Get Mystery Box with random crypto!

“አዋጅ! በሴቶች ላይ መልካምን ዋሉ አደራ!” ~ ~~~~ ~~~~ ~~~~ ~~~ እርግጥ ነው ትዳር | የምስራቅ እስቴ ወረዳ ሰለፍዮች ቻናል።

“አዋጅ! በሴቶች ላይ መልካምን ዋሉ አደራ!”
~ ~~~~ ~~~~ ~~~~ ~~~
እርግጥ ነው ትዳር በራሱ ትምህርት ቤት ነው፡፡ ነገር ግን ትዳር ሃላፊነት በጎደለው መልኩ ባልና ሚስት እንደ አቡሽ እና እንደ ሚጣ የሚነፋረቁበት ወይም የሚቦርቁበት መዋእለ ህፃናት አይደለም፡፡ አዎ በአንድ ጎጆ ውስጥ የሚኖር ሰው ቀርቶ በሆነ አጋጣሚ የተገናኘም ሰው ሊገፋፋና ሊጋጭ ይችላል፡፡ ይሄ በዱንያ ውስጥ ከምንፈተንባቸው ነገሮች አንዱ እንደመሆኑ በጥንቃቄ ልንጓዝ ይገባናል፡፡ ጌታችን እንዲህ ይላል፡-
(وَجَعَلۡنَا بَعۡضَكُمۡ لِبَعۡضࣲ فِتۡنَةً أَتَصۡبِرُونَۗ )
“ከፊላችሁንም ለከፊላችሁ ፈተና አድርገናል፡፡ ትታገሳላችሁን?” [አልፉርቃን፡ 20]
በትዳር ውስጥ በሴቶች ላይ የሚፈፀሙ እጅግ የበዙ ግፎችን ስመለከት እና ስሰማ የራሴ ሁኔታ ያስፈራኛል፡፡ ብዙ ሰው የትዳር ሰሞን “አበድኩልሽ ከነፍኩልሽ” እንዳላለ በእጁ ማስገባቱን ባረጋገጠ ማግስት ነገሮች መቀየር ይጀምራሉ፡፡ እዚህ ግባ በማይባሉ ምክንያቶች “አይንሽን ላፈር” የሚለውን ቤቱ ይቁጠረው፡፡ አንዳንዱ ለአስቤዛ መቶ ሰጥቶ የሁለት መቶ መስተንግዶ የሚጠብቅ አለ፡፡ ሌላው ለውጭ ሰው ተጨዋች፣ ተግባቢ፣ ሳቂታ፣ ገራገር ነው፡፡ ከቤቱ ሲገባ ግን ልጆቹ “መጣ መጣ” እያሉ በፍርሃት የሚያንሾካሹኩበት፣ ሚስት ካሁን አሁን “ምን ይል ይሆን?” እያለች በስጋት የምትዋጥበት አራስ ነብር ይሆናል፣ ግስላ፡፡ “የቤት ቀጋ የውጭ አልጋ” ይሏል እንዲህ ነው፡፡ ነብዩ ﷺ ግን “ከአማኞች ኢማኑ የተሟላው ስነ ምግባሩ ያማረው ነው፡፡ ከናንተ በላጫቻችሁ ለሴቶቻቸው በላጭ የሆኑት ናቸው” ብለው ነበር፡፡ [አሶሒሐህ፡ 284] ሌላው ሚስቱን፣ የልጆቹን እናት ከጭቃ የጠፈጠፋት ይመስል እንዳሰኘው ያደርጋታል፡፡ ከልጆቿ ፊት ያዋርዳታል፡፡ በዚህም ወይ እናት በልጆቿ እንድትናቅ በር ይከፍታል፤ አለያ ደግሞ ከተበዳይ እናታቸው ወግነው አባታቸውን እንደ ጠላት እንዲያዩ ያስገድዳል፡፡
