Get Mystery Box with random crypto!

“ውጫዊ ተስፋ” ከፍጥረቱ ጀምሮ ሰው ብቸኛ ተስፋው በሆነው በፈጣሪው ላይ አምጿል፤ ከብቸኛ ከለላ | ሰንፔር ሚዲያ Sapphire Media

“ውጫዊ ተስፋ”

ከፍጥረቱ ጀምሮ ሰው ብቸኛ ተስፋው በሆነው በፈጣሪው ላይ አምጿል፤ ከብቸኛ ከለላው ሽሽቷል። በዚያው ቅጽበት ሞት ነግሦበት፥ በሞት ፍርሃት ቀንበር ውስጥ ይኖራል። ገና ከጅምሩ ኅፍረቱን በግል ጥረቱ ለመሸፈን ቅጠል አገልድሟል፤ ሕሊናውን ሊያነጻ ግን አልቻለም። ሕያው ምንጭ የሆነውን አምላኩን ትቶ፥ ውሃ መያዝ የማይችሉ ቀዳዳ ማሰሮችን ይሰበስባል። ያለ ተስፋ መንከራተት ዕጣ ክፍሉ ሆኗል።

መልካም የማሰብና የማድረግ ፈቃዱና ዐቅሙ በክፉ እስራት ስለተያዘበት፥ ቢዳክርም የውስጡን መሻት ሊያረካ አልቻለም ። በተፍጨረጨረ ቊጥር ይበልጥ ተስፋ ይቆርጣል፤ በክፋት ረግረግ ውስጥ ይሰጥማል። የቁጣና የእርግማን ልጅ ስለሆነ ፍቅርና ምህረትን፤ ጥላቻ ስላዳሸቀው ሰላምና ዕርቅን ውስጡ ክፉኛ ይናፍቃል። በውስጡ ምንም በጎነት የሌለው ምውት ስለሆነ ከውጭ የሆነ የሚቤዤው ተስፋ አስፈልጎታል!

ይኼም ተስፋ፥ ጊዜውን ጠብቈ በ“ወንጌል” በኩል ተገልጧል። ወንጌል፥ ከዑር ምድር ተጠርቶ ለወጣውና የሕዝብ አባት ለተባለው ለአብርሃም በተገባው “ዘላለማዊው ኪዳን” አማካኝነት የተበሠረ የምስራች ነው። በይስሃቅና በያዕቆብ ቤት አልፎ፥ በይሁዳ ነገድ በኩል ተሻግሮ በእሰይ ልጅ በዳዊት “የዘለዓለም ንግሥና ኪዳን” ሆኖ ጸንቷል። የኪዳኑ ተስፋ ከዛሬ ፪ሺ ዓመት በፊት በይሁዳ ቤተልሔም በተወለደው የእስራኤል መሲሕ በኩል ዕውን ሆኗል!

እርሱም [መሲሑ] በዕውቀቱ ብዙዎችን የሚያድን የተስፋውን ቃል የተሸከመ የተስፋው ዘር ነው! ሰው ፈቅዶ በትዕቢቱ አምፆ፥ እግዚአብሔር ፈቅዶ በፍቅሩ የታረቀው በርሱ በኲል ነው። በመስቀል ቤዛነቱ ዕርቅ - ሰው ተስፋውን የሚሳለምበትን ዐዲስ መንገድ በደሙ ተመርቈ ተከፈተለት። በሚገለባበጥ ኪሩቤል የተዘጋው አስፈሪው የፍርድ በር፥ በሥጋው በኩል በድፍረት የሚገባበት የምሕረት በር ኾነ። የዕብራውያን ጸሐፊ ይኼን ሲያስረግጥ እንዲህ ይላል፤ “እኛም የነፍስ መልሕቅ የሆነ ጽኑና አስተማማኝ ተስፋ አለን፤ ይህም ተስፋ ከመጋረጃው በስተ ጀርባ ወዳለው ውስጠኛ መቅደስ ይገባል።” [6:19]

በወንጌል እውነት የተገለጠው “ሕያው ተስፋ” [1ጴጥ 1፥3]፣ ሰው ከውጭ የሚቀበለው “እንግዳ” ተስፋ እንጂ ከውስጡና ከአካባቢው የሚመነጭ አይደለም። “የክብር ተስፋ” [ቆላ 1፥27] መሠረቱ በተስፋው ዘር፥ በመሲሑ ኢየሱስ ላይ እንጂ በሰው ማንነትና ሁኔታ ሊሆን አይችልም። ብዙ ተሞክሮም አልተሳካም!

ሲ.ኤስ.ሉዊስ እንደሚለው “በዚህ ዓለም የምትሻውን ነገር እንሰጥሃለን የሚሉ ብዙ ነገሮች አሉ፤ ነገር ግን አንዳቸውም የሚሉትን አይሰጡህም። ...የትኛውም ልምምድ ሊያረካው የማይችል መሻት በውስጤ ካገኘሁ፣ ሊከተል የሚችለው ማብራሪያ ለሌላ ዓለም የተሠራሁ መሆኔ ነው። ምክንያቱም ፍጡራን ማርኪያ የሌለው መሻት ይዘው አልመጡምና።”

በቅዱሳት መጻሕፍትም፥ ተስፋ አንድም ቦታ ከሰው ማንነትና ልዩ ችሎታ ጋር ተያይዞ አልተገለጸም። የእስትንፋሱ ባለቤት ከሆነው ከአምላኩ ጋር እንጂ! የሰው ውስጣዊ ማንነቱና ችሎታው ተስፋን የመስጠት ዐቅም ቢኖራቸው፥ የተስፋው ዘር [ክርስቶስ] ለድነቱ ባላስፈለገው ነበር። ከአምላክነት የከፍታ ጫፍ ወርዶ፥ የሰብዕን የዝቅታ ጫፍ ባልቀመሰም ነበር።

ከዚህ ውጭ የኾነ ለሰው ልጅ ተስፋ የሚመስል ነገር ሁሉ፤ የማይጨበጥ ጒም፣ የሚያሰጥም አሸዋ፣ የሚያዳልጥ ጭቃ ነው። እንዲያረካን ጠጥተን ጥም የሚጨምር፤ ተደግፈንበት መሰበሩ ሳያንስ ወግቶ የሚያቈስል የሸንበቆ ምርኲዝ ነው። የቤተ ክርስቲያን አባት ቅዱስ አውግስጢኖስ በኑዛዜው ስለመፍትኼው ሲናገር...“ለአንተ ፈጥረኸናልና፤ ልባችንም በአንተ እስኪያርፍ ድረስ ዕረፍት አያገኝም” ብሏል!

ለዚህም ነው፤ የሰውን ዐቅምና ልዩ ችሎታ ከሚያጎሉና ከሚያንቈለጳጵሱ መድረኮች፥ እንዲሁም ሰው ተኮር “ሰባኪያን” መራቅ የሚያስፈልገው! ጊዚያዊ ተስፋዎቻችንም ቢሆኑ እንኳ፥ ትርጉም አግኝተው ሊያረኩን የሚችሉት ከማያሳፍረው “የክብር ተስፋ” መደላድል ላይ ሲስፈነጠሩ ብቻ ነው!

መልካም እሑድ!

ፍጹማን ግርማ