Get Mystery Box with random crypto!

የዒድ ውሎ - [በእውነተኛ ታሪክ ተመርኩዞ የተፃፈ] : (ᴛᴇᴀᴍ ʜᴜᴅᴀ) . የአመቱ ምርጥ ቀን ኢ | TEAM HUDA

የዒድ ውሎ - [በእውነተኛ ታሪክ ተመርኩዞ የተፃፈ]
:
(ᴛᴇᴀᴍ ʜᴜᴅᴀ)
.
የአመቱ ምርጥ ቀን ኢድ ለመንጋቱ ማስረጃ የሱብሒ አዛን ከአቅራቢያችን መስጂድ ተሰማ። 'አስማ' ውድ ልጄንና ባለቤቴን ከቀሰቀስኩ በኋላ ወደመታጠቢያ ቤት ገባሁ። ተጣጥቤ ከሰገድኩ በኋላ የልጅነት ማስታወሻዬን ለአፍታ ስከፍት የያዘኝ ከሕፃንነቴ በአንዱ ያሳለፍኩት የአረፋ ውሎዬን የከተብኩበት ገፅ ነበር።

*
*
አርብ 16/02/2005

ቤቱ ውስጥ በሚሰማው ጫጫታ ብቻ የኢድ ቀንን የሚለይ ሰው ካለ እኔ ነኝ። ኢድ ለኔ የአዘቦት ቀን ነው። ከተራው ቀን የሚለየው በብዛት ፎቶ በመነሳቴ ብቻ ነው። ካለንበት የወንዶች ክፍል በተቃራኒ ያለው የሴቶች ማደሪያ ክፍል ከወትሮው በተለየ ይናወጣል።

<<ሒጃቤን የት አደረጋችሁት?>>
<<ጫማው አንድ እግሩ የለም!>>
<< ለእናት ሐፍሳ ነው የምናገረው የእጅ ጌጤን ሰበራችሁት።>>
ሁሉም ያለ መሰማማት ይጮሀል። ኢድ እስክንሰግድ እንጂ ከዛ በኋላ ቀና አሳቢ መሳዮች ሲዘይሩን በተራቸው እነሱ ያውኩያ እኛ ተመልካች እንሆናለን። እዚህ ማሳደጊያ አራት ወንዶች ና ሰባት ሴቶች አለን። እናት ሐፍሳ የሁላችንንም መሻት ለመሙላት ትጥራለች። እጅ አጥሯት ስታዝን ሳይ ምነው ኢድ ባልኖረ እላለሁ። ልጆቿም ለመመፃደቅ ካልሆነ ዞር ብለው አያዩንም እንዲያም ሆኖ እናታችን ናት።

የወንዶች መሔጃ ባስ ሲመጣ ከሴቶቻችን ጋ መለያየት ግድ ሆነ። እስከ መሐል ከተማ በባስ ሔደን ከዛ ተልቢያ እያልን በእግር ጉዞ ጀመርን። አትዋሽ አትበሉኝና ከኢድ ብቸኛው የሚስበኝ ቦታ ይሔ ነው። የሙት ልጅ ሳልባልና ከንፈር ሳይመጠጥልኝ ከሰው እኩል ተስተካክዬ 'አላሁ አክበር' የምልበት።
የኢድ ሰላትን ከሰገድን በኋላ ኹጥባ ለማድመጥ ዘግየት አልን። ዙሪያዬን ቃኘሁ እንደተለመደው ሁሉም ኹጥባውን ትቶ ወደቤቱ መሽቀዳደም ያዘ።
<<እርድ ስላለባቸው ነው ኮ ዩሱፌ>> ይለኛል ታላቅ ወንደሜ ሐሰን። የሚያርዱትም ባይኖር መሔዳቸው አልቀረ። ኹጥባውን አድምጠን ወደ ባሳችን ተመለስን።
<< እናት ሐፍሳ ደውላ ነበር። ቤት ደርሰው በዛው ከነፈትሑዲን(የእናት ሐፍሳ የመጨረሻ ልጇ ነው) ጋር ይመጣሉ።>> ሲል የሁላችንም ታላቅ የሆነው ሐምዛ ነገረን። እናት ሐፍሳና ቤተሰቦቿ እስኪመጡ ቤት(ማሳደጊያው ውስጥ) ያዘጋጀነውን ዳቦ አቅርበን አፈጠርን።

ግቢ ተንኳኳ። ቀኑን ሙሉ እንዴት አረፈዱ ስንል የጠበቅናቸው ዘያሪዎቻችን... ከፊት ያለው ሰልፊ ስቲኩን ይዞ ቀድሞ ገባ። ሌሎቹ ዳቦ ለስላሳና ሌሎች ነገሮችን ተሸክመዋል። ሴቶቹ በእናት ሐፍሳ በኩል ሲደረደሩ ወንዶቹ ያለችን አዳፋ ሶፋ ላይ ተደረደሩ። ከኛ ይልቅ እነሱ የተራቡ ይመስላሉ። ገና ከመግባታቸው ሱፍራ ዘርግተው ምግቡን በሰሐን ካቀራረቡ በኋላ መብላት ጀመሩ። የረሐብ ስካራቸው ሲበርድ ካመጡት ለስላሳ ያስቀሩትን በአይኔ ቃኘሁ። ሶስት ያልተከፈተ ና አንድ የተጀመረ ጠርሙስ። ግቢውን ከፍቼ ወጣሁ። በሩ ላይ የመመገቢያ አዳራሽ ይል እንደሁ ብዬ። የለም!
የእናት ሐፍሳ ማሳደጊያ እንደሆነ የሚገልፀው ወረቀት ከዝናብ ብዛት በስብሶ ቀለሙን ለቋል። ሌላ የለም!

