ሐጀተል ወዳእ (የመሰናበቻው ሐጅ) . . ᴛᴇᴀᴍ ʜᴜᴅᴀ . በወርሀ ዙልሒጃ ከሚነሱ እውነታዎች አንዱ የሆነው የኢስላም አምስተኛው ማእዘን ሐጅ ነው። በነብዩላህ ኢብራሂም አለይሒሰላም እና በልጃቸው ኢስማኢል አማካኝነት በተገነባው ካእባ ዙሪያ የሚደረግ አምልኮ! የቆዳ ቀለም፣ ፆታ፣ ጎሳ፣ ብሔር፣ የሰውነት ገፅታ ሳይለያያቸው አቤቱ ጌታችን የሚሉበት የእኩልነት ማሳያ ኢባዳ! ወቅቱ አስረኛው አመተ ሒጅራ ወርሀ ዙልቃኢዳ ሐያ ስድስተኛው ቀን ቅዳሜ ነበር። ረሱሉ ሰለላሁ አለንሒ ወሰለም በይፋ ለሐጅ መነሳታቸውን ካወጁ በኋላ የመዲና ነዋሪዎች (የቻሉት በሙሉ) ከረሱሉ ሰለላሁ አለይሂ ወሰለም ጋር በመጣመር ስንቃቸውን ቋጥረውና ለጉዞ ተዘገጃጅተው ወደ መካ ጉዞ ጀመሩ። አቡበከር አስሲዲቅ እየመሩ በዘጠነኛው የሒጅሪያ አመት ወደ መካ ካቀኑ በኋላ ቀጣዩ የጉዞ ቅፍለት መሆኑ ነው። እኚህ መቶ ሺህ የሚደርሱ አስሐቦች ገላቸውን ተጣጥበውና ሐርመው (ኢህራም አድርገው) ጉዞ ተጀመረ። ረሱሉ ሰለላሁ አለይሒወሰለም ውድ ግመላቸው የሆነችው ቀስዋህ ላይ ከወጡ ጀምሮ መዲና በተልቢያ ተናወጠች።