Get Mystery Box with random crypto!

የከበሬታ ነገር! በአገልግሎት ምክንያት ያገኘኋት አንዲት የባለቤተስኪያን ሚስት ጋር እናወራለን፡፡ | ሰንፔር ሚዲያ Sapphire Media

የከበሬታ ነገር!

በአገልግሎት ምክንያት ያገኘኋት አንዲት የባለቤተስኪያን ሚስት ጋር እናወራለን፡፡ ግንኙነታችን ገራም እና ደኅነኛ ስለነበር፣ በጥሩ የወዳጅት መንፈስ እናወራለን፡፡ በእኔ በኩል የመቀራረባችን ምክንያት እንደው አንዳንድ ወጣ ወጣ ያሉ ነገሮችን በመቀራረብ መግራት ይቻል እንደሁ ከሚል የዋሕነት ነበር፡፡

ልጅቱ አብዝታ አገልጋዮች ከበሬታ ይገባቸዋል የሚል ሙግት ታነሳለች፡፡ ከበሬታውም በልዩ ልዩ መንገድ መገለጥ አለበት ባይ ነች፡፡ ለምሳሌ የተመረጠው እና የተሻለው ነገር ሁሉ ለአገልጋዮች ይገባል፤ የተሻለ መኪና መንዳት፣ በተሻለ ቤት መኖር፣ የተሻለ መብላት፣ መልበስ...
ይሄ ሁሉ መሆኑ የከፋ ባልሆነ፤ ነገር ግን ይህ ሁሉ የሚሆነው በሕዝብ ጫንቃ መሆኑ ነው አሳዛኙ ትራጀዲ፡፡ ይህን መሳዮቹ አገልጋዮች ግባቸው ይኸው ስለሆነ ይህንን ለማሳካት ሁሉን ነገር ከዚህ አንጻር ይቃኙታል፡፡ ስብከቱ፣ መዝሙሩ፣ መዋቅሩ ሁሉ ከዚህ አንጻር ይገነባል፡፡

የምእመናን ስኬትም ይሁን ውድቀት ለ“አገልጋዮቹ” ካለ ከበሬታ ጋር እንደሚያያዝ አድምተው ይለፍፋሉ፡፡ ምእመናን ወጥተው የሚገቡት በእነሱ ጥላ ከለላነት እንደሆነ አድርገው ያሳምናሉ፤ ቡራኬያቸው የምእመናን ወጥቶ መግቢያ ቀለብ እንደሆነ በየምእመኖቻቸው ልብ ውስጥ አጽንተዋል፡፡

ራሳቸውን በየተከታዮቻቸው ልብ ውስጥ አግዝፈው፣ ዙፋናቸውን ዘርግተዋል፡፡ “ከመረቅሁሁ” የሚል ማበራቻ ብቻ ሳይሆን፣ “ከረገምሁህ” የሚል ማስፈራሪያም አላቸው፡፡ ምእመናን መጋቢው፣ ነቢዩ ወይም ሐዋርያው እንዳይረግመው /ቃል እንዳያወጣበት ፀጥ እና ዝግ ብሎ ይኖራል (በ“አገልጋዩ” ፊት) እግዚአብሔርን በቅጡ አያውቀውም፤ ካወቀውም አገልጋይ ተብዬው በሳለለት ልክ እንጂ የመጽሐፉን እግዚአብሔር አያውቀውም፡፡ በክርስቶስ ነጻ እንደወጣ ሰው ሳይኾን፣ ልክ በአንድ ዓይነት ባዕድ አምልኮ እንደተተበተበ ሰው ዓይነት ድንብርብሩ እየወጣ ይኖራል፡፡ የእርሱ እግዚአብሔር ሁልጊዜ በእርሱ “አገልጋይ” በኩል ብቻ የሚፈስ ነው፡፡ አገልጋይ ተብዬዎቹም ምእመናቸው ከዚህ እንቅልፉ እንዲነቃ አይፈልጉም፡፡ ቅምጥል ኑሯቸውን ባንቀላፉ ምእመናን ላይ መስርተዋል፡፡

የቸርቻቸውን ዙሪያ በገዛ ፎቷቸው ያጥራሉ፤ ቢሮው እና መድረኮቻቸው ሳይቀር በተንቆጠቆጡ ምስሎቻቸው ይሞላሉ፡፡ አንዳንዶቹ ሚስት እና ልጆቻቸውን ሳይቀር ቸርች ባሉት ይዞታቸው ላይ ይሰቅላሉ፡፡ አንዳንዶቹም ምስሎቻቸውን አትመው በየዋሌቱ እንዲያዝ ያድላሉ፡፡ በዚህም ያለ ልክ ተንሰራፍተው፣ የጌታን ጌትነት ተጋፍተው በየሰዎቻቸው ላይ ይነግሣሉ፡፡

በዚህም ያን ያነገቡትን የቅንጦት ኑሮ ይኖራሉ፡፡ “ምርጥ ምርጡን ለሕፃናት!” እንደተባለው ዓይነት በምርጥ ምርጡ ይምነሸነሻሉ፡፡ ልዕልናቸውን ያለ ልክ ከፍ አድርገው “መጡ መጡ፤ ገቡ ገቡ” ይባልላቸዋል፡፡ በማንኛውም መንገድ ልዕለ ሰብ እንደሆኑ ያውጃሉ፡፡ ተራ በሚሉት ምእመን ላይ ጢባ ጢቤ ይጫወታሉ፡፡

