Get Mystery Box with random crypto!

ባንኮች ከሚያበድሩት 20 በመቶውን የግምጃ ቤት ሰነድ እንዲገዙበት የሚያስገድድ መመርያ ፀደቀ። | ሰሌዳ | Seleda

ባንኮች ከሚያበድሩት 20 በመቶውን የግምጃ ቤት ሰነድ እንዲገዙበት የሚያስገድድ መመርያ ፀደቀ።

ሁሉም የንግድ ባንኮች ከሚለቁት ብድር ውስጥ 20 በመቶውን በየወሩ ወደ መንግሥት የግምጃ ቤት ሰነድ ግዥ ፈሰስ እንዲያደርጉ የሚያስገድድ መመርያ መፅደቁን ሪፖርተር ዘግቧል፡፡ ከትናንት ጥቅምት 22 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ ተግባራዊ የሆነው መመርያ፣ ከኢትዮጵያ ልማት ባንክ ውጪ በሁሉም ባንክ ላይ ተግባራዊ ይሆናል፡፡

ባንኮቹ ያበደሩትን 20 ከመቶን በየወሩ እያሠሉ የግምጃ ቤት ሰነድ የሚገዙበት ገንዘብ ተጠራቅሞ አምስተኛው ዓመት ላይ የሚመለስላቸው ሲሆን፣ የወለድ መጠኑም ከተቀማጭ ወለድ ላይ ሁለት ከመቶ በመጨመር ይሆናል፡፡ ካለፈው ዓመት መስከረም ወር ጀምሮ ባንኮች የጠቅላላ ዓመታዊ ብድራቸውን አንድ በመቶ ከኢትዮጵያ ልማት ባንክን ቦንድ እንዲገዙበት የሚያዘው መመርያ እየተተገበረ ሲሆን፣ ይህ መመርያ ለአሥር ዓመታት የሚቀጥል ነው፡፡

አዲስ ከወጣው መመርያ ጋር ባንኮች በአጠቃላይ ከሚያበድሩት 21 በመቶውን ወደ መንግሥት ፋይናንስ ፈሰስ ያደርጋሉ ማለት ነው፡፡ ከዚሁ በተጓዳኝ ባንኮች ሰባት ከመቶ መጠባበቂያ ገንዘብ ማስቀመጥ እንዳለባቸው ይታወቃል፡፡ ስለዚህ በአጠቃላይ ባንኮች ከሚሰበስቡት ጠቅላላ ተቀማጭ ውስጥ 28 በመቶውን በተለያየ ምክንያት መልሰው ለማበደር ሊጠቀሙት አይችሉም ማለት ነው፡፡

አዲሱ መመርያ ከዚህ ቀደም ባንኮች ይሰጡ ከነበረው የ27 በመቶ ግዴታ ጋር ተመሳሳይ ሲሆን፣ ልዩነቱ ይኼኛው በየወሩ መሆኑ፣ ወለዱ ከፍ ማለቱና ከባንኮች የተሰበሰበው የግምጃ ቤት ሰነድ መግዣ ገንዘብ በንግድ ባንክ በኩል ለመንግሥት የልማት ድርጅቶች መሰጠቱ ነው፡፡ አዲሱ መመርያ ያስፈለገበት ዋነኛ ምክንያት የመንግሥትን የበጀት ጉድለት ለመሸፈን መሆኑ ታውቋል፡፡

via - reporter