Get Mystery Box with random crypto!

የአይጥ መርዝ በሶ ላይ በመጨመር ለልጇ ያጠጣችው እናት በቁጥጥር ስር ዋለች በደቡብ ክልል ወላይ | Our World

የአይጥ መርዝ በሶ ላይ በመጨመር ለልጇ ያጠጣችው እናት በቁጥጥር ስር ዋለች

በደቡብ ክልል ወላይታ ዞን ሶዶ ዙሪያ ወረዳ በአይጥ መርዝ የተመረዘ በሶ ለልጇ አጠጥታለች የተባለችዉ የ32 ዓመቷ ተጠርጣሪ በቁጥጥር  ስር  መዋሏ ፖሊስ አስታውቋል።

በዞኑ ሶዶ ዙሪያ ወረዳ ቶሚ ገረራ ቀበሌ ነዋሪ የሆነችዉ ወይዘዋ ጎረቤት ከሚገኝ አባወራ ጋር በድብቅ የፍቅር ግንኙነት መጀመሯ በሰዎች ዘንድ የሚወራዉ ወሬ ከ16 አመቱ ታዳጊ ልጇ ጆሮ ገብቶ ኖሮ የሰማዉን ነገር በአይኑ አይቶ ለማረጋገጥ በትእግስት ነገሩን ሲከታተል ቆይቷል።

ልጅ እናቱ በመንደርተኛዉ የታማችበትን የፍቅር ግንኙነት ትክክል መሆኑ በእርግጠኛነት ሲያውቅ ለወላጅ እናቱ የእናትነት ክብር ሳይነፍግ በትህትና ቀርቦ መክሮ ሊመልሳት ሲሞክር በእሺታ ተቀብላዉ ነበር።

የልጇን ምክር ተቀብላ በእሺታዋ ከመፅናት ይልቅ የእሱን ምክር ወደጎን ትታ ከሰዉየዉ ጋር የነበራትን ግንኙነት አጠናክራ ቀጠለች በዚህም የጀመረችዉ ፍቅር እናቱን ሊያሳጣዉ እንደሚችል ስጋት የገባዉ  ልጅ በድጋሚ እናቱን መክሮ ሊመልስ ጥረት ማድረጉ ይቀጥላል።

እናት ከጎረቤት የምትሰማዉ የፍቅር ቋንቋ ከልጇ ምክር ጋር ስታነፃፅረዉ የልጇ ምክር ለጆሮዋ ያልተመቸ ሆኖ ቢሰማት የጀመረችዉ የፍቅር ግንኙነት ከማቋረጥ ይልቅ ልጇን ከአጠገቧ ገለል ልታረገዉ ከዉሳኔ ትደርሳለች።

የካቲት  23 ቀን 2015 ዓ.ም ከቀኑ 7:00 ሰዓት አካባቢ የ16 ዓመቱ ታዳጊ  ከወላጅ እናቱ የቀረበለት ቤት ያፈራዉን ማእድ ከቀማመሰ በኋላ ለተመገበዉ ምግብ ማወራረጃ ይሆን ዘንድ ያዘጋጀችለት በሶ ጠጥቶ ከቤት ወጣ ይላል።

ታዳጊዉ ከደቂቃዎች በኋላ ሆዱ ላይ በሚሰማዉ የህመም ስሜት ምክንያት  ፊቱን ላብ አጥምቆት  እራሱን ስቶ ሲወድቅ የአካባቢዉ ህብረተሰብ ታማሚዉን በፍጥነት ወደ  ሶዶ ክርስቲያን ሆስፒታል  ያደርሱታል።

ሀኪሞች ወጣቱ መመረዙ በመረዳታቸዉ ህይወቱን ለማትረፍ አስፈላጊዉ ህክምና ቢያደርጉለትም ከቆይታ በኋላ የወጣቱ ህይወት ማለፉን የደቡብ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን የሚዲያ ክፍል ሀላፊ ምክትል ኮማንደር ታጁ ነጋሽ ለብስራት ሬዲዮ ተናግረዋል።

በሶዶ ዙሪያ ወረዳ የቶሚ ገረራዋ እናት ግን ለልጇ  ከምግብ በኋላ ለማወራረጃነት  በሰጠችዉ የተበጠበጠ  በሶ ዉስጥ የአይጥ መርዝ  አድርጋበት ህይወቱ እንዲያልፍ በማድረጓ በቁጥጥር ስር መዋሏን ኮማንደር ታጁ ነጋሽ ጨምረው ለብስራት ሬዲዮ ተናግረዋል።