መቸም መከባበር ክርስቲያናዊ እሴታችን ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያዊነት ትርፉታችንም ነው፡፡ እርስ በርስ ለመከባበርም ደግሞ የቃለ እግዚአብሔር መመሪያ አለን፡፡ ቢሆንም አገልጋዮች በተለየ መንገድ ይደግደግላቸው የሚል መመሪያ ግን ጨርሶውኑ የለንም፡፡

መሪ መምህራችን ጌታ ኢየሱስ አብዝቶ ካስተማራቸው ነገሮች መካከል ስለ ዝቅታ እና ትሕትና ያስተማረውን የሚያህል ያለ አይመስለኝም፡፡ ለተወሰኑ ጊዜያት በእኔ እበልጥ እና በፉክክር መንፈስ ይንገላቱ የነበሩትን ደቀመዛሙርቱን ደጋግሞ ገስጿል፡፡ ማገልግል በራሱ የታችኛውን ስፍራ መምረጥ ነው፡፡ ጌታችን ስለ ራሱ እንኳን ሲናገር “የሰው ልጅ ሊያገለግል፣ ነፍሱንም ስለ ብዙዎች ቤዛ ሊሰጥ እንጂ እንዲያገለግሉት አልመጣም” ብሏል፡፡ በዚህም አገልጋይነት ባርነት መሆኑን አጽንቷል፡፡

ከዚህም ሲያልፍ መምህር እና ጌታ የሆነው እርሱ በእውነተኛ መዋረድ እና ዝቅታ ወገቡን አሸርጦ የደቀ መዛሙርቱን እግር አጥቧል፡፡ ይህም የተወሰኑ ኦኬዥኖች እየጠበቅን ለማስመሰል ድራማ እንድንሠራ ሳይሆን፤ አገልጋይነት የሁልጊዜ የሕይወት ሥርዓታችን እንዲሆን የተሰጠ ትምህርት ነው፡፡

ይህንኑ ፈለግ የተከተሉትም ደቀመዛሙርት ይህንኑ ቅኝት ጠብቀው ነበር ሲያገለግሉ የነበሩት፡፡ አገልግሎታቸውን የገዛ ፍላጎታቸው መሙያ ሲያደርጉ ለአፍታም እንኳ አናይም፡፡ በማንኛውም መንገድ ራሳቸውንም አላሻሻጡም፡፡ በገዛ ቃላቸውም “ክርስቶስ ኢየሱስ ጌታ እንደሆነ እንጂ ራሳችንን አንሰብክም!” ብለው መስክረዋል፡፡ በስማቸው የተቋቋመ ቡድንንም አምርረው ኮንነዋል፡፡ አለፍ ብሎም የተለየ ከበሬታ በተዘጋጀላቸው ወቅትም በመንቀጥቀጥ ልብሳቸውን ቀደዋል፡፡
ግባቸው አንድ እና አንድ ክርስቶስ ኢየሱስ በአገልግሎታቸው እንዲገለጥ እና የሁሉን ሕይወት እንዲወርስ ብቻ ነበር፡፡ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ይህ አገልግሎት የሚጠይቀውን ዋጋ በደስታ ከፈሉ እንጂ፣ ማንንም ዋጋ አላስከፈሉም፤ ሰማይ ሙሉ ዋጋ ይዞ እንደሚጠብቃቸው ግን እርግጠኞች ነበሩ፡፡ በአገልግሎታቸውም በአንዳች ስንኳ ማሰናከያ አልሰጡም ነበር፡፡

ከበሬታን ግብ ያደረገ አገልግሎት ጨርሶውኑ ከጌታ አይደለም፡፡ የእኛ ክብር የእግዚአብሔር አንድያ ልጅ የከበረ ‘ለታ ብቻ ነው፡፡ በተለያየ መንገድ ራስን ማሻሻጥ በሚመስል መልኩ እርሱን ጋርዳችሁ የደመቃችሁ ሆይ ወዮላችሁ፡፡ ምስሉን እያደበዘዛችሁ፣ ምስላችሁን በየሰዉ ልብ ለማተም የምትታትሩ ሆይ ወዮላችሁ፡፡ እራሳችሁን እያዋደዳችሁ ዙፋናችሁን ከእግዚአብሔር ከዋክብት በላይ ልትገነቡ ያማራችሁ ሆይ ወዮላችሁ፡፡ የጌታ ቤት ባላችሁት ቸርቻችሁ ላይ ደማቅ ምስላችሁን ሰቅላችሁ ራሳችሁን ያነገሣችሁ ሆይ ወዮላችሁ፡፡
ቀን ሳይጨለም ለልባችሁ ሰው መሆናችሁን ንገሩት፤ ከፍ ብላችሁ በመፋነን ፋንታ የዝቅታን አገልግሎት ምረጡ፡፡ በጌታ ዘንድ ራሱን ከፍ ከፍ ሚያደርግ ሁሉ ይዋረዳል፤ ራሱንም የሚያዋርድ ከፍ ይላል፡፡
ጆሮ ያለው ይስማ!!

ማገናዘቢያ፡ ማቴ 20÷20-28፣ ሉቃ 14÷11፣ ዮሐ 13÷12-15፣ 2 ቆሮ 4÷5፣ 1 ጴጥ 5÷6

መጋቢ ስንታየሁ በቀለ