Get Mystery Box with random crypto!

የሶርያ ጦርነት 12 ዓመታትን አስቆጠረ (ረጅም ፅሁፍ) እንዴት ተጀመረ? መጋቢት 15 ቀን 2 | Our World

የሶርያ ጦርነት 12 ዓመታትን አስቆጠረ
(ረጅም ፅሁፍ)


እንዴት ተጀመረ?


መጋቢት 15 ቀን 2011 በሶርያ ዴራ፣ ደማስቆ እና አሌፖ ጎዳናዎች ላይ ከፍተኛ ብጥብጥ ተቀሰቀሰ፤ ተቃዋሚዎች ዲሞክራሲያዊ ለውጥ እንዲደረግ እና የፖለቲካ እስረኞች እንዲፈቱ ጠየቁ። ለተቃውሞ መቀስቀስ ምክንያት የሆነው ከጥቂት ቀናት በፊት በዴራ ከተማ ፕሬዝዳንት አል አሳድን ለማውገዝ አደባባይ የወጡ በአሥራዎቹ የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ወጣቶችን በማሰር እና በማሰቃየት ነበር።

ተቃውሞውን ተከትሎ በሶርያ መንግስት ከፍተኛ ርምጃ እና ጭቆና ተከተለ። እ.ኤ.አ. በሀምሌ 2011 ከሶርያ ጦር ኃይል የከዱ ሀይሎች መንግሥትን ለመገልበጥ ዓላማ ያለው የነፃ የሶሪያ ጦር መቋቋሙን አስታውቀው አመፁን ወደ እርስበርስ ጦርነት ለወጡት። እ.ኤ.አ. በ2012 ተቃውሞው የቀጠለ ሲሆን በዓመቱ በመላው አገሪቱ የተለያዩ አማፂ ቡድኖች ብቅ አሉ። በዚያው በ2013 አመት መጨረሻ ላይ የአይኤስ መነሳት በሰሜን እና በምስራቅ ሶሪያ እንዲሁም በርካታ የኢራቅን ግዛቶች በመውረር ፈተናው የሰፋ ሆነ።

ከአስራ ሁለት አመታት በፊት የሶርያ መንግስት ተቃዋሚዎች የሀገሪቱን ጎዳናዎች ላይ ደፍረው በመውጣት መንግስት እና ፕሬዚዳንቱን ባሽር አል አሳድን በመቃወም ነበር የእርስ በእርስ ጦርነቱ የተጀመረው። ተቃውሞዎቹ በፍጥነት አብዮታዊ ተፈጥሮን ይዘው “የአገዛዙን ውድቀት” ጠየቁ፣ ነገር ግን ከመንግስት ሃይለኛ ምላሽ በኋላ ህዝባዊ አመፁ ወደ ጦርነት ተቀየረ፣ ብዙ የውጭ ሃይሎችን እየጎተተ ሚሊዮኖችን አፈናቅሎ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ገደለ።

በጦርነቱ የተነሳ የሶሪያ ኢኮኖሚ እያሽቆለቆለ መጥቷል፣ አሁን ላይ 90 በመቶ የሚሆነው የሶርያ ህዝብ ከድህነት ወለል በታች እንደሚኖር የዓለም የምግብ ፕሮግራም መረጃ ያሳያል። የሶርያ ቀውስ ከተጀመረበት ከመጋቢት 2011 ጀምሮ በሀገሪቱ ከ306,000 በላይ ንፁሀን ዜጎች ወይም ከሶርያ ህዝብ 1.5 ከመቶ ያህሉ ተገድለዋል ሲል የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ባለፈው አመት ያወጣው አሃዛዊ መረጃ ያሳያል።

