Get Mystery Box with random crypto!

ከ20 ሚሊዮን በላይ ሴቶች የወር አበባ ንጽሕና መጠበቂያ አያገኙም ተባለ! በኢትዮጵያ የወር አበባ | Our World

ከ20 ሚሊዮን በላይ ሴቶች የወር አበባ ንጽሕና መጠበቂያ አያገኙም ተባለ!

በኢትዮጵያ የወር አበባ ከሚያዩ ከ35 ሚሊዮን ሴቶች ውስጥ 22 ሚሊዮን ወይም 75 በመቶ የሚሆኑ ሴቶች የወር አበባ ንጽሕና መጠበቂያ እንደማያገኙ የአደይ የሴቶች የሚታጠብ ንጽሕና መጠበቂያ መሥራች አስታወቁ።

የአደይ የሚታጠብ ንጽሕና መጠበቂያ መሥራች ወይዘሮ ሚካል ማሞ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ የአደይ የሴቶች የሚታጠብ ንጽሕና መጠበቂያ (ፓድ) ምርት በኢትዮጵያ ያለውን የሴቶች የወር አበባ የንጽሕና መጠበቂያ አቅርቦት እጥረት ለመፍታት ይረዳል። በዚህም ያለውን ከ20 ሚሊዮን በላይ ቁጥር ለመቀነስ እንዲሁም የዋጋ ንረቱን ለማረጋጋት ይረዳል።

ለዚህም አደይ ፓድ አንዱ የንጽሕና መጠበቂያ በአንድ የወር አበባ ኡደት ሁለት ጊዜ ጥቅም ላይ የሚውል ሲሆን፣ በአጠቃላይ አንድ መቶ ጊዜ መታጠብ የሚችል መሆኑን መሥራቿ ተናግረዋል። ይህ ድጋሚ ጥቅም ላይ የሚውል የሴቶች ንጽህና መጠበቂያ ያለውን የምርት እጥረት ከመቅረፍ ባለፈ የዋጋ ንረቱንም ሊቀንስ ይችላል ብለዋል።

ይህ በድጋሚ ጥቅም ላይ የሚውል የሴቶች የንጽሕና መጠበቂያ ለሰውነት ተስማሚ ከሆነ ግብዓት የሚሠራ ምቹ የሆነ ፣ፈሳሽ የሚችል፣ምንም የጎንዮሽ ጉዳት የሌለው መሆኑን የጠቀሱት መሥራቿ፣ በአንድ ሳምንት ውስጥ ለ5ሺ ሴቶች የሚደርስ ንጽሕና መጠበቂያ እንደሚመረት ተናግረዋል።

እርሳቸው እንዳሉት፤ አንዲት ሴት በወር አበባ ምክንያት በአማካኝ ከሦስት እስከ አምስት ቀናት ከትምህርት ወይንም ከሥራዋ በንጽሕና በአቅርቦት እጥረት ምክንያት ትስተጓጎላለች። ለዚህም በትኩረት ሴት ተማሪዎች ላይ እየሠሩ ይገኛል። ይህም ምርት ከ18 እስከ 24 ወራት የሚያገለግል በመሆኑ በወር አበባ ምክንያት ከትምህርቷ ሳትስተጓጎል እንድትገኝ የሚያደርጋት ይሆናል።

የትኛዋም ሴት የንጽሕና መጠበቂያ በማጣት ምክንያት ከትምህርት ገበታዋ ይሁን ከአስፈላጊ ሥራዎቿ መቅረት የለባትም የሚሉት ወይዘሮ ሚካል እስካሁንም በሀገሪቱ ለሚገኙ ከ300 ሺ በላይ ሴት ተማሪዎች ንጹሕ የሆነ የንጽሕና መጠበቂያ በመሥራት ተደራሽ ተደርጓል ሲሉ ገልጸዋል።

ዋናው ችግራችን አብዛኛው ግብዓት ከውጭ የሚመጣ በመሆኑ የቀረጥና የግብር ጉዳይ መፍትሔ አለማግኘቱ ነው ሲሉም ተናግረው እንዲሁም የቦታ ጥበት እንዳለባቸው አስረድተዋል።

ሴቶችን ማብቃት ሲባል የመጀመሪያው ነጥብ የወር አበባ ንጽሕና መጠበቂያ ማቅረብ ነው። ለዚህም መንግሥት ይህንን የሴቶች ንጽሕና መጠበቂያ ዋጋ ንረት ለመቅረፍ እንዲሁም ተደራሽነቱን ለመጨመር ምርቶቹን እንዲሁም የምርቶቹን ጥሬ እቃ ከቀረጥ ነጻ ማድረግ እንዳለበት ጠይቀዋል።

እንደ ወይዘሮ ሚካል ገለጻ፤ ያለውን የወር አበባ ድህነት ለመቅረፍ ፣ ከቀረጥ ነፃ እንዲሆን እንዲሁም በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲቀርብ እና ተደራሽ እንዲሆን የተለያዩ ንቅናቄዎች የተደረጉ ሲሆን ከነዚያም ውስጥ ‹ቀረጥ ይወሰንልን ፣ ዋጋ ይተመንልን›፣ ‹ሰብዓዊ መብቴን አትቅረጹ›፣ ‹አበባ አየሽ ወይ ትምህርት ቤት ትሄጃለሽ ወይ?› የሚጠቀሱ ሲሆን አይ ኬር ኢትዮጵያ እና ጀግኒት ኢትዮጵያ ጋር በአጋርነት እንደሚሠሩ ወ/ሮ ሚካል ገልጸዋል።

Via EPA