Get Mystery Box with random crypto!

መምህራችን ክቡር ቀሲስ ኅብረት የሺጥላ (Hibret Yeshitila Hibret) ከዛሬ 10 ዓ | ኦርቶዶክስ ተዋህዶ - ‌🇴‌🇷‌🇹‌🇭‌🇴‌🇩‌🇴‌🇽 ‌🇹‌🇪‌🇼‌🇦‌🇭‌🇩‌🇴

መምህራችን ክቡር ቀሲስ ኅብረት የሺጥላ (Hibret Yeshitila Hibret) ከዛሬ 10 ዓመት በፊት ያጋሩን ጽሑፍ ነው! በየዓመቱ እንደ አዲስ የሚነበብና ባለብዙኅ ምሥጢር ትምህርት በመሆኑ ተደጋግሞ እንዲነበብ አጋርቻለሁ!
በጎ ጾም መልካም ንባብ ያድርግልን!

✮༒✮ #ጾመ_ሐዋርያት ✮༒✮

(በቀሲስ ኅብረት የሺጥላ)

በየዓመቱ በዕለተ ሰኑይ ብቻ (ሰኞ ቀን ብቻ) የሚጀምሩ ሦስት አጽዋማት አሉ፡፡ እነርሱም ዓቢይ ጾም፣ ጾመ ነነዌ እና ጾመ ሐዋርያት ናቸው፡፡
እነዚህ አጽዋማት ምን ጊዜም ቅበላቸውእሁድ ሲሆን የሚገቡት ደግሞሰኞ ቀን ነው፡፡

በየትኛውም ዓመት ይህን ዕለት አይለቁም፡፡ ስለዚህ የ2004 ጾም ሐዋርያት ግንቦት 27 ሰኞ ዛሬ ተጅምሯል ፡፡ (ጽሑፉ የተለጠፈበትን ዓመት ያመለክታል ለዘንድሮው ሰኔ 1 ዛሬ ሰኞ) ቤተ ክርስቲያናችን ያለችበትን ነባራዊ ሁኔታ ከግምት ውስጥ በማስገባት፣ በየግላችንም ያጋጠሙንን መንፈሳዊና ሥጋዊ ውጊያዎች በማሰብ ድል የምናደርግበትን ኃይል ፈጣሪያችን ይሰጠን ጾሙን ከወትሮው በበለጠ ጥንቃቄ ልንጾመው ይገባናል፡፡

የጾሙን ታላቅነት ተረድተን እንድንጾመው የትመጣውን፣ ትንቢቱን፣ ምሳሌውንና ምሥጢሩን መረዳት አጋዥ ስለሚሆነን አስቀድመን ስለጾሙ እንማር ዘንድ በአጭሩ አቅርቤዋለሁ! የምችለውን ያህል እጽፍ ዘንድብርታቱንና ጥበቡን የሰጠኝ አምላከ ቅዱሳን ሐዋርያት ክብር ምስጋና ይድረሰው! አሜን!

ጾመ ሐዋርያት በራሳቸው በሐዋርያት የተጀመረ ጾም እንደመሆኑ መጠን በአንደኛው መቶ ክፍለ ዘመን ማለትም ከዛሬ አንድ ሺህ ዘጠኝ መቶ ዓመታት በፊት ጀምሮ ሲጾም የኖረ ጾም ነው፡፡ ለዚህም የመጽሐፍ ቅዱስ፣ የአዋልድ መጻሕፍትና የታሪክ በርካታ ምስክሮች አሉ ስለዚህ ጾሙን እንደ እንግዳ ነገር መቁጠርና ዘመን አመጣሽ አድርጎ ማየት የራስን አላዋቂነት ያሳያል፡፡ ይህን ማለት ያስፈለገው ጥቂቶች ጾሙን ድሮ ያልነበረና ዘመን አመጣሽአድርገው ስለሚናገሩ ነው፡፡
ጾመ ሐዋርያት ቤተ ክርስቲያን ዕድሜያቸው ለጾም የደረሱ ምእመናን በሙሉ እንዲጾሙአቸው ካወጀቻቸው ሰባት የአዋጅ አጽዋማት መካከል አንዱ ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በጌታችንና በአምላካችን በኢየሱስ ክርስቶስ አንደበት ቀን የተቀጠረለት፣ ትንቢት የተነገረለትና ምሳሌ የተመሰለለት ጾም መሆኑ ከአጽዋማት ሁሉ ለየት ያደርገዋል፡፡

