Get Mystery Box with random crypto!

አይኤምኤፍ የኢትዮጵያን የ2023 ምጣኔ ሀብት ትንበያ ወደ 5.3 በመቶ ዝቅ አደረገ። የዓለም አ | ሰሌዳ | Seleda

አይኤምኤፍ የኢትዮጵያን የ2023 ምጣኔ ሀብት ትንበያ ወደ 5.3 በመቶ ዝቅ አደረገ።

የዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (አይኤምኤፍ) እ.ኤ.አ. የ2023 የኢትዮጵያ ምጣኔ ሀብት 5.7 በመቶ እንደሚያድግ ተንብዮ የነበረ ቢሆንም፣ ትላንት አዲስ ባወጣው የዓለም ምጣኔ ሀብት ዳሰሳ ሪፖርት ትንበያ በ0.4 ቀንሶ 5.3 በመቶ አድርጓል፡፡  

አይኤምኤፍ በአዲሱ ሪፖርቱ ለኢትዮጵያ ያስቀመጠው ትንበያ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው አገሮች በ2023 ያድጋሉ ብሎ ካስቀመጠው ትንበያ ጋር እኩል ነው፡፡ በሚያዝያ ወር 2014 ዓ.ም. ላይ አስቀምጦት የነበረው ትንበያ ግን ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው አገሮች ካስቀመጠው 5.6 በመቶ ዕድገት የሚበልጥ ነበር፡፡

ትናንት የወጣው ሪፖርት የኢትዮጵያ ምጣኔ ሀብት ዕድገት ትንበያው ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ተብለው ከተዘረዘሩት ሰባት አገሮች የኢኮኖሚ ዕድገት ትንበያ ጋር ሲነፃፀር፣ ሦስተኛ ደረጃ ላይ መቀመጥ የሚችል ነው፡፡ ከታዳጊ አገሮች ከፍተኛውን ዕድገት እንደሚኖራት የተተነበየላት ዲሞክራሲያዊት ሪፐብሊክ ኮንጎ ስትሆን፣ የተተነበየው ዕድገት 6.7 በመቶ ነው፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት የተጠናቀቀውን የ2014 በጀት ዓመት ሲጀምር፣ የአገሪቱ ምጣኔ ሀብት በ8.7 በመቶ ያድጋል የሚል ግምቱን አስቀምጦ የነበረ ቢሆንም፣ በበጀት ዓመቱ ማጠናቀቂያ ይኼ እንደማይሳካ አስታውቋል፡፡ የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሺዴ ግንቦት 30 ቀን 2014 ዓ.ም. የ2015 አጠቃላይ በጀትን ሲያቀርቡ፣ የ2014 በጀት ዓመት ዕድገት ከሰባት በመቶ የዘለለ እንደማይሆን ተናግረው ነበር፡፡

via - reporter