መቀመጫውን በዩናይትድ ኪንግደም ያደረገው የሶሪያ የሰብአዊ መብቶች ታዛቢ ቡድን በበኩሉ በጦርነቱ በአጠቃላይ የሟቾች ቁጥር ወደ 610,000 እንደሚደርስ ገምቷል። በየካቲት ወር ሰሜን ምዕራባዊ ሶሪያን ካወደመው የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋ በፊት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት 14.6 ሚሊዮን ሶሪያውያን ሰብአዊ እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው ገልጿል፣ 6.9 ሚሊዮን ሰዎች በአገር ውስጥ ተፈናቅለው የሚገኙ ሲሆን ከ5.4 ሚሊዮን በላይ የሶሪያ ስደተኞች በጎረቤት ሀገራት ተገን ጠይቀው ይኖራሉ። በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ በጀርመን እና በሌሎች የአውሮጳ ህብረት ክፍሎች እንዲሁም በሌሎች አካባቢዎች ጥገኝነት ጠይቀዋል።


በሶርያ የሚገኙ ተፋላሚዎች እነሆ እነማን ናቸው?

የሶሪያ ፕሬዝዳንት ባሽር አል አሳድ እ.ኤ.አ. ከ1971 ጀምሮ በስልጣን ላይ ከነበሩት አባታቸው ሃፌዝ አል-አሳድ ስልጣኑን ተረክበው ሀገር መምራት የጀመሩት በ2000 ዓመት ነበር። ሀገሪቱን በብረት መዳፍ በመምራት ተቃዋሚዎችን በማፈን የኬሚካል ጦር መሳሪያ በመጠቀም በሺዎች በማሰር እና በማሰቃየት ምዕራባውያኑ ክስ ቢያቀርቡባቸውም በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሶርያውያን ግን በደማስቆ ቤተመንግስት መቆየታቸው እንደሚያስደስታቸው ዳጉ ጆርናል ዘግቧል።

ነፃ የሶሪያ ጦር (FSA) ወይም የሶሪያ ብሔራዊ ጦር የሚባለው እ.ኤ.አ በ2011 ከሶሪያ ጦር በከዱ እና በቱርክ እንዲሁን በበርካታ የአረብ ሀገራት በሚደገፉ ሲቪሎች የተቋቋመ የታጠቁ ብርጌዶች ስብስብ ነው። እ.ኤ.አ. በታህሳስ 2016 ከአሌፖ ጦርነት ጀምሮ በሰሜን ምዕራብ ሶሪያ ውስጥ የኢድሊብ ውስን ቦታዎችን ቡድኑ እንደተቆጣጠረ እስካሁን ቆይቷል።

በጦርነቱ ሌላኛው ተፋላሚ ሀያት ታህሪር አል-ሻም (ኤችቲኤስ) ሲሆን ቀደም ሲል ጀብሃ ፈታህ አል ሻም ወይም ጀብሃ አል-ኑስራ ተብሎ ይጠራ ነበር። ጀብሃ አል-ኑስራ የአል-አሳድ መንግስት ተቃዋሚ ሲሆን የአልቃይዳ አጋር ሆኖ በ 2011 ተመስርቷል።በአሁኑ ጊዜ ይህ ኤች ቲ ኤስ የተሰኘው ቡድን "ማንኛውንም ድርጅት ወይም ፓርቲ የማይከተል ገለልተኛ አካል" መሆኑን ይገልፃል።

ሌላኛው የጦርነቱ ተዋናይ ሲሆን ሂዝቦላህ ሲሆን የሺአ የታጠቀ ቡድን ነው። ሂዝቤ በሊባኖስ እና በኢራን የሚደገፍ የፖለቲካ ሃይል ሲሆን የፕሬዝዳንት አል-አሳድን መንግስትን ለመደገፍ ወደ ሶሪያ የገባ ሀይል ነው። በአሁኑ ጊዜ በሶሪያ ውስጥ ምንም አይነት ግዛት አይቆጣጠርም።

የሶሪያ ዴሞክራሲያዊ ኃይሎች (ኤስዲኤፍ) ይህ ቡድን የኩርድ እና የአረብ ሚሊሻዎች ጥምረት ሲሆን የተመሰረተው በ2015 ዓመት ነበር።በአብዛኛው የYPG ተዋጊዎችን እና የአረብ፣ የቱርክ እና የአርመን ተዋጊዎችን ቡድኑ ያካትታል። ቱርክ ግዛት ገንጥሎ የኩርዶች ሀገር ለመመስረት የሚንቀሳቀሰው ይህው ቡድን ከ1984 ጀምሮ ከ40,000 በላይ ሰዎችን የገደለ የትጥቅ ዘመቻ ከአንካራ መንግስት ጋር አድርጓል።በኤስዲኤፍ ቁጥጥር ስር የሶርያ ዋና ዋና ከተሞች የሆኑት ራቃ፣ ኳሚሽሊ እና ሃሳኬህ የተሰኙ ከተሞች በቡድኑ እጅ ስር ይገኛሉ።

