Get Mystery Box with random crypto!

ያልወለደቻቸውን ሦስት ህፃናትን ይዛ የተገኘች ግለሰብን ጉዳይ እያጣራ መሆኑን ፖሊስ አስታወቀ፡፡ ፖ | Skyline media

ያልወለደቻቸውን ሦስት ህፃናትን ይዛ የተገኘች ግለሰብን ጉዳይ እያጣራ መሆኑን ፖሊስ አስታወቀ፡፡ ፖሊስ የህፃናቱን ወላጆች ወይም አሳዳጊዎች እያፈላለገ ነው።

ሰኔ 22 ቀን 2015 ከቀኑ 8 ሰዓት በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ወረዳ 7 ትልቁ አውቶቡስ ተራ አንዲት ግለሰብ ሦስት ህፃናትን ይዛ የተመለከቱ ፖሊስ ለፀጥታ ስራ ያደራጃቸው አካላት ለፖሊስ ጥቆማ ይሰጣሉ።

የአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ ጥቆማውን መነሻ በማድረግ ባደረገው ክትትል እና ባሰባሰብው መረጃ ግለሰቧ ሦስቱን ህፃናት ከቡታጅራ ይዛቸው እንደመጣች በማረጋገጡ ፖሊስ መምሪያው ተጠርጣሪዋን በቁጥጥር ስር አውሎ ምርመራ መጀመሩን አስታውቋል፡፡

ግለሰቧ ህፃናቱን እንዳሳደገቻቸው ብትገልፅም አጠራጣሪ ጉዳዮች በመኖሩ ፖሊስ የህፃናቱን ወላጆች ወይም አሳዳጊዎች እያፈላለገ ነው፡፡ ህፃናቱ በአሁኑ ወቅት ክበበ ፀሐይ ህፃናት ማሳደጊያ የሚገኙ መሆኑን ፖሊስ አስታውቆ መረጃውን በማድረስ የዜግነታቸውን ለተወጡ የፀጥታ አጋዥ ኃይሎች መምሪያ ምስጋናውን አቅርቧል።

የህፃናቱ ወላጅ ወይም አሳዳጊ ነኝ የሚል ግሰለብ አዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ ማመልከት እንደሚችል እና ስለ ህፃናቱ ተጨማሪ መረጃ ያለው ማንኛውም ግለሰብ ለመምሪያው መረጃ በመስጠት እንዲተባበር የአዲስ አበባ ፖሊስ መልእክቱን አስተላልፏል፡፡