Get Mystery Box with random crypto!

ልብ አድርግልኝ!! እያወራሁ ያለሁት ሃላፊነት የማይሰማው ደዩስ ባል እንደሚያደርገው እንድትሆን አይ | የምስራቅ እስቴ ወረዳ ሰለፍዮች ቻናል።

ልብ አድርግልኝ!! እያወራሁ ያለሁት ሃላፊነት የማይሰማው ደዩስ ባል እንደሚያደርገው እንድትሆን አይደለም፡፡ ምን ለበሰች? አይገደውም፡፡ ማን ጋ ዋለች? አይደንቀውም፡፡ የት አመሸች? አይሞቀውም፡፡ ይሄ ደዩስ ነው! ከርፋፋ ነገር፡፡ ደይዩስነት ከእንስሳትም አሳማዎች ጋር ነው በስፋት የሚንፀባረቀው፡፡ የወንድ አልጫ ማለት ይሄ ነው፡፡ እራሱ ኃላፊነቱን ጥሎ ጠፍቶ የሚያጠፋ እንከፍ፡፡ እንጂ ወንድ ማለት “ወጥ ቀጠነ” ብሎ አቧራ የሚያስነሳ፣ ምግብ ላይ የሆነ ጉድፍ አገኘሁ ብሎ አገር የሚበጠብጥ አይደለም፡፡ ቢገባህ ነብዩ ﷺ የቀረበላቸው ምግብ ከተመቻቸው ይበሉታል፡፡ ካልሆነ ግን አቃቂር እያወጡ ነገር አይሰነጥቁም፣ በነገር አይሸነቁጡም፡፡ ታዲያ አርአያህ ማን እንዲሆን ነው የምትፈልገው? ጌታችን (ለእናንተ አላህንና የመጨረሻውን ቀን የሚከጅል ለሆነ ሰው፣ አላህንም በብዙ ለሚያወሳ በአላህ መልእክተኛ ላይ መልካም ምሳሌ አለላችሁ!!) ይላል፡፡ [አሕዛብ፡ 21]
ወንድሜ የሚስትህን ነውር ለማንም አታውራ፡፡ ማንም ቢሆን የሚስትህን ያክል ቅርብ አይደለም፡፡ አንተን ባል ብላ ለእናት ለአባቷ የማትገልጠውን ገላዋን ላንተ ነፃ አድርጋለች፡፡ ልብስ እንደሆንክላት ልብስህ ሆናልሃለች፡፡ አዎ ሚስትህ ከየትኛውም አልባሳት የበለጠች ምቾትን የምትሰጥህ፣ ነውርህን የምትሸፍንልህ ቆንጆ ልብስህ ናት፡፡ ልብስህን እየገሸለጥክ የራስህን ነውር ባደባባይ አታስጣ፡፡ ሌላው ቀርቶ ብትፈታት እንኳን ነውሯን አትዝራ፡፡ ከሰለፎች አንዱ ከሚስቱ ጋር የሆነ ክፍተት ይኖርበታል፡፡ “ምንድነው ችግሩ?” ቢሉት “እንዴ! እንዴት ብየ የሚስቴን ነውር አወጣለሁ?” አላቸው፡፡ ከሚስቱ ጋር ሲለያይ ጊዜ “እሺ አሁንስ ምን ነበር ችግሯ? ንገረን” አሉት፡፡ “እንዴ! እኔ ምን አግብቶኝ ነው የሌላ ሰው ነውር የማወጣው?” አላቸው፡፡ እኛ ግን አብረንም ሆነን ከሰው ሁሉ ለአካላችን ቅርብ የሆነች ሚስታችንን ነውር የሷን ያክል ለማይቀርበን ምናልባትም ይሄ ነው የሚባል ቅርበት ለሌለን ሰው እንዘከዝካለን፡፡ ከተለያየንማ ጭራሽ የሌለውንም ጭምር እንቀደዳለን፡፡ አንዳንዱማ የራሱን ነውር ለመሸፈን በሌለችበት የሚወነጅል አለ!! አላሁል ሙስተዓን!! ያለባትን ብናወራ ያገጠጠ ሃሜት ነው፣ በህይወት አጋራችን ላይ የሚፈፀም ክህደት!! የሌለባትን ብናወራ አይን ያወጣ ቅጥፈት ነው፣ ድንገት ያስተዋሉ እለት ህሊናን የሚጠዘጥዝ ውርደት!!
