#የማጀት_ሥር_ወንጌል ሙያተኛ ሀገሬ ከማጥገብ ጎደለ በረከት እራቀው ፥ የገበታሽ ለዛ ተሻምቶ ለመጉረስ ከበላነው ይልቅ ፥ የደፋነው በዛ፡፡ ሙያሽ ባያስደፍር ፥ አጀብ ቢሰኙበት ማዕዱ ቢሙላላ ፥ ዓይነቱ ቢያምርበት አበዛዙ አይደለም አበላሉ ላይ ነው ፥ የገበታሽ ውበት፡፡ እየተማመንን! የፉክክር ቅሚያ ፥ በርሃብ እየናጥን ከደፋነው ጠግቦ ፥ ውሻችን በለጠን፡፡ ከምርት አላነስን ጎተራችን ሙሉ ጀግና አራሽ ፥ መች አጥተን? ማሰብ የጎደለው አያያዛችን ነው ፥ ገደል የከተተን፡፡ ይልቅ ግዴለሽም! ከምግባር ምጣድ ላይ ሳንበስል አንጋግተሸ ፥ ከማዕድ አትምሪን ገበታሽ እንዲያምር ከእግዜር የሚያስታርቅ ፥ ፍቅር አስተምሪን። ገበታ ዕድሜ ነው ፥ ባለ ማሰብ መክነን ሳንፀነስ ጃጀን ፥ ሳንጣድ አረርን ከዘመን ገበታ ከፊደል አቅድመን ፥ ዘር እየቆጠርን ገበታ ሀቅ ነው በክፋት ሊጥ ጋግረው ፥ ያሻገቱት እውነት በሆዳም እስክስታ ረግጠው ያፈኑት ፥ የምስኪናም ጩኸት እስከ ልጠይቅሽ... በጥም ደዌ ደቆ የረሃብ ጠኔ ደፍቶት ፥ እልፍ ትውልድ ያልፋል ቢራ ለመጥመቂያ ሚበተን ገብስ ግን ፥ ከሀገር መች ይጠፋል፡፡ ከሆድ በማይሻገር የማጀት ቤት ዕውቀት ፥ አጥብበሽ አትለኪን እስቲ መኖር ይግባን ከማስተዋል መቅደስ ፥ ሰው መሆን ስበኪን። ዘመን ካልገበረው ከችጋር ተራራ ፥ ከሲኦል ዳር ኑሮ እንዴት ነው መሻገር ከመርፌ ቀዳዳ ፥ በጠበበ አይምሮ። ከምስኪን ዘመን ላይ የማይኖሩበትን ፥ ዕድሜ መበዳደር ለአንዲት ማምሻ ደስታ በአያት እስትንፋስ ላይ ፥ ቁማር መደራደር ያሳፍራል አይደል? እያደጉ ማነስ ፥ እያነሱ መዝቀጥ አጎንብሶ ያፀናን የድሃ እናት ጉልበት ፥ በጭካኔ መርገጥ ያሳምማል አይደል? መንገስ ከሚያባላስ መጥገብ ከሚያቃቅር ፥ ማግኘት ከሚያጎለን ማጣት ውሎ ይግባ ባርነት ይሰንብት ፥ ድህነት ይግደለን፡፡ ከረፈደ ፀፀት ደረት እየደቁ ፥ ከእግዜር ቢዋቀሱ ትርጉሙ ምንድነው ? ሲኖር ተቃቅሮ ፥ ሲሞት መላቀሱ። በእናታችን አድባር ፥ በፍቅሯ ይሁንብን መድመቅ ካጋደለን ፥ ቆሽሸን ይመርብን በመጠማት ሲቃ እስትንፋስ እስኪያንቃት ፥ ነፍሳችን ትርበትበት ብቻህን ከመጥገብ አብሮ መራብህ ነው ፥ ሰው የመሆን ውበት፡፡ በድፍን ግልብ እሚያጋድል ህዝብ የመሆን መንጋ ፥ አይንዳን በማሰብ ስር እንፈወስ ፥ በሰውነት ፀበል እንዳን። አየህ! ሰው ስትሆን ከመንጋነት ሚያግድ እረኛ አያሻህም ፥ ከህሊናህ በላይ ስታስብ መሪ ነህ በብስለት ከፍታ ፥ በማስተዋል ሰማይ፡፡ አየህ! ሰው ስትሆን የጎጥ አረም ነቅለህ በአንድነት መስክ ላይ ፥ ፍቅር ትዘራለህ፣ በወረወሩብህ የጥላቻ ድንጋይ ትውልድ የሚያፋቅር ፥ ድልድይ ታበጃለህ፡፡ አየህ! ሰው ስትሆን ዝምታህ ኃያል ነው ጀግና የሚያንበረክክ ከፈሪ ቀረርቶ ፥ ከባዶ ሰው ጩኀት ሀገር ላምስ ከሚል በመንደር አጀንዳ ፥ በአሽኮለሌ ተረት፡፡ አየህ! ሰው ስትሆን ነጻ ነህ እያሉህ መታሰር ያምርሃል መቀመቅ መበስበስ የኖርክለት እውነት ፥ ሀገር እስኪፈታ በሀቁ እስኪመዘን ስለ በርባን ክብር የቆሸሸው ፍቅር ፥ የታሰረው ጌታ ከድል ታሪክ ሰማይ ከሥልጣኔ ዳር ፥ ከጥበብ ከፍታ እንሻገራለን ህዝብነትን ትተን ፥ ሰው የሆንን ለታ፡፡ በትረ ጥበበ ቢካን ዓለም ሊያንቀጠቅጥ ፥ ድል ሥልጣን ቢሰጠው ጀግና መሪ አይደለም ብርቱ ተመሪ ነው ፥ ሀገር ሚለውጠው፡፡ አስተውል ወዳጄ ጠልተን ላንጣላ ችለን ላንጋደል ፥ ነደን ላንፋጀው የኛው ትርምስ ነው በልቶ ለሚያባላ ፥ ጠላት ሚበጀው፡፡ ስጋና ደም እንጂ የአንድነታችን ውል ፥ የፍቅራችን ቀለም ያሰመርነው ክልል የታጠርንበት ዘር ፥ ቋንቋችን አይደለም፡፡ ከመዋሃድ መቅደስ ትውልድ እናስተምር ፥ ዘመን ይመርቀን ፍቅራችን ምን ጎድሎት ፥ ደማችን ያስታርቀን፡፡ በልጆቿ አጥንት በደም ኪዳን ምለን ፥ የገባንላት ቃል ከጩኀት ያለፈ ዘመን የሚሻገር ፥ ተግባር ይጠይቃል፡፡ በአንድ ሃሳብ ተጋምደን በድል ድር እናብር ውድቀታችን ያንቃን ፥ ሠርተን እናሳምን ሆነን ድል እንንሳ ፥ የአፍ ጀግንነት ይብቃን፡፡ 98 viewsፍቅር-ኤል, 18:34