ተመልሼ ስገባ በር ላይ ሐምዛን አገኘሁት።
<<የሆነ ነገር ፈልገህ ከሆነ ብዬ ነበር። ለምንድነው የወጣኸው ዩሱፍ?>>
<<ስማማ ወንድሜ ሐምዛ፣ የኛ ቤት ኢድ ኢድ ላይ ብቻ የመመገቢያ አዳራሽ ይሆናል እንዴ? ለምን ቤታቸው አይበሉም?>> አይኑን እያየሁ ጠየቅኩት። የሴቶቹ ሳቅ ሙሉ ግቢውን እያወከ ስለነበር ወደአንድ ጥግ ጎተት አድርጎኝ እንዲህ አለኝ
<<ስማ ዩሱፍ ገና የአስራሁለት አመት ልጅ ነህ። ይህን ሰዎች የሚያደርጉት መልካም አስበው እንደሆነ ብቻ እወቅ እሺ። ደሞ እንግዶቻችን ፊት እንዲህ ብትል...ዋ! እናት ሐፍሳ ታዝንብናለች። በል ና እንግባ።>> እጄን ይዞኝ ወደ ቤት ገባን። ስንገባ ግን ጭራሽ ቪዲዮ ላይ ናቸው፣ የስልኩ ፍላሽ (መብራት) አህላም ላይ እየበራ ስለነበር እንባዋ ይፈሳል። የsolar አለርጂኳ እንደተነሳ ስለገባኝ እንደምንም እያራመድኳት ወደ መኝታ ክፍል ገባሁ። የዛሬ አመት በር ላይ ተጥላ ካገኘኋት ጀምሮ እየተባባሰ የመጣ የአይን ሕመም አለባት። በጠብታ እያስታገስን ነው እስካሁን ያቆየነው። እንቅልፍ ሸለብ ሲያደርጋት ወደ ሳሎን ተመልሼ መጣሁ። ሊወጡ አካባቢ ነው መሰለኝ፣ የመጨረሻ ፎቶ ብለው ደረደሩንና አበሩብን። የባለካሜራውን እጅ ነክሼ ተመልሳችሁ አትምጡ ማለትን ወደድኩ። ተንኮሌ የገባው ሐሰን በአይኑ ጎሸም ባያረገኝ ኖሮ...!

እናት ሐፍሳ ልቧ ቀና ነው። እስከበር ድረስ የምስጋና ናዳ እያወረደች ከሸኘቻቸው በኋላ የበሉበትን የሰሐን ክምር ከሴቶቹ ጋር ለማጠብ ወደጓሮ ሔደች። ወንዶቹ ደሞ እንደ ፈረቃችን ቤቱን ስንጠርግ መግሪብ ደረሰ። ከሐሰን ጋ ወደ መስጂድ ወጥተን ስንመለስ እንዲህ አለኝ፦
<<ሰዎች ሶስት አይነት ናቸው። እንደ እናት ሐፍሳና እንደቅድሞቹ ወንድሞቻችን እና እንደሌሎቻችን። ሳይኖራቸው ግን የሚሰጡ፣ ቢኖራቸውም ለመስጠት ወደ ኋላ የማይሉ አሉ። ኖሯቸው ደሞ ሲሰጡ የሚሳሱ ና ለታይታ የሚቸሩም አሉ። ተራርፏቸው ግን አላህ በቀልባቸው የመስጠትን ኒእማ ስለነፈጋቸው ብቻ የማይሰጡም አሉ። አንተ ታዲያ አርአያ የምታደርገው አላህ የሚወደውን እንጂ ስላደረሱብህ ለመበቀል የሚያነሳሱህን አይደለም። ገብቶሀል አይደል?>>
<<አዎ እንደእናት ሐፍሳ እሆናለሁ። ትልቅ መኪና እገዛላትና እንደኛ አይነቶቹን ሰብስቤ እንደእናታችን እንዲሆኑ መክራቸዋለሁ።>> ከልቤ ደስ እያለኝ ነበር ያልኩት። ሊመፃደቁ እጃቸውን ሲዘረጉላቸው ላዘኑት መፅናኛ ሆናለሁ።
*
*
*
<<አልሐምዱሊላህ ለዚህ ላደረስከኝና ቃሌን ሞልቼ የእናት ሐፍሳን ማሳደጊያ እንዳስፋፋ ለረዳኸኝ>> ከማለቴ ባለቤቴ ወዳለሁበት ተጠግታ <<ዩሱፌ እናት ሐፍሳ አንተን በማሳደጓ አትርፋለች>> ስትል ግንባሬን ሳመችኝ።

ኢድ ሙባረክ በድጋሚ

@Re_ya_zan