Get Mystery Box with random crypto!

በምሳሌው መሠረት በጣፊ ወይም በልብስ ሰፊ የተመሰለው ኢየሱስክርስቶስ ነው፡፡ በአዲስ እራፊ ጨርቅ | ኦርቶዶክስ ተዋህዶ - ‌🇴‌🇷‌🇹‌🇭‌🇴‌🇩‌🇴‌🇽 ‌🇹‌🇪‌🇼‌🇦‌🇭‌🇩‌🇴

በምሳሌው መሠረት በጣፊ ወይም በልብስ ሰፊ የተመሰለው ኢየሱስክርስቶስ ነው፡፡ በአዲስ እራፊ ጨርቅ ምሳሌነት የተወከለው ደግሞ ኢየሱስ ክርስቶስ በአዲስ ኪዳን እንድንጾመው የሠራልን ጾም ነው፡፡ የተቀደደውና መጣፊያ የሚያስፈልገው ልብስ ደግሞ የሐዋርያት ሕይወት ምሳሌ ነው፡፡
እንደ ምሳሌው ሁሉ ሰዎች የክርስቶስ ልብሶች ይባላሉ፡፡

‹‹አልባሲሁሰ ለክርስቶስ መሃይምናን እሙንቱ›› እንዲል፡፡ ይህም ‹‹የክርስቶስ ልብሶቹ ምእመናን ናቸው፡፡›› ማለት ነው፡፡ክርስቶስም ለሰዎች ልብሳቸው ነው፡፡ሐዋርያው ‹‹እናንተ የተጠመቃችሁ ክርስቶስን ለብሳችኋል›› ብሏልና፡፡(ገላ3.27) ምእመናን የክርስቶስ ልብሶች ናቸው ማለት የክብሩ መገለጫዎች ናቸው ማለት ነው፡፡ ልብስ የክብር መገለጫ ይሆናልና፡፡ እርሱ ደግሞ ለምእመናን ልብስ ነው ማለት ጌጣቸው፣ ነውራቸውንየሚሸፍንላቸውና ክብራቸውም እርሱ ነው ማለት ነው፡፡

ጾም ‹‹እራፊ›› መባሏ ምሥጢር አለው፡፡ ይኸውም እራፊ የተለያየውን እንደሚያቀራርብና አንድ እንደሚያደርግ ጾምም የተለያዩ ፈቃዳት ያሏቸውን ነፍስና ሥጋ አንድ ታደርጋለች፡፡ ከዚህም በላይ ከእግዚአብሔር የተለየውን ሰውም አስታርቃ አንድታደርገዋለች፤ ከመንጋውም እንዲቀላቀል ትረዳዋለች፡፡

‹‹በአረጀ ልብስ አዲስ እራፊ የሚያኖር የለም፤ መጣፊያው ልብሱን ይቦጭቀዋልና፤ መቀደዱም የባሰ ይሆናል፡፡›› ማለት አንድ የስፌት ባለሙያ ባረጀ ልብስ ላይ አዲስ እራፊ እንደማይጥፍ ሁሉ ኢየሱስ ክርስቶስም የሐዋርያት ሰውነት በኃጢአት ያረጀ ሆኖ ሳለ በመንፈስ ቅዱስ ሳያድስላቸው አዲስ የሠራውን የአዲስ ኪዳን ጾም ጹሙ ብሎ ሐዋርያትን አያዛቸውም ማለት ነው፡፡

ሰውነታቸው ሲታደስ ያን ጊዜ ግን ይጾማሉ፡፡
ይህ አገላለጥ እግዚአብሔር መንጋዎቹን ያለ አቅማቸው እንዲሸከሙ የማያደርግ አዛኝ ጌታ መሆኑን ያሳያል፡፡
እንዴት ቢባል ሐዋርያትን ሊፈጽሙት በማይችሉበት ሁኔታ ውስጥ እያሉ እንዲጾሙ አላዘዛቸውምና፡፡ ፈጣሪ ለሕዝቡ መቼ ሕግ መስጠት እንዳለበት በሚገባ ያውቃል፡፡ ለእስራኤላውያን በባርነት ሳሉ ዐሥርቱ ትእዛዛትን ያልሰጣቸው ስለዚህነው፡፡ ቢሰጣቸውም ሊጠብቁት አይችሉም ነበርና፡፡ በባርነት ያለ ሰው የራሱ ነጻነት እስከሌለው ድረስ የፈቀደውን ማድረግአይችልም፡፡

