Get Mystery Box with random crypto!

ዲሽ አተካከል ለፍፁም ጀማሪዎችና ለተካኑ የዲሽ ቴክኒሺያኖች ዲሽ ለመጀመሪያ ጊዜ ለመትከልና ለመግ | ƝƲƦƲ ሳይቴክ

ዲሽ አተካከል ለፍፁም ጀማሪዎችና ለተካኑ የዲሽ ቴክኒሺያኖች

ዲሽ ለመጀመሪያ ጊዜ ለመትከልና ለመግጠም የተሰማሩ የዲሽ ባለቤት ግለሰቦች ፡ ጀማሪ ወይም ልምድ ያላቸው ቴክኒሺያኖች መያዝ የሚገባቸው የሳተላይት ዲሽ መግጠሚያ መሳሪያዎችና አጠቃቀማቸው፡-
– ማንኛውም የሳተላይት ዲሽ ቴክኒሺያን በቅድሚያ የሚገጥመውን የሳተላይት ዲሽ አይነትና አቅጣጫ በአትኩሮትና በበቂ ሁኔታ ከምንም በላይ መገንዘብ ይኖርበታል፡፡
– በአብዛኛው በሃገራችን የሚገጠሙና ስርጭታቸው በሰፊ ከሚገኙ የሳተላይት ዲሽ ቻናሎች ለመጥቀስ ያህል በየቤታችን የሚገኘውና እጅግ ብዙ ተጠቃሚዎች ያሉት የናይልሳትና ከ 5 እና 6 አመታት በፊት ሁሉም የሀገራችን ብሎም ተወዳጅ የውጭ ቻናሎች ይገኙበት የነበረው አሁን በአረቡ አለም ዘንድ ብቻ በስፋት በጥቅም ላይ የሚውለው የአረብሳት ቻናል እና ነፃ የኳስ ቻናሎች ማለትም ቨርዛሽ ቲቪ፣ ቶሎዶ ቲቪ እና ሌሎችን የእንግሊዝና ስፔን ላሊጋ ብሎም፣ የቻምፒዮንስ ሊግ ጨዋታዎችን የሚያስተላልፉ ቻናሎች የሚገኙባቸው የያህሳት ቻናል ዲኤስቲቪ እና የ ፓወር ቪዩ ቻናሎች የሚገኙ ሲኖን እንደ አንድ የሳተላይት ዲሽ ጀማሪም ሆነ የተካነ ቴክኒሺያን ማወቅ ከሚገቡን ነገሮች መካከል የእያንዳንዱን ቻናል አቅጣጫና አቀማመጥ ነው፡፡ እነዚህን ቻናሎች በአግባቡ ለመትከል እንዲረዳን የአቅጣጫ ጠቋሚ ማለትም ኮምፓስ መጠቀም በብዛት የሳተላይት ዲሾችን ለመግጠም ጥቅሙ እጅግ ከፍ ባለ ደረጃ የሚረዳን ሲሆን አጠቃቀሙን በቀጣይ ፅሁፋችን ከፍተኛ አትኩሮት ወደምንሰጥበት መሰረታዊ ፅንሠ ሃሳቦች ጋር ይዘን በሰፊው እንመለስባቸዋለን፡፡
– ማንኛውም የሳተላይት ዲሽ ለመትከል የተዘጋጀ ጀማሪም ሆና የተካነ ባለሙያ መያዝ ያለባቸው እጅግ መሰረታዊና የምንጊዜም አጋዠ መሳሪያዎች መካከል የሚከተሉትን መዘርዘር ይቻላል፡፡
በተለምዶ አስር ቁጥር ብለን የመንጠራው የብሎን መፍቻ ለባለ 60 ሴንቲሜትር ሳህንና (ለ 90 ሲንቲሜትርና ከዛ ክፍ ለሚሉ የዲሽ ሳህኖች፣ 10 ቁጥርን ጨምሮ እንደአስፈላጊነቱ 10፣11፣12፣ እና ከዚያ በላይ ያሉት መፍቻዎች በተናጠል ወይም (በህብረት) ማለትም በአንድ የብረት ዘንግ ሶስቱንም በስሩ የያዘ መፍቻ ወይም ከአነስተኝ እስከ ከፍተኛ የብሎን አናት ቁጥሮችን በማጥበቅና በማላላት የምንጠቀምበት በተለምዶ ካበ እንግሊዝ (Wrench) ብለን የምንጠራውን ባለ አንድ ወጥ በጣት በማሽከርከር እንደ ብሎኑ አናት መጠን የሚጠብና የሚሰፋ መፍቻ በቅርብ ከሚገኝ የህንጻ መሳሪያ መደብር መግዛትና ሁሌም ዲሽ ለመትከልም ሆነ ለማስተካለል በምንቀሳቀስበት ጊዜና ቦታ መያዝ፡፡
