Get Mystery Box with random crypto!

ድሮ ነው አሉ፤ ሰውዬው ለአሽከራቸው ክፉ ነበሩ። በተለይ ሲበሉ ሰው እንዲያያቸው አይፈልጉም።አሽከራ | Semeredin Shemsee

ድሮ ነው አሉ፤ ሰውዬው ለአሽከራቸው ክፉ ነበሩ። በተለይ ሲበሉ ሰው እንዲያያቸው አይፈልጉም።አሽከራቸው ሁል ጊዜ ቀን አደግድጎ ማታ መብራት ይዞ ይመግባቸዋል።

ታዲያ አልፎ አልፎ ያጎርሱኛል በሚል ተስፋ ዞር እያለ ቢያያቸው እሳቸው እንኳንስ ሊያጎርሱት ቀርቶ ለምን ዞር ብሎ ያየኛል ሲሉ በዐይነ መዓት እያዩት ጥርግ አድርገው ይበላሉ ።አሽከራቸው እንደ አህያ ቢሰራላቸውም፣ እሳቸውን አደግድጎ ቆሞ ሲመግብ መብራቱን ይዞ ፊቱን አዙሮ መቆም ሲገባው ''ምን አባቱ እየዞረ ያየኛል '' በሚል ብቻ ይጠሉት ነበር።

አንድ ቀን ይሄው አሽከራቸው በጠና ይታመምና ወደ ሀኪም ቤት ይዘውት ይሄዳሉ። ከምርመራው በኃላ መርፌ መወጋት ስለነበረበት ሀኪሙ መርፌውን ወደ ታፋው ሲያመቻች ሰውዬው ከኃላ ቆመው ዶክተሩን ''ዶክተር እባክህን ታፋውን ሳይሆን ማጅራቱን ውጋልኝ '' ይሉታል ።ሀኪሙም በሰውዬው ንግግር ቢገረምም እንደማይሆን ነገራቸው ።

ሰውዬው አሁንም ማጅራቱን እንዲወጋላቸው ይለምናሉ ፣ሁለቱ ሲከራከሩ አሽከርየው ጣልቃ ይገባና ''ዶክተርዬ ተወው አትከራከር፤ ያመመኝ ማጅራቴን ባይሆንም ለጌቶች ሲባል ማጅራቴን ውጋኝ'' አለ ይባላል ።

ስንቶቻችን ይሉኝታ በሚሉት ገመድ ተተብትበን የበላንን ሳይሆን ያልበላንን ለማከክ ተገደን እንኖር ይሆን ? ግን ለም ? እኛ ስለራሳችን መኖር ሲገባን ከራሳችን በላይ ስለራሳቸው ብቻ ሊያኖሩን የሚሞክሩትን ሁሉ ዝም ማለት ተገቢ አይመስለኝም ።