አይኤስ አይኤስ በውጭ ተዋጊዎች የተደራጀው ይህው ቡድን የመንግስት ስርዓት የፈጠረ እና በጠንካራ የማህበራዊ ሚዲያ እንቅስቃሴው ይታወቅ ነበር። ይህው ቡድን እ.ኤ.አ በ2014 በግምት አንድ ሶስተኛውን የኢራቅ እና ሶሪያን ግዛቶች ተቆጣጥሮ የነበረ ቢሆን ከ2019 ወዲህ ድባቅ ተመቷል።

በሀገራት ደረጃ የሩሲያ መንግስት ዋንኛው የደማስቆ አስተዳደር ደጋፊ ሲሆን ሞስኮ በአሁኑ ወቅት በሶርያ የጦር ሰፈር ገንብታ ከባሽር አላሳድ ጎን ትገኛለች።ኢራን በተመሳሳይ ከሶርያ ጎን ተሳፋለች።

ቱርክ የባሽር አላሳድ ወዳጅ የነበረች ቢሆንም በአመፁ መነሻ ወቅት ከአቋማ ተንሸራታ የዋይፒጂን ታጣቂዎች ለመውጋት በሚል የሶርያ ታጣቂዎችን በምድሯ እስከማስታጠቅ ደርሳ ነበር።አሜሪካ የደማስቆ መንግስት ከስልጣን እንዲነሳ ታጣቂዎችን በመርዳት በጦርነቱ ሚናዋ ከፍ ያለ ነበር።

ጦርነቱ በሶርያ በዩኔስኮ ከተመዘገበችው የቤልና የባአል ሻሚ ቤተመቅደሶች መገኛ ፓልምይራ ከተማ እስከ ቱርክ ድንበር የምትጋራውን ኢድሊብን አፈራርሷል።በነዳጅ ሀብቷ ዝነኛ ከነበረችው ዴር አዝ ዞር ከተማ አንስቶ በኤፍራጥስ ወንዝ ላይ የተመሰረተችውን ራቃን 80 በመቶ መሰረተ ልማት አውድሟል።የሶርያ የኢንዱስትሪና የኢኮኖሚ ከተማ አሊፖ የወንበዴዎች መሸሸጊያ አድርጓታል።

ከ12 ዓመታት በኃላ ታዲያ ምን አዲስ?

ዛሬም የሶርያ ፕሬዝዳንት የዓይን ሀኪሙ ባሽር አላሳድ ናቸው።ለፕሬዝዳንቱ ጀርባ ሰጥተው ግንኙነት አቋርጠው የነበሩ የአረቡ ዓለም ሀገራት ዳግም ወዳጅነቱን ፈልገዋል። ኤምሬትስ በድማስቆ የዘጋችውም ኤምባሲ በድጋሚ ስትከፍት አል አሳድም አቡዳቢ ደርሰው ተመልሰዋል።ግብፅ፣ ኦማን፣ ኢራቅና ሊቢያ ወዳጅነታቸውን አጠናክረዋል።ሶርያ ወደ አረብ ሊህ እንድትመለስም ሂደቱ ተጀምሯል።ዳግም ከ12 ዓመት በፊት ሶርያ ወደነበረችበት ትመለሳለች።መቶሺዎች ሲገደሉ ሚሊዮኖች ስደተኛና የአካል ጉዳተኛ ሆኑ፣ንብረት ሲወድም፣ኢኮኖሚው ሲናጋ፣ፍርሃት ሲነግስ ከዚህ ሁሉ የእልቂት አዙሪት በኃላ ግን እየነጋ ይመስላል። እውነታው ደግሞ የተለወጠ የተገኘ አዲስ ድል ግን የለም።