በታላላቅ ተአምራት ከባርነት ካወጣቸው በኋላ ግን ሕጉን ሰጣቸው፡፡ ስለዚህ ከክርስቲያን ወገን ማንም ቢሆን ከአቅሙ በላይ የሆነ ነገርፈጣሪ እንዳዘዘው አያስብ፡፡ የታዘዝነው ሁሉ በዐቅማችን ልክ እንደሆነ እንመን፡፡

③ኛ... ‹‹በአረጀ አቁማዳ አዲስ የወይን ጠጅ የሚያኖር የለም፤ ቢደረግ ግንአቁማዳው ይፈነዳል: የወይን ጠጁም ይፈሳል፡፡ አቁማዳውም ይጠፋል፡፡›› ይህ ስለ ጾመ ሐዋርያት የተመሰለው ሦስተኛውና የመጨረሻው ምሳሌ ነው፡፡
በአረጀ አቁማዳ የተመሰለው ሐዋርያት በጸጋ መንፈስ ቅዱስ ሳይታደሱ በፊት የነበራቸው ሕይወት ሲሆን፤ በአዲስ ወይን የተመሰለው ደግሞ ጌታችን በወንጌል የመሠረተልን ጾም ነው፡፡ የጾም ሕግን የሰጠን ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ ደግሞ በጠጅ ጣዩ (በጠማቂው) ተመስሎ ቀርቧል፡፡ አዲስ ጠጅ ባረጀ አቁማዳ እንደማይጣል አምላካችንም ባልታደሰ ሕይወታቸው ሐዋርያትን እንዲጾሙ አላዘዛቸውም፡፡

ቀደም ሲል ጾም ሥጋን ለጊዜው ደስ ባለማሰኘቱ በኀዘን እንደሚመሰል ተመልክተን ነበር፡፡ አሁን ደግሞ በዚህ ምሳሌ ጾም ነፍስን ደስ የሚያሰኝ በመሆኑ በወይንተመስሎ አገኘነው፡፡ ‹‹ወይን የሰውን ልብ ደስ ያሰኛል›› እንዲል፡፡ (መዝ103.15) ጠጅ ጣዮች ሲጥሉ (ሲጠምቁ) ተመልክታችሁ ታውቃላችሁ? አስቀድመው ቦታ ያዘጋጁለታል፡፡ እግር እንዳይበዛበትም ጥላ እንዳይወድቅበትም ይጠነቀቃሉ፡፡ እንዳይነፍስበትም ቀን ከሌሊት ይተጉለታል፡፡ በመጨረሻ ሥራው አልቆ ሳለ ጠጁ ከደረቀ (ከጠነከረ) ይላላ ብለውማር ያልሱታል (ይበርዙታል)፡፡ ከላላ ደግሞ ይድረቅ ብለው ጊዜ ይሰጡታል፡፡

በጠጅ ለተመሰለ ለጾምም በዓይነቱ ተመሳሳይ ከጥቅሙ አኳያ ደግሞ የበለጠ ጥንቃቄ ሊደረግለት ያስፈልጋል፡፡ ለጠጅ ቦታ እንደሚዘጋጅለት ለጾምም ሰውነትን ማዘጋጀትና ጊዜና ዕለት ወስኖ መመደብ በአጠቃላይ ጾምን ማወጅ ይገባል፡፡ ስንዱ እመቤት ቤተክርስቲያናችን የአጽዋማት ዐዋጅ ስላላት እኛ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ልጆች የዚህ ችግር የለብንም፡፡ ለጠጅ እግር እንዳይበዛበትና ጥላ እንዳይድቅበት እንደሚጠነቀቁለት ጾማችንም በከንቱ ውዳሴ አጋንንት እንዳይገቡበትና ያለ መልካም ሥራ በጾም ብቻ ቀርተን ዋጋው እንዳያንስብን እየተጠነቀቅን መጾም ይገባናል፡፡ ጠጅ ደረቀ ይላላ፤ ላላ ይድረቅ እንደሚባል ጾማችን በሕግ ከተሠራልን በላይ ሠዓቱ እንዳይበዛና ከዓቅማችን በላይ አልፎ ሰውነታችን እንዳይጎዳ፤ እንደዚሁም የአጽዋማትን ሰዓት ሳንጠብቅ ቀርተንም መንፈሳዊ ሕይወታችን እንዳይላላ ማዕከላዊውን ስፍራ ይዘን በሕገ ቤተክርስቲያን መሠረት በጥንቃቄ መጾም እንደሚገባን ይህ ሦስተኛው ምሳሌ ያስረዳናል፡፡

