Get Mystery Box with random crypto!

ከዚህ በታች የሰፈረው ሃሳብ በአጤ ኃይለሥላሴ የሥልጣን ዘመን ስለአማራ ቀጣይ እጣ ፈንታ ለመወያየት | ሽፈራው የሶማው

ከዚህ በታች የሰፈረው ሃሳብ በአጤ ኃይለሥላሴ የሥልጣን ዘመን ስለአማራ ቀጣይ እጣ ፈንታ ለመወያየት ጉምቱ የኃይለሥላሴ ባለስልጣናት በድብቅ ተሰባስበው ነበር፤ በስብሰባቸውም ደጃዝማች ፀሐዬ የተናገሩት ሀሳብ እንደ ነብይ ያስቆጥራቸዋል። ዛሬም ድረስ በዛውን ወቅት ለተነሳው ሀሳብ መፍትሔ የሚያበጅ የአማራ ሊህቅ አልተገኘም።

ሀሳቡ ይሄ ነው፦

"የዐፄ ኃይለሥላሴ ዙፋን መዝመሙ በብዙኃኑ እየታወቀ የመጣው ፲፱፻፷ ዓ.ም ጀምሮ ነው። ለዚህ ዋና ምክንያቱ ደግሞ የጸሐፌ ትእዛዝ ወልደጊዮርጊስን አይነት በውስጥ አስተዳደር የተካነ፣ ችግር አስቀድሞ አነፍንፎ ብልሃት የሚያበጅ ባለመገኘቱ ነበር። ጸሐፌ ትእዛዝ አክሊሉ ሀብተወልድ የተለመደውን የጎንዮሽ አሠራር አያውቁበትም፣ የሚፈልጉትም አልነበሩ።

ስለዚህ ከባህሉ ጋር የሚሄድ ዘዴ በመፍጠር ለችግሮች መፍትሔ ማቅረብ አልቻሉም። በዚህ ምክንያት የኢትዮጵያን ችግር አንድ አድርጎ የሚሰፋ አንድ ብልህ መሪ ታጣ። ይህ ሁኔታ ያሳሳባቸው የመንግሥት ባለሥልጣኖች ችግሩን ለመፍታት የሰው ለውጥ እንደሚያስፈልግ ማሰብ ያዙ። እየተባባሰ የሄደውን የፖለቲካ ትኩሳት ለማብረድም ለጊዜው አክሊሉ ሀብተ ወልድን በይልማ ደሬሳ ለመተካት ዐቀዱ፡፡ ጃንሆይ ግን ፈቃደኛ ባለመሆናቸው አክሊሉን በይልማ ደሬሳ የመተካቱ ሐሳብ ቀረ፡፡ በዚህ ዓይነት መፍትሔ ለማምጣት የሚደረገው ጥረት የማይሳካ መሆኑ እየታየ በመሔዱ ቀስ በቀስ የባለሥልጣኖቹ ስብስብ (መንዜ፣ መራ ቤቴ፣ ቡልጋ እየተባባለ) እየተቧደነ
መከፋፈል ጀመረ፡:

በዚሁ ወቅት የአክሊሉ ሀብተ ወልድ ሥልጣን አሠራር መንግሥትን አደጋ ላይ ይጥላል ብለው ይሠጉ ከነበሩት መካከል አንዱ ደጃዝማች ፀሐዩ ዕንቁ ሥላሴ በተለይ አንዳንድ አስተያየታቸውም ይታወቅ ነበርና እንደ አፈንጋጭ ይታዩ ነበር፡፡ ለዚህ ይመስላል በ፲፱፻፷፭ ዓ.ም. መጀመሪያ አካባቢ የጎንደር ተወላጅ የነበርነውን አቶ ዳኘው (ኋላ አምባሳደርና የጐንደር ጠቅላይ ግዛት አስተዳዳሪ፣ ኮሎኔል ሞላልኝ በላይ ኋላ የጐጃም ክፍለ ሀገር አስተዳዳሪን እና እኔን (የኦጋዴን ልማት ዋና ሥራ አስኪያጅ) አዲስ አበባ ቀጨኔ መድኃኔ ዓለም መንገድ ላይ ካለው ቤታቸው ከተመረጡ አስተናጋጆች ውጪ ማንም በሌለበት ጋበዙን፡፡

ተጋባዦች የተመረጥነው ከኋላችን የአካባቢዎቻችን ድጋፍ እንዳለን ግምት ውስጥ በማስገባት ነበር፡፡ ድግሡ የተሟላ ሆኖ ግብዣው የተደረገበት ዋና ጉዳይም የአማራውን ሕዝብ ለማስተባበር እንድንሠራ ነበር፡፡
ደጃዝማች ፀሐዩ ‹‹ከእንግዲህ ወዲህ ማንም ቢመጣ ተነሳሁ የሚለው አማራው ሕዝብ ላይ እንጂ ለይቶ የሸዋ፣ የጐንደር፣ የጐጃም አይልም፡፡ እኛም ወደድንም ጠላንም የአማራው አንገት አንድ መሆኑን ማወቅ አለብን፡፡ ስለዚህ አማራው መተባበር አለበት›› አሉን፡፡ በዕለቱ በጉዳዩ ላይ ከተነጋገርን በኋላ እኛም የምንችለውን እንደምናደርግ ተስማምተን ተለያየን፡፡ መቼም በዚያ ወቅት ስለጉዳዩ በቀጥታ ያነጋገሩን ደጃዝማች ፀሐዩ ዕንቆሥላሴ ይሑኑ እንጂ ሌሎች ጎላ ጎላ ያሉ የሸዋ መኳንንቶችም በተገናኘንበት ጊዜ ሁሉ በዚሁ ጉዳይ ዙሪያ ያሻርቱን (ያባብሉን፣ ያግባቡን) ነበር። ለማንኛውም ይሄም ሐሳብ የትም የደረሰ አልነበረም፡፡"

ከገጽ 366 - 67
ማን ይናገር የነበረ...
የታህሣሡ ግርግር እና መዘዙ
ደራሲ፤ ብርሃኑ አሥረስ
አሳታሚ፦ አአዩ ፕሬስ