Get Mystery Box with random crypto!

“ሠላም ከሌለ ኮርማም ቢታረድ አይጣፍጥም” - ተፈናቃዮች የገና በዓል በኦሮሚያ ክልል ግጭት፣ ስጋ | Sheger Press️️

“ሠላም ከሌለ ኮርማም ቢታረድ አይጣፍጥም” - ተፈናቃዮች

የገና በዓል በኦሮሚያ ክልል ግጭት፣ ስጋት እና ዋጋ ንረት ተጭኖታል!

በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ወለጋ ዞን ኪረሙ ወረዳ የተፈናቀሉ አንድ አርሶ አደር አስተያየት ሰጪ እንዳሉት “በአሉ ቀዝቃዛ ነው፡፡ የበዓልም ድባብ የለም፡፡ በዚ ላይ መንገዶች በብዛት ስለሚዘጋጉ ሽንኩርት የለም፤ ሌላውም ሸቀጥ ስለማይገባ በዓሉን አስቸጋሪ አድርጎብናል” በማለት የጸጥታው ስጋት በህይወታቸው ሁሉ ፈታኝ እንደሆነባቸው አስረድተዋል፡፡

እንደ ሰማይ ርቆ የናረው ኑሮ እንኳን በዓል ማክበር ነገን የሚያስናፍቅ ብርቱ ፈተና ደቅኗልም በማለት ያሉበትን ሁኔታ አስረድተዋል፡፡ “እርሻ ካቆምን ሶስት ዓመት ነው፡፡ ምንም የሚላስ የሚቀመስ የለንም፡፡ ከሌላ ቦታ የሚመጣው ሸቀጥማ በታም እየተወደደ ነው” ብለዋል፡፡

አሰርተያየት ሰጪው ከምንም በላይ የራቀንና የናፈቀን ያሉትንም ሲያስረዱ “ከሁሉም በላይ እኛ የምንጓጓለት እና የሚናፍቀን ሰላም ነው” ብለዋል፡፡ያለ ሰላም የሚከበር በዓልም ሆነ ደስታ ባዶ ነው ሲሉም ሃሳባቸውን አከሉ፡፡

በግጭት የተፈናቀሉ በምሥራቅ ወለጋ ዞን ኪረሙ ወረዳ የሚገኙ ነዋሪ “ሠላም ከሌለ ኮርማም ቢታረድ አይጣፍጥም” ሲሉም ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።

በቅርቡ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ዘረጋሁ ባለው የአስተዳደር መዋቅር ከፍተኛ አለመረጋጋት በተፈጠረበት ምስራቅ ቦረና እና ጉጂ ዞን አዋሳኝ ወረዳ በሆነው ጎሮዶላ የሚኖሩት አስተያየት ሰጪ ጸጥታውና በዓሉን በማስመልከት ሃሳባቸውን ካጋሩን ናቸው፡፡ ዱሬቲ ባነታ የተባሉት እኚህ አስተያየት ሰጪ የጸጥታው ይዞታ በዓሉን ከማደብዘዝ አልፎ ህይወትን ፈታኝ አድርጎብናልም በማለት ሃሳባቸውን አጋርተውናል፡፡መከላከያ ሠራዊት እና የኦሮሚያ ጸጥታ አስከባሪዎች ራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ብሎ ከሚጠራው ታጣቂ የገቡበት ግጭት እስካሁን መፍትሔ አላገኘም።

“በዚህ በዓል በኛ ዘንድ የሚከወን የበኣል ዝግጅት እና መንፈሱ የለም፡፡ እኔ አሁን የክርስትና እምነት ተከታይ ነኝ፡፡ ግን ባለው የጸጥታ ችግር ምንም የበዓል ስሜትም አይሰማኝም፡፡ መንግስት በሰላም እየኖርን እያለን ነው ድንገት ያላሰብነውን መዋቅር ዘረጋሁ በሚል ሰላማችን የጠፋው፡፡ይህን ተከትሎ በተፈጠረው የህዝብ ቅሬታ ሰላማችን በብዙ ተፈትኗል፡፡ እናም እኛ ጋ ምንም የበዓል ስሜት የለም አሁን፡፡ አሁን ባለንበት ሁኔታ በዓሉን ማክበርም አንችልም” በማለት ነው አስተያየታቸውን ያጋሩን፡፡

---ዘገባው የዶቼ ቬሌ ነው----

@sheger_press
@sheger_press