መልእክተኛው ﷺ “በሴቶች ጉዳይ አደራችሁን” ብለው ነበር፡፡ [ቡኻሪና ሙስሊም] እጅግ ብዙ ወንድ ግን “ሴትና ጫማ ከአልጋ ስር” ነው ፖሊሲው፡፡ ሁሌ እሷን ካላሸማቀቀ፣ ሁሌ እሷን ካላዋረደ ወንድ የሆነ አይመስለውም፡፡ ወንድሜ ከሚስትህ የሆነ የማትወደው ባህሪ ሊኖር ይችላል፡፡ ሰው ነችና ይሄ የሚጠበቅ ነው፡፡ ግን ስላንተስ ማን ያውራ? አንተስ የሚጠላ ጎን አይኖርህምን? ምነውሳ ታዲያ የራስህንም ብታይ? ምነው በጎ ጎኖቿንም ብትመለከት? ምንም ጥሩ ነገር ሳታይባት ነው ለትዳር የመረጥካት? ነብዩ ﷺ እንዲህ ይላሉ፡- “አንድ ሙእሚን ወንድ አንዷን ሙእሚናህ ሴት (ሚስቱን) አይጥላ፡፡ ከሷ የሆነን ባህሪ ቢጠላ ሌላ የሚወደው አለውና፡፡” [ሙስሊም]
አንተ ያማረህን ከውጭ እየሰለቀጥክ ቤትህን የምትዘነጋ ከሆንክ ማሰቢያ የቀለለህ ገልቱ ነህ!! አንተ “እኔ ነኝ ያለ” እያማረጥክ እየለበስክ ሚስትህን የምትረሳ ከሆንክ ቀላል ነህ፣ ኪሎህ ቢከብድም ዋጋህ የወረደ!! ለመሆኑ ሚስትህን አንተ ካልፈቀድካት ማን ይፍቀዳት? ቤተሰቦቿማ አንተን ሰው ብለው፣ አንተን ባል ብለው አደራ ሰጥተውሃል!! ታዲያ ምነው አደራ በላ ትሆናለህ? አንተ በሚስትህ ላይ የምትሰራውን በእናትህ፣ በእህትህ፣ በሴት ልጅህ ላይ ሲፈፀም ብታየው ያስደስትሃልን? ይሄው ውዱ ነብይ ﷺ “ከምትበሉት አብሏቸው፡፡ ከምትለብሱትም አልብሷቸው፡፡ አትምቷቸውም፡፡ ...” ይላሉ፡፡ [ሶሒሕ አቢ ዳውድ፡ 1861] እስኪ ይህን ሐዲሥ እንደ መነሻ ይዘን እራሳችንን እንፈትሽ፡፡
አንዳንዱ አቅሙ ሳይኖረው ሁለተኛ ያገባና ቤቱን የጦርነት አውድማ ያደርገዋል፡፡ እራሱም ቤተሰቡም የሰቀቀን ህይወት እንዲገፉ ያደርጋቸዋል፡፡ ሌላው ሁለተኛ ባገባ ማግስት የመጀመሪያዋን ከነመኖሯም ይረሳታል፡፡ ጌታችን (አለማስተካከልንም ከፈራችሁ አንዲትን ብቻ ያዙ…) ሲል ነበር ያዘዘው፡፡ [አኒሳእ፡ 3] እሱ ግን “ትዳር አላት” እንዳይባል እርግፍ አድርጎ ትቷታል፡፡ “ትዳር የላትም” እንዳይባል ኒካሑ እንዳለ ነው፡፡ ((በአየር ላይ) እንደተጠለጠለችም አድርጋችሁ ትተዋት ዘንድ (ወደ ወደዳችኋት) መዘንበልን ሁሉ አትዘንበሉ) ብሎ ነበር ጠቢቡ ጌታ፡፡ [አኒሳእ፡ 129] ልብ በል! ነብዩ ﷺ “ሁለት ሚስት ኖሮት ወደ አንዷ ያጋደለ ሰው ነገ በቂያማ ቀን አንድ ጎኑ የወደቀ ሆኖ ይመጣል” ይላሉ፡፡ [ሶሒሑ መዋሪዲ ዞምኣን፡ 1089] ታዲያ መጨረሻህ ይህ እንዲሆን ነው የምትፈልገው? ወንድሜ የበደልካት ሚስትህን ሞት ሳይቀድምህ በፊት በጊዜ “ዐፍው” አስብላት፡፡ ያለበለዚያ ነብዩ ﷺ እንዳሉት “ግፍ ነገ የቂያማ ቀን የጨለማ ንብርብር