Get Mystery Box with random crypto!

ለአገልጋዩ ወይስ ለእግዚአብሔር? አንዳንድ ጊዜ፣ አገልጋዮች የእግዚአብሔርን ቤት ሥርዓት ሲያበላሹ | ሰንፔር ሚዲያ Sapphire Media

ለአገልጋዩ ወይስ ለእግዚአብሔር?

አንዳንድ ጊዜ፣ አገልጋዮች የእግዚአብሔርን ቤት ሥርዓት ሲያበላሹ፣ ውግንናችን ለማን እንደሆነ ይገለጣል።

በዘሌዋውያን 10 የተጻፈ አንድ አስገራሚ ታሪክ አለ፡፡ ለመቅደስ አገልግሎት የተለዩት የአሮን ልጆች ናዳብና አብዩድ፣ በእግዚአብሔር መሠዊያ ላይ እርሱ ያላዘዘውን እንግዳ እሳት አነደዱ፡፡ እግዚአብሔር ወዲያው ቀሰፋቸው፡፡ ይህ በሚሆንበት ጊዜ አባታቸው አሮንና ሌሎች ወንድሞቻቸው በማደሪያው ድንኳን ውስጥ አገልግሎት ላይ ነበሩ፡፡ ይህን በገዛ ቤተሰባቸው ላይ የወረደ አስደንጋጭ መቅሰፍት ሲመለከቱ፣ እዬዬያቸው ለማቅለጥ ተነሱ:: ይህን ጊዜ ሙሴ በመሐል ገባ፡፡ “ማልቀሱን እንዳታስቡት!” አላቸው፡፡ “እንዳትሞቱ፣ በሕዝቡም ላይ ቊጣ እንዳይመጣ…እንዳታለቅሱ!” (ዘሌ. 10፡6)፡፡

አሮንና በሕይወት የተረፉት ልጆቹ የገቡበት አጣብቂኝ አንድ ነው፡- ባንድ በኩል፣ በመቅደስ ለሚያገለግሉት ለእግዚአብሔር ቁጣና ፍትሕ መወገን ይጠበቅባቸዋል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የተቀሰፉት የሥጋ ዘመዶቻቸው ስለሆኑ ጥልቅ ሐዘንና የልብ ስብራት ገጥሟቸዋል፡፡ ስለ ወንድሞቻቸው አምርረው ማልቀስ፣ ልብሳቸውን መቅደድና ጸጉራቸውን መንጨት ፈልገዋል፡፡ ነገር ግን ይህን እንዳያደርጉ ተከለከሉ፡፡ ከድንኳኑ ወጥተው እንዲቀብሯቸው እንኳን አልተፈቀደላቸውም፡፡: ሙሉ በሙሉ ለእግዚአብሔር ቅድስና እንዲወግኑ ተጠየቁ፡፡ (የቱንም ያህል የሥጋ ዘመዶቻቸው ሞት ቢያማቸውም) እርማቸውን ውጠው ከእግዚአብሔር ፍትሕ ጋር በመስማማት እንዲቀጥሉ ተነገራቸው፡፡ የእግዚአብሔር መሠዊያ ሲረክስ፣ ቀዳሚ ተቆርቋሪነታቸው በመሠዊያው ለሚመለከው አምላክ እንጂ መሠዊያውን አርክሰው ለተቀጡት ዘመዶቻቸው አልነበረም፡፡

ዛሬም እንዲያ ነው! ከየትኛውም አካል ጋር ጥብቅ የስሜት ቁርኝት ቢኖረንም ከእግዚአብሔር ክብርና ስም አይበልጥም፡፡ እርሱ ለክብሩ ያለው ቀናኢነት በእኛም ዘንድ እንዲኖር ይፈልጋል፡፡

አንዳንዶቻችን የእግዚአብሔር ክብር ሲነካ ምንም የማይመስለን፣ የሆነ የምንወደው ሰው (አገልጋይ) ሲነካ አገር ይያዝልን የምንል ነን፡፡ ከእግዚአብሔር ቅድስና በላይ የአጥፊው ሞራል ያሳስበናል፡፡ የእግዚአብሔር ስም በገዛ መሠዊያው ላይ ሲቃለልና ሲረክስ “የዝሆን ጆሮ ይስጠኝ” ያሉ ብዙዎች፣ ያጠፉ አገልጋዮች ሲገሰጹ ከዛጎላቸው ብቅ ብቅ ይላሉ፡፡ ኢየሱስ ሲሰደብ አፉን ሸብቦ የተቀመጠ፣ ኢየሱስን በሰደቡት ላይ ጠንካራ ቃል ስትናገር አፉ ይፈታል፡፡ ሊያሸማቅቅህ ሰይፉን ስሎ ይከሰታል፡፡ የእረኞች ዐለቃ ሲዋረድ ያልቆረቆረው፣ የሆነ የሚወደው እረኛ (መጋቢ) የተዋረደ ሲመስለው ያንዘረዝረዋል፡፡

ከእግዚአብሔር ወገን ከሆንን፣ ከሰው ክብር በላይ የእርሱን ክብር አብልጠን እንውደድ፡፡ የምንቆረቆርላቸውን አገልጋዮች፣ የእውነት የምንወዳቸው ከሆነ፣ የእግዚአብሔርን ክብር ነክተው እንዳይጠፉ እንንገራቸው፡፡ ቅድስናውን ለማቃለል ዳር ዳር ሲሉ “ተው” እንበላቸው፡፡ አደባባይ የወጣ ጥፋታቸውን መደባበቅና ለእነርሱ ጥብቅና መቆም፣ ወደ ባሰ እልኸኝት ይመራቸው እንደ ሆነ እንጂ ምንም አይጠቅማቸውም፡፡
የእግዚአብሔር ክብር ይበልጣል!

አሳየኸኝ ለገሠ