ወንድሜ! ካለልህ ለሚስትህ ደግ ሁን፡፡ ባል እንጂ ደባል አትሁን፡፡ ስትመጣ ተፍለቅልቃ በደስታ የምትቀበልህ እንጂ ገና መምጫህ ሲቃረብ ልቧ የሚጨነቅ የሚጠበብ፣ ድምፅህ ሲሰማ አመዷ የሚቦን አታድርጋት፡፡ ከቻልክ በመልካም ተኗኗር፡፡ ካልሆነልህ በመልካም ተለያይ፡፡ አለቀ፡፡ (በመልካም መያዝ፤ ካልሆነ በበጎ መለያየት) ይላል ቁርኣኑ፡፡ [አልበቀራህ፡ 229] አስተውል! ብትለያዩም ሙስሊማ እህትህ እንጂ ጠላትህ አይደለችም፡፡ በተለይ ደግሞ ልጆች ካሏችሁ የግፍ ሰንሰለትህን እያረዘምክ ከጓዳህ ጠላት አታፍራ፡፡ ምንም አይነት ቂምና በቀል አያስፈልግም፡፡ በጣም የሚገርመው በሰላሙ ጊዜ ስንት ህይወት እንዳላሳለፉ፣ ስንት መከራ አብረው እንዳልገፉ፣… እህል ውሃቸው አልቆ መለያየት ሲመጣ ጊዜ ለመስማት የሚሰቀጥጡ፣ ለማየት የሚያንቀጠቅጡ ግፎች ሲፈፀሙ ይታያል፡፡ አንዳንዱ ጨቅላ ልጇን ከላዩዋ ላይ የሚመነጭቅ አለ፡፡ ሌላው ድሮ ያልሰጣትን መህሯን የሚክድ አለ፡፡ ዐጂብ የሆነ መውረድ!! ሌላው ከሷ አልፎ ቤተሰቧን ጭምር አበሳ የሚያሳይ አለ፡፡ ሌላው “እስኪ ከዚህ በኋላ የሚያገባትን አየዋለሁ” አይነት የሚፎክር አለ፡፡ አንዴ ከተለያየ በኋላ ከሚያገባት ሰው ጋር መቀያየም ግፋ ሲልም መደባደብ ምን የሚሉት እብሪት ነው?! ሱብሓነላህ! እስኪ ይህን በጉልበት የሚታሰብበት የጃሂሊያህ ሱና ተመልከቱ፡፡ እስኪ እንዲህ አይነቱን ቂላቂል የራሱ ጠላት ታዘቡ፡፡ ይሄ ድሮም ሲበድል እንደኖረ፣ ሲለያይም በሰላም እንዳልተለያየ በግልፅ እያመላከተ ነው፡፡
እስኪ አሁን ጨቅላ ህፃንን ከእናት እቅፍ በመመንጨቅ የፈታትን ሚስት መበቀል ምን የሚሉት አረመኔነት ነው? አቤት የሰው ልጅ ገልቱነት! አቤት የሰው ልጅ ጭካኔ!! በርግጠኝነት ይህን የሚያደርገው ለልጁ ተቆርቁሮ አይደለም፡፡ ተምሳሌት የሆነ ልዩ የእናትነት ፍቅሯን፣ በርህራሄ የሚንሰፈሰፍ አንጀቷን አይቶ በልጇ የሚበቀል ወንድ ያለጥርጥር ወንዶች በወንድነታቸው እንዲያፍሩ፣ ሴቶች ወንዶችን ጭራቅ አድርገው እንዲስሉ የሚያደርግ ሲበዛ ርካሽ የሆነ ምግባር ነው!!
አላህ ማስተዋሉን ያድለን፡፡
(ኢብኑ ሙነወር፣ ጥቅምት 26/2008)
የቴሌግራም ቻናል፦
https://t.me/IbnuMunewor