ነው፡፡” [ቡኻሪና ሙስሊም] በየጓዳው በበዳይ ባሎቻቸው ግፍ ሳቢያ ደም እንባ የሚያነቡትን ሴቶች ቤቱ ይቁጠራቸው፡፡ ወላሂ ወንድነትህን ተጠቅመህ በደካማዋ ሴት ላይ የምትፈፅመው ግፍ እሷ ላይ ከደረሰው የከፋ ያስከፍልሃል፡፡ “የተበዳይን እርግማን ተጠንቀቅ፡፡ በሷና በአላህ መካከል መጋረጃ የለምና!!” ይላሉ ከልብ ወለድ የማይናገሩት ነብይ ﷺ፡፡ [ቡኻሪና ሙስሊም] የስሙን መጠሪያ የዐይን ማረፊያ ልጆቹን ከሷ አግኝቶ፣ ስሜቱን በሷ ላይ አርክቶ፣ ህይወቱን በሷ ላይ መስርቶ፣ የቤት ጣጣውን ሁሉ ከሷ ላይ ጥሎ፣ … ከዚያም አለጠም ጣፈጠ ያለፈውን ሁሉ በመዘንጋት ምንም ዋጋ እንደ ሌላት ልክ እንደ ቆሻሻ፣ እንደ ቆረቆንዳ መወርወር ምን የሚሉት ኢ-ሰብኣዊነት ነው?! ምን የሚሉትስ ገልቱነት ነው?! በእናትህ፣ በልጅህ፣ በእህትህ ላይ እንዲህ ቢፈፀም ደስ ይልሃልን? አትጠራጠር! የእጅህን ታፍሳለህ! የዘራሃውን ታጭዳለህ! “አልጀዛኡ ሚን ጂንሲል ዐመል” ይላሉ አበው፡፡ “ስራ ለሰሪው እሾህ ላጣሪው” እንደማለት፡፡
አትዘንጋ!! ልክ አንተ በሚስትህ ላይ ሐቅ እንዳለህ ሁሉ ሚስትህም ባንተ ላይ ሐቅ አላት፡፡ ሃይማኖታችን እንዲህ ነው የሚያዘው፡-
- (وَلَهُنَّ مِثۡلُ ٱلَّذِی عَلَیۡهِنَّ بِٱلۡمَعۡرُوفِۚ)
(ለእነሱም (ለሴቶቹ) የዚያ በነርሱ ላይ ያለባቸው (ሃላፊነት) አምሳያ (ሐቅ በባሎቻቸው ላይ) አላቸው፡፡” [አልበቀራህ፡ 228]
- (وَعَاشِرُوهُنَّ بِٱلۡمَعۡرُوفِۚ)
(በመልካም ተኗኗረዋቸው፡፡) [አኒሳእ፡ 19]
- “አዋጅ! ለናንተ በሴቶቻችሁ ላይ ሐቅ አላችሁ፡፡ ለሴቶቻችሁም በናንተ ላይ ሐቅ አላቸው፡፡” [ሶሒሑልጃሚዕ፡ 7880]
- “ለቤተሰብህም ባንተ ላይ ሐቅ አለ፡፡ እያንዳንዱን ባለ ሐቅ ሐቁን ስጥ!” [ቡኻሪ]
- “ለሚስትህ ባንተ ላይ ሐቅ አለ፡፡” [ቡኻሪና ሙስሊም]
ይልቅ ቂል አትሁን፡፡ ለሚስትህ/ቾህ፣ ለልጆችህ ደግ፣ ምቹ ሁንና ቤትህን ምድራዊ ጀነት አድርገው፡፡ ብቻ አንተ ቻልበት፡፡ ከጅምሩ ሷሊሐዋን ምረጥ፡፡ ወይም ሷሊሐ እንድትሆን ጣር፡፡ ያኔ ገና ስታያት ትረካለህ፡፡ በልጆችህ አስተዳደግ ትረካለህ፡፡ ላንተ ባላት መቆርቆር ትረካለህ፡፡ በጨዋነቷ፣ በቁጥብነቷ ትረካለህ፡፡ ዱንያ ላይ ከዚህ በላይ ምን ድሎት አለ?! ነብዩ ﷺ “ዱንያ መጣቀሚያ ነች፡፡ ከመጣቀሚያዎቿ ሁሉ በላጩ ደግ (ሷሊሐህ) የሆነች ሴት ናት” ይላሉ፡፡ [ሙስሊም]