Get Mystery Box with random crypto!

#ካነበብኩት... - 4 የቢላል የጥንካሬ ምንጭ ምን ነበር? ሚሥጥሩ ከአንዲት ሀሳብ የተቀዳ | TEAM HUDA

#ካነበብኩት... - 4

የቢላል የጥንካሬ ምንጭ ምን ነበር?

ሚሥጥሩ ከአንዲት ሀሳብ የተቀዳ ነዉ፡፡ የሰዉ ልጅ እኩል ነዉ የሚለዉ የነብዩ ሙሃመድ (ሰዐወ) መልእክት ድንገት ሲወራ ሰምቶ ነዉ፡፡ ከመጤፍ የማይቆጠር ማንነቱ ክብር እንዳለዉ የሚናገር ሰዉ መልእክት ሲሰማ ወዲያዉ ከዉስጡ ተዋሃደ፡፡ ለአመታት በባርነት የገረደዉን ኡመያ ከልቡ ጠላ፡፡ በአረቢያ ስለሚሰማዉ አዲስ እምነት ጥበባትም ልቡ ተዘነበለ፡፡

"አስተዉል"

የተልፈሰፈሰ ወኔ ነበረዉ፡፡ ኡመያን ሲበዛ ይፈራዋል፤ ቁጣው ሁለመናዉን ነበር የሚያናጋበት፡፡ አሁን ግን እንደኡመያ የሚንቀዉ ሰዉ አልነበረም፡፡
ስለሰዎች እኩልነት የሚያዉጀዉን አዲስ አብዮት ከልቡ ተቀበለ፡፡ ስለመቀበሉም ዑመያ ሲሰማ እጅግ በንዴት ናረ፡፡ እንደወትሮዉ በፍርሃት ካባ ተጀቡኖ እየተንቀጠቀጠ ይጠብቀኛል ብሎ ቢያስብም ቢላል ልበ-ሙሉ እንደሆነ ቆመ፡፡ እንግዳ ነገር ያየዉ ዑመያም ተደናበረ፡፡

ትኩር ብሎ አየዉ፤ በቢላል ፊት ላይ ግን አንዳች ለዉጥ ሳይታይ ቀረ፡፡ ስለሰብዓዊ ዘሮች እኩልነት የሚያስተምረዉን የረሱል (ሰ.ዐ.ወ) ጥበበ-ብርሃን መቀበሉን ሳያመነታ ነገረዉ፡፡ ቀና ብሎ ለማየት እጅግ ይንቀጠቀጥ የነበረዉ ቢላል ዑመያን ፊት ለፊት እያየ በዉስጡ ስለያዘዉ አዲስ ማንነት ሳይደብቅ ገለጠለት፡፡ ይህም እጅግ የከበደ ቅጣት አስከተለበት፡፡ ከ40 ዲግሪ ሙቀት በሚልቀዉ የአረቢያ አሸዋማ ሜዳ ላይ የገዘፈ አለት ሆዱ ላይ በመጫን ዑመያና ግብረ አብሮቹ ይገርፉት ጀመር፡፡ የግርፋቱ ምክንያት አዲስ የተቀበለዉን አስተሳሰብ (እምነት) እንዲተዉ ነዉ፡፡ ቢላል ግን ፍጹም አዲስ ሰዉ ሆነባቸዉ፡፡

ለብዙ ሆነዉ ከሚገፉት አለት በላይ የጠነከረ አቋም ያዘባቸዉ፡፡ የግርፋታቸዉ መጠን ሲጨምር የርሱም አቋም ይበልጥ እየጠነከረ መምጣቱ ግራ አጋባቸዉ፡፡ በመጨረሻም መግረፋቸዉ ሲያደክማቸዉ ከበረሃዉ ድንጋይ ሆዱ ላይ እንደጫኑበት ጥለዉት ሄዱ፡፡ ሲመለሱም ግን አቋሙን አልቀየረም፡፡

አዲስ በገነባዉ የዉስጥ ማንነቱ ጠነከረ፡፡ በየትኛዉም ዉጫዉ ተፅዕኖም ላይቀረይዉ ጸንቶ ቆየ፡፡ በመጨረሻ ከሞት ተርፎ ነጻ ወጣ፡፡ በዓለም የኢስላም ታሪክ ቀዳሚዉ የአፍሪካ ጥቁር የነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) ሙዓዚን በመሆን በወርቃማ ብዕር የታሪክ ቅጽ ላይ ሰፈረ፡፡

*

ዉጫዊ ማንነታችን ያድጋል ግን መሰረታዊ መልኩን አይለዉጥም፡፡ ከልጅነት ወደ እርጅና ጊዜ ጠብቀን እናዘግማለን፡፡ የመልካችን መሰረተ ምስል ግን ይታወቃል፡፡ በዚህ የአካላዊ (ባዮሎጂካዊ) ማንነታችን የምንፈጥረዉ ተፅዕኖ የለም፡፡ እንደተወለድን እናድጋለን፡፡ አንደግ ብንል ፈቃድ የለንም፤ ሞትም በመጣ ጊዜ አንሙት ብንል አንችልም፡፡ ሙሉ ነጻነት ያለን በዉስጣዊ ማንነታችን ላይ ነዉ፡፡

ደካማዉን ስብዕና ማጠንከር ይቻላል፡፡ ሰነፉን ማንነት ማጎበዝ ይቻላል፡፡ የሰዎች ስኬታማነት በዉጫዊ ገጽታቸዉ (አካላዊ ቅርጻቸዉ) አይወሰንም... በዉስጣቸዉ በሚገነቡት ጠንካራ መንፈስ እንጂ፡፡ ዉስጣችን እንዲጠነክር በፈተናዎች መከበብ አለበት። ምቾት ባለበት ሜዳ ጥንካሬ አይኖርም፡፡ ችግሮች ናቸዉ ወደ ምቾት ወይም የስኬት ከፍታ የሚያወጡን፡፡

____

በወንድም ሙሐ
መድ አሊ ቡርሐን ከተፃፈው የስኬት ፈለግ ቁጥር አንድ መፅሐፍ የተቀነጨበ

@Re_Ya_Zan