ይህን ትምህርት ጌታችን መድኃኒታች ኢየሱስ ክርስቶስ የሚቋጨው ‹‹አዲሱን የወይን ጠጅ በአዲስ አቁማዳ ያኖረዋል ሁለቱም ይጠባበቃሉ፡፡›› በሚለው ኃይለ ቃል ነው፡፡ ዐረፍተ ነገሩ አዲስ የወይን ጠጅ መጣል ያለበት በአዲስ አቁማዳ መሆኑን ይናገራል፡፡ ስለዚህ ሐዋርያት ሕይወታቸው በጸጋ መንፈስ ቅዱስ ከታደሰ በኋላ በአዲሱ አቁማዳቸው አዲሱን ወይን ጣሉ፡፡ ማለትም በአዲስ ሕይወት የአዲስ ኪዳንን ጾም (ጾመ ሐዋርያትን) መጾም ጀመሩ፡፡

አዲስ የወይን ጠጅ በአሮጌ አቁማዳ ሲጣል ያፈነዳዋል፡፡ በአዲስ አቁማዳ ሲጣል ግን ያለፋዋል እንጂ ሊያፈነዳው አይችልም፡፡ ስለዚህ ወይኑም አቁማዳውም አዲስ የሆኑ እንደሆነ አቁማዳው ወይኑን ያፈላዋል፡፡ ወይኑ ደግሞ አቁማዳውን ያለፋዋል፡፡ በዚህ ጊዜ‹‹ሁለቱም ይጠባበቃሉ›› የሚለው ቃል ይፈጸማል፡፡ ጾምና ሰውነት እንደ ወይንና አቁማዳ ናቸው፡፡ ወይንና አቁማዳ እንደሚጠባበቁ (እንደሚጠቃቀሙ) ጾምና ሰውነትም እንዲሁ ናቸው፡፡ ሰው የጾም ሕግን ቢጠብቅ ሕግም እርሱን ትጠብቀዋለች፡፡ ‹‹ይጠባበቃሉ›› የተባለው ለዚህ ነው፡፡ ይህን የሚያስረዳ ‹‹አኮ ንሕነ ዘነዓቅቦሙ ለሕገጋት አላ እማንቱ ሕገጋት የዓቅቡነ ለዓቂብ ወለተፀውኖ›› የሚል ቃል ይገኛል፡፡ ይህም ‹‹ሕጎችን እኛ አንጠብቃቸውም፡፡ እነርሱ መጠበቅን ይጠብቁናል፤ መጠጊያም ይሆኑናል እንጂ፡፡›› እንደማለት ነው፡፡
ወይኑ ቆዳውን ማልፋቱ መልካም ነገር ነው፡፡ የለፋ ቆዳ ብዙ አገልግሎት ስላለው ይፈለጋልና፡፡ ለቀበቶ፣ ለቦርሳ፣ ለጫማና ለልብስ የሚሆነው የለፋ ቆዳ ነው፡፡ የጾምም ጥቅም እዚህ ላይ ነው፡፡ ለልዩ ልዩ አገልግሎትና ጥቅም የሚውል መንፈሳዊ ሕይወት እንዲኖረን ከፈለግን በጾም የለፋ (የደከመ) ሰውነት ያስፈልገናል፡፡ ቆዳን ማልፋት ማዘጋጀት እንጂ ከጥቅም ውጭ ማድረግ አይደለም፡፡ ሰውነትን በጾም ማድከምም ለመንፈሳዊ ሥራ ማዘጋጀት እንጂእንዳይሠራ ማድረግ እንዳልሆነ መረዳት ያስፈልጋል፡፡ የታረሰ መሬት ለዘር እንደሚመች በጾም የደከመ ሰውነትም ለመንፈሳዊጉዞ ይመቻል፡፡ ቅዱስ ዳዊት ‹‹ጉልበቶቼ በጾም ደከሙ›› ያለው ለዚህ ነው፡፡ (መዝ108.24)

ይህን የመሰለ ምሥጢር ያለውን ጾም ‹‹የሽማግሌዎች ጾም፣ ከጥንት ያልነበረ›› እያሉ በመጽሐፍ እና በቀኖና የሌላ ስም በመስጠት ምእመናን እንዳይጾሙት ማድረግ የዲያብሎስ ትጥቅ የማስፈታት ዘዴ እንጂ ሌላምን ሊሆን ይችላል?