Get Mystery Box with random crypto!

መነጠል በድጥ ጎዳና ላይ ፤ እግሬ ይራመዳል ታጥቦ ጭቃነትን ፤ ልቤ ይላመዳል ያገኘውን ለመዳሰስ | ሰንፔር ሚዲያ Sapphire Media

መነጠል

በድጥ ጎዳና ላይ ፤ እግሬ ይራመዳል
ታጥቦ ጭቃነትን ፤ ልቤ ይላመዳል
ያገኘውን ለመዳሰስ ፤ እጄ ይፈጥናል
የሞት ፍሬን ለመቅመስ ፤ ምላሴ ይጎመጃል

ሀሳቤን በሙሉ ፤ ከምድሩ ላይ ጥዬ
ከሞት ተጣብቄአለሁ ፤ ከግንዱ ተነጥዬ

በተነሳው ወጀብ ፤ ላለመወድቅ ብጥርም
እግሬ በድጥ ላይ ነውና ፤ መሰበሬ አይቀርም።
ዕድፍ የለብኝም ፤ ብትልም ምላሴ
በታጥቦ ጭቃነት ፤ ቆሽሿል ልብሴ
ለአምላክ መሸነፌን ላሳይ ፤ እጆቼን ባነሳም
በግብዝነት እሾህ ፤ መዳፎቼ ተወግተው - ተጨማልቄአለሁ በደም

‹‹ካንደበቴ እውነት›› ፤ ከአፌ ፅድቅ ርቆ
ከሞትኹ ሰነበትኹኝ ፤ አጥንቴ ደርቆ
በዚህ ኹሉ ውድቀት ውስጥ ፤ ነፍሴ ብታልፍም
በንስሃ ለመታጠብ ፤ እንባን አላፈስም

ምክንያቱም
የእውነት ቃል ቀሎብኝ ፤ በስጋዊነት ደምቄኣለሁ
በርኩሰት ካባ ፤ በዓለም ነግሻለሁ

አንዳንድ ጊዜ
በሞኞች መንደር
በቂሎች ሰፈር
ውርደትን በክብር መለወጥ ፤ ከፅድቅ ይቆጠራል
የሞት ፍሬን ማፍራት ፤ በብዙ ያስከብራል።

ቢሆንም ቢሆንም
ይሄንን እውነት ልክደው አልሻም
ሀሳቤን በሙሉ ፤ ከምድሩ ላይ ጥዬ
ከሞት ተጣብቄአለሁ ፤ ከግንዱ ተነጥዬ፡፡
/////

ቢቶ