2021-12-01 16:36:27
ኢትዮጵያ እንደ ርብቃ በሆድዋ ያሉ ልጆችዋ እየተዋጉባት "እንዲህ ከሆነ ይህ ለእኔ ምኔ ነው?" ብላ እየጮኸች ነው:: ለእናት ልጆችዋ ቢጋደሉላት ምን ይጠቅማታል? ሟቹም ልጅዋ ገዳዩም ልጅዋ ነውና ከመቁሰል በቀር ምንም አታገኝም:: ዳዊት ልጁ አቤሴሎም ሌላ ልጁን አምኖንን በገደለ ጊዜ ያለቀሰውን ለቅሶ ኢትዮጵያ ታለቅሳለች:: በዚህ መካከል ምስኪኑ ወገናችን ይረግፋል:: እጅ እጁን ሲቆርጥ ደስታና ፉከራ የለም:: ብንችል በዚህ ሰዓት በጸጸት እንጸልይ:: ካልቻልን ደግሞ ቢያንስ ዝም እንበል:: የሀገርን ሰላም የምትፈልጉ ሁላችሁ ከሩቅ በለው በለው ማለት ትታችሁ ማረን ማረን በሉ::
በሩቅ ሆነን አይነካንም ብለን እየፎከርን በምስኪኑ ላይ እሳት የምናነድ አንሁን:: በወገን ሞት ተደስተን እንደባዕድ ሀገር ጦርነት የድል ዜማ ብናዜም እግዚአብሔር ከሰማይ ሆኖ ይፈርድብናል::
ከራሳችን በላይ ሌላ ጠላት የለንምና ጌታ ሆይ ከራሳችን አድነን:: ኢትዮጵያ እጅዋን ወደ እግዚአብሔር መዘርጋት ትታ ራስዋ ላይ ቃታ የሳበችበት ዘመን ላይ ደርሰናል:: ጌታ ሆይ በዓይነ ምሕረትህ ተመልክተህ እኛው ያነደድነውን እሳት አብርድልን:: በትግራይ በአማራ በኦሮሚያ ያሉ በዚህ እሳት ዙሪያ የሚማገዱ ወገኖቻችንን ከጥፋት ይጠብቅልን:: በግራም በቀኝም የተሰለፉት በድህነት የሚኖሩ አንድ ውኃ የጠጡ የኢትዮጵያ ልጆች ናቸው:: አባቶቻቸው ሳይለያዩ አብረው ከብዙ ጠላት ጋር ታግለው ባቆዩአት መሬት ላይ ወንድማማቾች ጦር እየተሳበቁ ነውና በቸርነትህ ልባቸውን አራራ:: ወንድምን ገድሎ እንደ ቃየን ከመቅበዝበዝ በቀር ትርፍ እንደሌለ አሳያቸው:: ጠግቦ በልቶ ሳያድር ተመስገን ማለትን ያልተወ ሕዝብህን ጌታ ሆይ በምሕረትህ አድነው::
ዲያቆን ሄኖክ ሀይሌ
4.4K viewsJo_si Amor, 13:36