ጌታችን ስለዚህ ጾም ትንቢተ በመናገር፣ ምሳሌ በመመሰል ሰፊትምህርት የሰጠው ፈሪሳውያን ወደ እርሱ ቀርበው ‹‹ደቀ መዛሙርትህ የማይጦሙት ስለ ምንድር ነው?›› ብለው በጠየቁት ጊዜ ነው፡፡ እርሱም ሲመልስ እንዲህ አላቸው፡- ‹‹ሚዜዎች ሙሽራው ከእነርሱ ጋር ሳለ ሊያዝኑ ይችላሉን? ነገር ግንሙሽራው ከእነርሱ የሚወሰድበት ወራት ይመጣል፤ በዚያ ጊዜም ይጦማሉ፡፡ በአረጀ ልብስ አዲስ እራፊ የሚያኖር የለም፤ መጣፊያው ልብሱን ይቦጭቀዋልና፤ መቀደዱም የባሰ ይሆናል፡፡ በአረጀ አቁማዳ አዲስ የወይን ጠጅ የሚያኖር የለም፤ ቢደረግ ግን አቁማዳው ይፈነዳል፤ የወይን ጠጁም ይፈሳል፡፡ አቁማዳውም ይጠፋል፡፡ ነገር ግን አዲሱን የወይን ጠጅ በአዲስ አቁማዳ ያኖረዋል ሁለቱም ይጠባበቃሉ፡፡›› (ማቴ9.14-17)

በመቀጠል እስከ መጨረሻ የምንመለከተው ከላይ የሰፈረውን የማቴዎስ ወንጌል አጭር ገጸ ንባብ ሐሳብ በመሆኑ መለስ እያሉ
ታሪኩን ማንበብ ወይም በልብ ከመዘገቡ በኋላ ቀጣዩን ክፍል ማንበብ ምሥጢሩን ለመረዳት ያግዛል፡፡
በዚህ የጌታችን መልስ ውስጥ ‹‹ነገር ግን ሙሽራው ከእነርሱ የሚወሰድበት ወራት ይመጣል በዚያ ጊዜም ይጦማሉ፡፡›› የሚል ስለጾመ ሐዋርያት የተነገረ የትንቢት ቃል እናገኛለን፡፡ ይህ አምላካዊ ቃል ጾሙ ስለሚጀመርበት ወራት ቀጠሮ ይሰጣል፡፡ ያም ጊዜ ሙሽራው ከእነርሱ ከተወሰደ በኋላ ያለው ጊዜ ነው፡፡ ‹‹ሙሽራው ከተወሰደ›› በኋላ ማለት ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ሰማይ ካረገ በኋላ ማለት ሲሆን በቤተ ክርስቲያን ጾመ ሐዋርያት ከዕርገት በኋላ የሚጀምረው በዚህ ቃል ምክንያት ነው፡፡ ይህም ቤተ ክርስቲያን ምን ያህል መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረት ያላት መሆኗን ያሳያል፡፡
ጾመ ሐዋርያት ከዕርገት በኋላ ለዐሥር ቀናት ያህል ዘግይቶ እንጂወዲያው አይጀምርም ምክንያቱም የሐዋርያት ሰውነት በአዲስ ሁኔታ ጌታችን ላዘጋጀው የአዲስ ኪዳን ጾም ተመቻችቶ ያልተገኘ በመሆኑ ነው፡፡ ስለዚህ በመጀመሪያ የሐዋርያት ሰውነት ለጾሙ መዘጋጀት ነበረበት፡፡ ከዚያ በኋላ ሐዋርያት መጾም ጀምረዋል ይህም በጌታችንን የመልስ ቃል ውስጥ የተካተተ እንጂ የፈጠራ ድርሰት አይደለም፡፡ ‹‹በአረጀ ልብስ ላይ››እና ‹‹በአረጀ አቁማዳ›› የሚሉት ሁለት ተከታታይ ምሳሌያዊ ማብራሪያዎች ሐዋርያት ሰውነታቸው በመንፈስ ቅዱስ ከመታደሱ በፊት ጾም መጾም እንደማይጀምሩ ወይም እንደሌለባቸው የሚያስረዱ ምሳሌዎች ነበሩ፡፡ ስለዚህ ሐዋርያት የተዘጋጀላቸውን ጾም መጾም የጀመሩት ከኢየሱስክርስቶስ ዕርገት በኋላ በዐሥረኛው ቀን በወረደ ጸጋ መንፈስቅዱስ የሕይወት ሕድሳት አግኝተው ነው፡፡

