Get Mystery Box with random crypto!

እንዳትሆን ጠንቀቅ በል! أَفَرَأَيْتَ مَنِ اتَّخَذَ إِلَهَهُ هَوَاهُ | የምስራቅ እስቴ ወረዳ ሰለፍዮች ቻናል።

እንዳትሆን ጠንቀቅ በል!
أَفَرَأَيْتَ مَنِ اتَّخَذَ إِلَهَهُ هَوَاهُ وَأَضَلَّهُ اللَّهُ عَلَى عِلْمٍ وَخَتَمَ عَلَى سَمْعِهِ وَقَلْبِهِ وَجَعَلَ عَلَى بَصَرِهِ غِشَاوَةً فَمَنْ يَهْدِيهِ مِنْ بَعْدِ اللَّهِ أَفَلَا تَذَكَّرُونَ
((ዝንባሌውን አምላኩ አድርጎ የያዘውን፣ አላህም ከእውቀት ጋር ያጠመመውን፣ በጆሮውና በልቡ ላይም ያተመበትን፣ በዐይኑም ላይ ሺፋን ያደረገበትን ሰው አየህን! ታዲያ ከአላህ በኋላ የሚያቀናው ማነው አትገሰፁምን)) (አልጃሢያህ፡ 23)
9. በኳስ ምክኒያት የራስህንም ሀላፊነት ያለብህን አካላትም ሐቅ እንዳትሸራርፍ፡፡ ሰርክ ኳስ እያሳደድክ በዚያ ሳቢያ ሀላፊነትህን ባግባቡ እየተወጣህ ካልሆነ አደጋ ላይ ነው ያለኸው፡፡ ነብዩ ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም “ሁላችሁም እረኛ ናችሁ (ሀላፊነት አለባችሁ)፡፡ እያንዳንዳችሁም ስለእረኝነታችሁ (የተሸከማችሁት ሀላፊነት) ተጠያቂ ናችሁ) ይላሉ፡፡ መከታተሉ በጤናም ይሁን በትኛውም መልኩ እራስህንም የሚጎዳ መሆን የለበትም፡፡ አይደለም በቀልድና በዛዛታ ቀርቶ በዒባዳም እራስን መጎዳት አይፈቀድም፡፡ እስኪ ይህን ታሪክ አንዴ እንመልከት፡፡ ነብዩ ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም መዲና ሲገቡ ሰልማኑልፋሪሲን እና አቡ ደርዳእን ረዲየላሁ ዐንሁማ ወንድማማች አድርገው አቆራኟቸው፡፡ ሰልማን አቡደርዳእን ሊጎበኝ ቤቱ ሲመጣ ሚስቱ ኡሙ ደርዳእ ረዲላሁ ዐንሃ እራሷን ጥላ አያት፡፡ “ምን ሆነሻል?” አላት፡፡ “አይ ወንድምህ አቡደርዳእ ለዱንያ ደንታ የለውም” ስትል እንዲያ የሆነችበትን ምክኒያት ነገረችው፡፡ ወዲያው አቡ ደርዳእ መጣ፡፡ ለሰልማን ምግብ አዘጋጀለትና “ብላ እኔ ፆመኛ ነኝ” አለው፡፡ ሰልማን ግን “አንተ ካልበላህ የምበላ አይደለሁም” አለው፡፡ ከዚያም (ፆሙን አፍርሶ) በላ…፡፡ ሌሊቱ ሲመጣ አቡ ደርዳእ ለሰላት ተነሳ፡፡ “ተኛ” አለው ሰልማን፡፡ ቆይቶም ተነሳ፡፡ “ተኛ” አለው አሁንም፡፡ የሌሊቱ መጨረሻ ሲደርስ ሰልማን እራሱ “ተነስ” አለውና አብረው ሰገዱ፡፡ ከዚያም ሰልማን እንዲህ አለው “ለጌታህ ባንተ ላይ ሐቅ አለ፡፡ ለራስህም ባንተ ላይ ሐቅ አለ፡፡ ለቤተሰብህም ባንተ ላይ ሐቅ አለ፡፡ እያንዳንዱን ባለሐቅ ሐቁን ስጥ!!” አቡ ደርዳእ ከነብዩ ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ዘንድ ሄደና የሆነውን ነገራቸው፡፡ እሳቸውም “ሰልማን እውነት ተናገረ” አሉ፡፡ (ቡኻሪ የዘገቡት ነው) እንግዲህ አስተውል ሰሐባው በኳስ ሳይሆን በዒባዳ እንኳን እራሱን መጠበቅ እንዳለበት ተነግሮታል፡፡ አንተስ?
10. በኳስ ምክኒያት አጉል ወገንተኝነትና ዘረኝነት ውስጥ አትግባ!! ዘረኝነት የመሀይማን መገለጫ ነው!! ነብዩ ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ((ተዋት! ምክኒያቱም እሷ (ዘረኝነት) ጥንብ ነችና!)) ይላሉ፡፡
11. በኳስ ምክኒያት አጉል ቁጣ ውስጥ አትግባ፡- ነብዩ ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም “ምከረኝ” ያላቸውን ሰው (አትቆጣ!) ብለውታል፡፡ ደጋግሞ ሲጠይቃቸው ደጋግመው ((አትቆጣ!!) ብለውታል፡፡ “እከሌ ቡድን ተሸነፈ” ብሎ አጉል ብስጭት ውስጥ የሚገባን “ቂል” የሚለው ቃል በበቂ ሁኔታ ይገልፀው ይሆን?!! እኔ እንጃ!
