Get Mystery Box with random crypto!

የአገሪቱ የስንዴ ፍላጎት ተሸፍኖ አሥር ሚሊዮን ኩንታል ትርፍ ምርት እንደሚገኝ ተገለጸ። ዘንድሮ | ሰሌዳ | Seleda

የአገሪቱ የስንዴ ፍላጎት ተሸፍኖ አሥር ሚሊዮን ኩንታል ትርፍ ምርት እንደሚገኝ ተገለጸ።

ዘንድሮ በመኸርና በበጋ መስኖ የሚለማው የስንዴ ምርት ለአገር ውስጥ ፍጆታ ከመዋል አልፎ አሥር ሚሊዮን ኩንታል ትርፍ የሚገኝበት መሆኑን የግብርና ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡ ሚኒስቴሩ እንዳስታወቀው፣ የ2014/15 የመኸር ምርት ዘመን ሰብል በዚህ ወቅት እየተሰበሰበ ሲሆን፣ ይገኛል ተብሎ ከሚጠበቀው 108 ሚሊዮን ኩንታል የስንዴ ምርት ባሻገር በበጋ መስኖ 52 ሚሊዮን  ኩንታል እንደሚገኝና በድምሩ 160 ሚሊዮን ኩንታል ምርት አገሪቱ ታገኛለች ተብሎ ይጠበቃል ተብሏል፡፡

የአገሪቱ የሕዝብ ቁጥር ግንዛቤ ውስጥ ገብቶ፣ በተጨማሪም በየዓመቱ የሚያድገውን የአገር ውስጥ የፍጆታ መጠን በትክክል በማስላት በ2015 ዓ.ም. 97 ሚሊዮን ኩንታል ስንዴ ለአገር ውስጥ ፍጆታ እንደሚያስፈልግ መረዳቱን ያስታወቀው የግብርና ሚኒስቴር፣ ይህንን ዝርዝር ጥናት በርካታ ኢኮኖሚስቶችና የሰብል ልማት ሰዎች ያጠኑት ስለመሆኑ ገልጿል፡፡

‹‹ሌላው ቢቀር በመኸርና በመስኖ ብንሠራ 107 ሚሊዮን ኩንታል ማምረት እንችላለን፣ በጣም በዝቅተኛ ግምት ነው ይህንን የገመትነው፡፡ ይህን ብቻ በማሰብ አሥር ሚሊዮን ኩንታል ትርፍ ምርት አለን፤›› ያሉት በግብርና ሚኒስቴር የእርሻና ሆልቲካልቸር ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ መለሰ መኮንን (ዶ/ር)፣ በድምሩ በመኸርና በመስኖ የሚለማው የምርት መጠን ከታቀደው በላይ እንደሚሆን አስረድተዋል፡፡ ‹‹አሥር ሚሊዮን አይደለም ከዚያ በላይ ትርፍ ማምረት የምንችልበት ዕድል አለ፡፡ ይህንንም ኤክስፖርት ማድረግ የምንችልበት ዕድል አለ፤›› ሲሉ  ሚኒስትር ዴኤታው መናገራቸውን ሪፖርተር ዘግቧል፡፡