ከላይ በተጠቀሰው የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ትምህርት ውስጥ ስለጾመ ሐዋርያት የቀረቡ ሦስት ዓይነት ምሳሌዎችን እናገኛለን፡፡ ምሳሌዎቹ በምሥጢር የተሞሉ በርካታ መንፈሳዊ መልእክቶችን ያዘሉ ናቸውና ተራ በተራ እንመለከታቸዋለን፡፡

①ኛ...‹‹ሚዜዎች ሙሽራው ከእነርሱ ጋር ሳለ ሊያዝኑ ይችላሉን?›› የሚለው ዐረፍተ ነገር በገጸ ንባቡ ውስጥ ስለ ሐዋርያት ጾም የተመሰለው የመጀመሪያው ምሳሌ ነው፡፡ ሚዜዎች የተባሉት እንደ መጥምቁ ዮሐንስ መንገድ የሚጠርጉ፣ የሚያስተምሩና ምእመናንን ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ የሚያቀረቡ ሁሉ ናቸው፡፡ ሙሽሪትን ወደ ሙሽራው መውሰድ የሚዜዎች ሥራ መሆኑ በአይሁድና በኢትዮጵያውያን ባህል ሲሠራበት የኖረ ነው፡፡ ስለዚህ ዋነኞቹ ሚዜዎች ሐዋርያት ናቸው ማለት ነው፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ሙሽራ ሲሆን ቤተክርስቲያን (ምእመናን) ደግሞመርዓት (ሴት ሙሽራ) ትባላለች፡፡ (2ቆሮ11.2፤ዮሐ3.29)
‹‹ሚዜዎች ሙሽራው ከእነርሱ ጋር ሳለ ሊያዝኑ ይችላሉን?›› ሲልሚዜዎች ሙሽራውን ለማስደሰት ሲሉ ምንም የሚያሳዝን ነገር ቢያጋጥማቸውም እንኳን ጨክነው በመቻል ያሳልፉታል እንጂ በሙሽራው ፊት እንደማያዝኑ፤ እንደዚሁም መጾም ተገቢ ነገር ቢሆንም ሐዋርያትኢየሱስ ክርስቶስ ከእነርሱ ጋር ሳለ መጾም እንደማይገባቸው ነገር ግን ከእነርሱ ተለይቶ ሲያርግ መጾም እንደሚጀምሩ ያስረዳል፡፡

በዚህ ምሳሌያዊ ንባብ ውስጥ ጾም በኀዘን ተመስሏል፡፡ መጾም ተድላነቱ ለነፍስ እንጂ ለሥጋ አይደለምና፡፡ ሥጋ ጾምን እስኪለምድ ድረስ ቅጣት ይሆንበታል፡፡ ስለዚህ በጾም ነፍስ ስትደሰት ሥጋ ግን ያዝናል፡፡ በዚህ ምክንያት ጾም በኀዘን ተመስሏል፡፡ በዚህም ምክንያት ጾም በብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ከኀዘን፣ ከዕንባ፣ከጸጸትና ከንስሐ ጋር ተያይዞ ቀርቧል፡፡ (ኢዩ2.12)

②ኛ...‹‹በአረጀ ልብስ አዲስ እራፊ የሚያኖር የለም፤ መጣፊያው ልብሱን ይቦጭቀዋልና፤ መቀደዱም የባሰ ይሆናል፡፡›› ይህ ዐረፍተ ነገር ደግሞ ሁለተኛው ምሳሌ ነው፡፡ እራፊ ማለት ቅዳጅ ወይም መጣፊያ ጨርቅ ማለት ነው፡፡ የስፌት ባለሙያ ባረጀ ልብስ ላይ አዲስ ጨርቅ አይጥፍም (አይሰፋም) ወይም አይለጥፍም፡፡ ይህም አንደኛ ግንጥል ጌጥ እንዳይሆን፤ ሁለተኛ ላሮጌ ልብስ ሲባል አዲሱን ማበላሸት እንዳይመጣና አዲሱ ካሮጌው ስለሚበረታ የባሰ እንዳይቦጭቀው በማሰብ ነው፡፡