2022-03-28 08:24:33
"ጾምን አጋመስነው አትበሉ" ገብረ እግዚአብሔር ኪደብዙ ሰዎች ደስ ተሰኝተውና እርስ በእርሳቸው፡- ግማሹን ጾም ፈጽመናል፤ የጾሙ እኩሌታ አለፈ ሲባባሉ ተመልክቻለሁ፡፡
እኔ ግን እነዚህ ሰዎች በዚሁ ምክንያት ደስ ሊላቸው እንደማይገባ እመክራቸዋለሁ፤ የጾሙ እኩሌታ ማለፉን ሳይኾን የኃጢአታቸው እኩሌታ መኼዱን መወገዱን ያስቡ፤ እንደዚያ ከኾነም ሐሴት ያድርጉ፡፡
ደስ ልንሰኝበት የተገባው ነገር ይኼ ነውና፡፡ ሊታይ የሚገባው ይኼ ነው፤ ጥንቱም እነዚህን ኹሉ ነገሮች የምናከናውናቸው ስሕተቶቻችንን እንድናስተካክል፣ ጾሙ ሲጀምር እንደ ነበርንበት ሳይኾን እንድንነጻበት፣ ክፉ ልማዶቻችንን ወደ ጎን አድርገን የተቀደሰውን በዓል በዓለ ትንሣኤን እንድናከብር ነውና፡፡
እንደዚህ ካልኾነ ግን ጾሙን መጨረሳችን በራሱ ለእኛ ታላቅ ጉዳትን ይዞ ከመምጣት ውጪ ሌላ ምንም ረብ ጥቅም አይሰጠንም፡፡
ስለዚህ ብዙ ጊዜ መጾማችንን ብቻ አንመልከት፤ ይህ ምንም ትልቅ ነገር አይደለምና፤ ይልቁንስ በዚህ ጾም ራሳችንን አሻሽለን እንደ ኾነ፣ ጾሙ ከተፈታ በኋላም የዚሁ ፍሬ ጎምርቶ ይታይብን እንደ ኾነ ሐሴት እናድርግ፡፡
የክረምት ጥቅሙ ይበልጥ የሚታወቀው ወራቱ ካለፈ በኋላ ነውና፡፡
የዚያን ጊዜ የአበባው ማበብ፣ የአዝመራው ማፍራት፣ ሌሎች ዕፅዋትም በቅጠላቸውና በፍሬያቸው በወርሐ ክረምት ያገኙትን ጥቅም ግልጽ አድርገው ይናገራሉና! በእኛም ዘንድ ልክ እንደዚህ ይኹን፡፡
በወርሐ ክረምቱ በብዛትም በዓይነትም የተለያየ ዓይነት የዝናብ ጠብታዎችን ተቀብለናል፤ ብዙ ተከታታይ ትምህርቶችን ተምረናል፤ መንፈሳዊ አዝርእት ተዘርተዉብናል፤ የቅምጥልነት እሾኽም ቈርጠን ጥለናል፡፡
ስለዚህ ጾሙ በተፈታ ጊዜ የጾሙ ፍሬ ይከብበን ዘንድ፣ ከጾሙ የሰበሰብናቸውን መልካም ነገሮችም ጾሙን ራሱን እናስታውሰው ዘንድ የሰማነውን ነገር አጽንተን በመያዝ እንትጋ።
በእንተ ሐውልታት፣ ፲፰፥፩-፪
2.0K viewsNatnael, 05:24