12. አንዱን ቡድን ለመደገፍ በሚል ተልካሻ ሰበብ አታጨብጭብ! አትዝፈን! አትጨፍር፡፡ ዘፈን የተፈቀደው ውስን የሆኑ ክስተቶችን ምክኒያት በማድረግ ለሴቶች ብቻ ነው፡፡ ነብዩ ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም እንዲህ ይላሉ፡ (ሁለት ድምፆች የተረገሙ ናቸው!! የፀጋ ጊዜ መዝሙር እና የፈተና ጊዜ ዋይታ!!) “ወንድ ከዘፈነ ሴት ሆነ” ይላሉ ሸይኹል ኢስላም ኢብኑ ተይሚያ እና ሸይኹል አልባኒ አላህ ይማራቸውና፡፡
13. ኧረ ከአቅል ሁን! ለመሆኑ ኳስ ሲከታተሉ ገደብ የለሽ ስሜት ውስጥ ስለገቡ ብቻ የሚሞቱ ሰዎች እንዳሉ ታውቅ ይሆን? ካላወቅክ በዚህ ላይ የተደረጉ ጥናቶችን አፈላልግ፡፡ “እከሌ ቡድን ተሸነፈ” ብለው እራሳቸውን የሚያጠፉ እንደሚያጋጥሙስ ይሰወርህ ይሆን? ብቻ ከኳስ ጋር በተያያዘ በየትኛውም ምክኒያት ህይወትህን ብታጣ ነገ አላህ ፊት መልስህ ምን እንደሚሆን ከወዲሁ አስብበት!! ጂሃድ ላይ አስደናቂ ጀብዱ ሲፈፅም ውሎ በደረሰበት ቁስለት ስቃዩን መቋቋም አቅቶት እራሱን የገደለውን ሰው ነብዩ ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም “የእሳት ነው!” ማለታቸውን አትዘንጋ፡፡ አንተ ከሱ የተሻለ አሳማኝ ምክኒያት ካለህ ቀጥልበት!! አስተውል! ሞት አማክሮ አይመጣም፡፡
14. በኳስ ምክኒያት አንዱን በመደገፍ ሌላውን በመንቀፍ፣ ሌሎችን ለማናደድ፣ ወይም እንዲሁ በአጉል ብስጭት ፀያፍ ቃላትን አታውጣ! ዘወትር “ሐያእ” አይለይህ፡፡ ነብዩ ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ምን እንደሚሉ አስተውል!
((الْبَذَاءُ مِنَ الْجَفَاءِ, وَالْجَفَاءُ فِي النَّارِ, وَالْحَيَاءُ مِنَ الْإِيمَانِ, وَالْإِيمَانُ فِي الجنة))
((ፀያፍ ቃላት መጠቀም ዋልጌነት ነው! ዋልጌነት ደግሞ ወደ እሳት ነው!! “ሐያእ” ከኢማን ነው፡፡ ኢማን ደግሞ ወደ ጀነት ነው!!)) ሸይኹል አልባኒ “ሰሒሕ” ብለውታል፡፡ (አስ-ሰሒሐህ፡ 495)
15. ኳስ ለመመልከት ብለህ ከአጅነቢ ሴት ጋር ተቀላቅለህ እንዳትቀመጥ፡፡ መቀላቀሉ ሌላው ቀርቶ ሰይጣናዊ ጉትጎታ ከሚቀንስበትም ቦታም አልተፈቀደም፡፡ ለሴቶች ከመስጂድ ይልቅ ቤታቸው እንዲሰግዱ መመረጡን ለመስገድ ከወጡም ሽቶ ሳይቀቡ፣ ሳይዋዋቡ መሆኑን አስተውል፡፡ ነብዩ ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም “ከወንዶች የሰላት ሰፎች በላጩ የመጀመሪያው ነው፣ የከፋው ደግሞ የመጨረሻው (ለሴቶቹ የሚቀርበው) ነው፡፡ ከሴቶቹ የሰላት ሰፎች ደግሞ በላጩ የመጨረሻው (ከወንዶች የራቀው) ነው፡፡ የከፋው ደግሞ የመጀመሪያው (ለወንዶቹ የቀረበው) ነው” ማለታቸውን አስተውል፡፡ ሌላው ቀርቶ ነብዩ ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ወንዶችና ሴቶች ከመስጂድ ውጭ ከሰላት ሲመለሱ ቢቀላቀሉ ሴቶቹን “ወደ ኋላ ሁኑ” ብለው ዳር ይዘው እንዲሄዱ ነው የነገሯቸው፡፡
16. ኳስ ለማየት ብለህ አስካሪ መጠጥ ከሚሸጥበት ወይም ከሚጠጣበት “ባር” እና “ካፍቴሪያ” ውስጥ ወይም ሌሎች ወንጀሎች ከሚፈፀሙባቸው አካባቢዎች ድርሽ እንዳትል፡፡ አላህን ፍራ! እምነትህንም እራስህን አክብር፡፡
ኢን ሻአላህ ከቻልኩ በዚህ ጉዳይ የኡለማዎችን ብይን አሰባስቤ ለመመለስ እሞክራለሁ፡፡
~----~~ ----
(ኢብኑ ሙነወር፣ ሃምሌ 03/2006)
የቴሌግራም ቻናል
https://t.me/IbnuMunewor