Get Mystery Box with random crypto!

ሁለት ሰዎችን በመግደል በውሃ መፍሰሻ ቱቦ ውስጥ የጨመሩት የጥበቃ ሠራተኞች በዕድሜ ልክ ጽኑ እስራ | Our World

ሁለት ሰዎችን በመግደል በውሃ መፍሰሻ ቱቦ ውስጥ የጨመሩት የጥበቃ ሠራተኞች በዕድሜ ልክ ጽኑ እስራት ተቀጡ!

በአምስት ቀናት ልዩነት ውስጥ ሁለት ግለሰቦችን ነፍስ በማጥፋት አስክሬናቸውን በውሃ መፍሰሻ የመንገድ ቱቦ ውስጥ የከተቱት ግለሰቦች በእድሜ ልክ ጽኑ እስራት ተቀጡ፡፡በፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ልዩ ልዩ ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ህግ የክስ መዝገብ እንደሚያሳየው 1ኛ ተከሳሽ ዘካሪያስ ኮዶ 2ኛ ተከሳሽ ዮሃንስ ማጠሉ 3ኛ ተከሳሽ አስራት አበበ የተባሉት ተከሳሾች በተለያየ ጊዜ በመገናኘት ባጃጅ ከግለሰቦች ላይ በሃይል ለመንጠቅ ሲመካከሩ እና ሲዘጋጁ ቆይተዋል፡፡

በዝግጅታቸው መሰረትም ጥር 27 ቀን 2013 ዓ.ም ከምሽቱ 02፡30 ሲሆን÷ በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 12 ክልል ልዩ ቦታው ቦሌ ቡልቡላ ሙሉ ወንጌል አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን አካባቢ የባጃጅ ባለቤት የሆነው ሟች ማናየ እንየውን በ30 ብር ኮንትራት በማናገር ወደ ሙሉ ወንጌል ቤተክርስቲያን እንዲወስዳቸው ይስማማሉ፡፡

ሟች አድርሷቸው ከባጃጁ ሊያወርዳቸው ሲቆም 3ኛ ተከሳሽ ሟችን በክርኑ አንቆ ሲይዘው፣ 2ኛ እና 3ኛ ተከሳሾች የሟችን እግር በጋራ ይዘው በማውረድ መሞቱን ሲያረጋግጡ ከቤተ ክርስቲያኑ ፊት ለፊት ካለ የመንገድ ቱቦ በመክተት የሟችን 500 ብር የሚገመት ስልክ እና 185 ሺህ ብር የሚገመት ባጃጅ ወስደዋል፡፡

በተጨማሪም የካቲት 2 ቀን 2013 ዓ.ም ከምሽቱ 03፡30 ሰዓት ሲሆን 1ኛ እና 2ኛ ተከሳሾች የመጀመሪያውን ወንጀል ከፈጸሙ ከአምስት ቀናት በኋላ ምትኩ መለሰ የተባለን ግለሰብ 1ኛ ተከሳሽ የጀኔሬተር ባትሪ ሊሸጥለት በተስማሙት መሰረት ደውሎ እንዲመጣ በማድረግ ተከሻሶች በጥበቃ ሰራተኝነት ተቀጥረው ከሚሰሩበት ሙሉ ወንጌል ቤተ ክርስቲያን ጊቢ ውስጥ እንዲገባ እና እንዲደበቅ አድርገዋል፡፡

ከደበቁ በኋላም 2ኛ ተከሳሽ “ሌባ ሌባ” በማለት ሟችን በያዘው የጥበቃ ዱላ ጭንቅላቱን ሲመታው 1ኛ ተከሳሽም ሟች በወደቀበት የመታው በመሆኑ ህይወቱ አልፏል፡፡በዚህ ጊዜም የሟችን 450 ብር የሚገመት ስልኩን እና ይዞት የነበረውን 3 ሺህ ብር በመውሰድ ከአሁን በፊት የማናየ እንየውን አስክሬን በከተቱበት ቱቦ ውስጥ መደበቃቸው ተገልጿል፡፡ተከሳሾች በፖሊስ ክትትል እና በህብረተሰቡ ድጋፍ ተይዘው በ1996 ዓ.ም የወጣውን የኢፌዴሪ የወንጀል ህግ በመተላለፍ በፈጸሙት የሰው መግደል እና ከባድ የውንብድና ወንጀል ክስ ተመስርቶባቸውዋል፡፡

በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ የሰው መግደል ወንጀል ችሎት የቀረቡት ተከሳሾች ድርጊቱን አልፈፀምንም በሚል የእምነት ክህደት ቃላቸውን የሰጡ በመሆኑ ዓቃቤ ህግ ያሰባሰባቸውን የሰው እና የሰነድ ማስረጃዎች በማቅረብ ተከራክሯል፡፡ተከሳሾችም መከላከያ ማስረጃ በማቅረብ ያሰሙ ቢሆንም በዓቃቤ ህግ የቀረበውን ሰው እና የሰነድ ማስረጃ ማስተባበል ባለመቻላቸው ፍርድ ቤቱ ተከሳሾቹን በተከሰሱበት አንቀፅ ስር ጥፋተኛ ናቸው ማለቱን ከፍትሕ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡ፍርድ ቤቱ ሀምሌ 25 ቀን 2014 ዓ.ም በዋለው ችሎት 1ኛ እና 2ኛ ተከሳሾች የፈፀሙት ተደራራቢ ወንጀል በመሆኑ በሁለቱም ክሶች አንድ የቅጣት ማክበጃ በመያዝ እያንዳንዳቸው በእድሜ ልክ ፅኑ እስራት እንዲቀጡ 3ኛ ተከሳሽ 4 የቅጣት ማቅለያ ተይዞለት በ15 ዓመት ፅኑ እስራት እንዲቀጣ ወስኗል፡፡