Get Mystery Box with random crypto!

#ካነበብኩት -3 «እናንተ ያመናችሁ ሰዎች ሆይ! በትእግስትና በሰላት ታገዙ።» | TEAM HUDA

#ካነበብኩት -3

«እናንተ ያመናችሁ ሰዎች ሆይ! በትእግስትና በሰላት ታገዙ።»
(አልበቀራህ:153)

ፍርሀትና መረበሽ ሲመጣብህ ወዲያውኑ ተነስና ስገድ፡፡ ነፍስህ ምቾትና እርጋታ ታገኛለች፡፡ ሶላትህን በተመስጦ እስከሰገድከው ድረስ ለውጥ እንደሚያመጣልህ ዋስትና ኣለው፡፡ ነቢዩ (ሲዐ.ወ) ችግር በሚያጋጥማቸው ጊዜ “ቢላል ሆይ! አዛን አሰማና ገላግለን” ይሉ ነበር፡፡

ሶላት የአይናቸው ብርሃን፣ የደስታቸው ምንጭ ነበር፡፡ የብዙ ደጋግ ሰዎችን የህይወት ታሪክ አንብቤያለሁ፡፡ ችግርና መከራ በመጣባቸው ጊዜ ቁርጠኝነታቸውና መንፈሰ ጠንካራነታቸው እስኪመለስላቸው ድረስ ተነስተው ይሰግዱ ነበር፡፡

ጦርነት ላይ እጅና እግር ሲደክም፣ ጭንቅላቶች ሲበሩ፣ ነፍሶች ከስጋ ሲለያዩ የፍርሀት ሰላት ይታዘዛል፡፡ በዚህ ወቅት ጥንካሬ የሚመጣው ከልብ በመነጨ ሶላት ብቻ ነውና፡፡
ይህ በበርካታ ስነልቦናዊ በሽታዎች የተጠመደ ትውልድ ስግደት እንዲፈፅምና የአላህን ደስታ እንዲያገኝ ወደ መስጊድ መመለስ አለበት፡፡ ይህ ካልሆነ ኣይናችን በእንባ ይታጠባል፤ ልባችን በሀዘን ይቃጠላል፡፡

አምስት ወቅት ሶላቶችን በደንብ ከሰገድን ጌታችን ለሃጢያታችን ምህረቱን፣ ከጸጋዎች ሁሉ ትልቁን፣ ከደረጃዎች ሁሉ ከፍተኛውን ይሰጠናል፡፡ ሶላት ጥሩ የህመም ማስታገሻ ነው፡፡ ምክንያቱም በልብ ውስጥ እምነትን ያንቆረቁራል፡፡ ከመስጊድና ከሶላት የራቁ ሰዎች ህይወታቸው በሀዘንና በምሬት የተሞላ ነው፡፡

“ለነሱ ጥፋት ተገባቸው፤ ስራዎቻቸውንም አጠፋባቸው፡፡” (47፡8)

“ለኛ በቂያችን አላህ ነው፤ ምን ያምር መጠጊያ::” (3፡173)

ጉዳዮችህን ለአላህ ብትሰጥ፣ ወደሱ ብትጠጋ፣ ቃል የገባቸውን ነገሮች ብታምን፣ ባዘዘው ነገር ብትደሰት፣ እሱን ብትወድና እርዳታውን በትዕግስት ብትጠብቅ ትላልቅ የኢማን ፍሬዎችን ትቀጥፋለህ፤ የአማኞችን ደጋግ ባህሪያት ትይዛለህ፡፡ እነዚህን ጥሩ ነገሮች ወዳንተ ስታመጣ የወደፊቱን በተመለከተ ሰላም ታገኛለህ፡፡ ምክንያቱም ሁሉንም ነገር ለፈጣሪህ ትሰጣለህ፡፡ ውጤቱም እንክብካቤ፣ እገዛ ፣ ጥበቃና ድል ማግኘት ይሆንልሀል፡፡

ነቢዩ ኢብራሂም አለይሂ ሰላም እሳት ውስጥ በተደረጉ ጊዜ “ለኛ አላህ በቂያችን ነው፤ ምን ያምር መጠጊያ' አሉ፡፡ ከዚየም አላህ እሳቷን ቀዝቃዛ፣ ምቹና ሰላማዊ እንድትሆን አደረገላቸው፡፡
ነቢዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) እና ባልደረቦቻቸው በጠላቶቻቸው አደገኛ ጥቃት በተቸገሩ ጊዜ ከዚህ አንቀፅ ጋር ተዛማጅ የሆኑ ቃላትን ነበር የተናገሩት፡፡

« በቂያችንም አላህ ነው፤ ምን ያምር መጠጊያ። ከአላህም በሆነ ፀጋና ችሮታ ክፉ ነገር ያልነካቸው ሆነው ተመለሱ። የአላህንም ውዴታ ተከተሉ። አላህም የታላቅ ችሮታ ባለቤት ነው።»
(አል ኢምራን:173-174)

የደረሰበትን ችግር በራሱ የመመለስ ችሎታ ያለው ሰው የለም። ምክንያቱም የሰው ልጅ የተፈጠረው ደካማና ልፍስፍስ ሆኖ ነው። ሆኖም በችግር ወቅት ሙዕሚን ሰው እምነቱንና መመካቱን በጌታው ላይ ይጥላል። ይህ ሲሆን ሁሉም ችግሮች ሊወገዱ እንደሚችሉ ያውቃልና፡፡

“ምዕመናን እንደሆናቹሁ በአሏህ ላይ ተመኩ::”
(5:23)

ለራሳችሁ ታማኝ ለመሆን የምትመኙ ሰዎች ሁሉ ከችግርና ከአደ ጋ ሊጠብቃችሁ በሚችለው በሀያሉ ጌታ ላይ ተመኩ፤ ህይወታችሁን በዚህ መርህ ኑሩ- ለኛ አላህ በቂያችን ነው፡፡ ምን ያምር መጠጊያ፡፡

_____

ተሕዘን ከሚለው የዶክተር ዓዒድ አልቀርኒ መፅሐፍ የተወሰደ! [በአማርኛው የምን ሐዘን በሚል በእህት ሐዲያ ሙሐመድ ተተርጉሟል!]

@Re_Ya_Zan