ም 131 viewsፍቅር-ኤል, 18:35