የሚቻልና አቅማችን ከፈቀደ (በተለይ ዲሽ መትከልን እንደ ዘላቂ ሙያ ለያዡ) ሙሉ በሙሉ ዲጂታል የሆነ የሳተላይት ማሰሻ ወይም Finder በመግዛት ለአስፈላጊው ስራ መዘጋጀት፡፡ አቅም የማይፈቅድ ከሆነም ቆየት ያለውን ነገር ግን ላዩ ላይ ዲጅታል ፋይንደር የሚል ፅሁፍ ያለውንና ከ 0 እስከ 10.5 ዲ.ቢ የሚለካውን ባለ ሜትሩን የሳተላይት ዲሽ ማሰሻ ከ 400 ብር ባልበለጠ ገንዘብ በአካባቢያችን በሚገኙ የኤሌክትሮኒክስ እቃዎች መሸጫ መደብሮች መግዛትና መያዝ፡፡ ለስራችን ቅልጥፍና የሚረዳን የመጀመሪያው አይነት ዲጅታል ፋይንደር ሲሆን የራሱ የሆነ የባትሪ ሀይል ስላለው መብራት እንኳን ቢጠፋ ጣራ ላይ ባለንበት ስራችንን ለመጨረስ ያስችለናል በተጨማሪም የፋይንደሩ ሰሌዳ ላይ ልክ ሪሲቨሩ ላይ እንደምናየው ሲግናልና ኳሊቲ ማንበቢያ ስላለውና የምንፈልጋቸውን የቻናል ፍሪኩዌንሲዎች ሞልቶ ስለሚይዝልን ስራችንን እጅግ ፈጣን ያደርግልናል፡፡ እጅግ በጣም የሚያስፈልገን ከሆነ ደግሞ በአንገት የሚንጠለጠል የምናስሰውን ቻናል በፋይንደሩ ሰሌዳ ላይ ልክ እንደ ቴሌቪዥን ምስሉን በጥራት የሚያሳይ ድምፁንም በጥራት የሚያሰማ ሲግናልና ኳሊቲ ማንበቢያ ያለው እጅግ ዘመናዊ የሆነ ፋይንደር ገዝተን ስራችንን በጣም በዘመናዊ መልኩ ማካሄድ እንችላለን፡፡
-ከ ፋደራችን አይነትና አቅም ጋር የሚሄድ ተወርዋሪ ገመድ ከዲሹ ጋር ከሚመጣው RG-6 Coaxial Cable (የዲሽ ገመድ) ወይም ከቴሌቪዥን የውጭ አንቴና ጋር ከሚመጡ በውስጣቸው ቀጭን የኮፐር ወይም መዳብ ዘንግ ከያዙ ገመዶች ቆርጦ ርዝመቱ ከ 60 ሳንቲሜትር ያላነሰ ተወርዋሪ ገመድ (Jump Caple) በሁለቱም በኩል የሴቴ ወይም (Female Connector) የያዘ ገመድ ማዘጋጀት፡፡ የገመዱ ጫፍ አንደኛው ወደ የዲሹ ጭንቅላት (LNB) ላይ የሚታሰር ሲሆን ሌሌኛው ጫፍ ፋይንደሩ ላይ (To LNB) በሚለው አቅጣጫ የሚታሰር ይሆናል፡፡ የፋይንደርን አጠቃቀም ወደ ፊት ሰፋ ያለ ትንታኔ የምንሰጥበት ስለሆነ ለዛሬው እዚህ ላይ እንግታው፡፡
-ተወርዋሪ ገመድ ወይም ከዲሹ ጋር አብሮ የሚመጣውን ገመድ ጫፎች ለመላጥ፣ Female Connector ችን ለማያያዝ፣ ገመዶችን ለማሳጠር ወይም ለመቀጠልና ለማስረዘም እንዲረዳን አንድ ጥሩ የሆነ ፒንሳ ያስፈልገናል፡፡ በአቅራቢያችን ማግኘት የምንችል ከሆነ ደግሞ ኬብል ስትሪፐር ወይም ኬብል ከተር መግዛት ስራችንን ቀልጣፋ ያደርግልናል፡፡
-የዲሹን LNB ማቀፊያ ለማጥበቅና ለማላላት ብሎም LNB ለመቀየርና አዳፕተሮችን ለመፈታታትና ለማጥበቅ ሊረዳን የሚችል በሁለቱም በኩል ሲቀያያር ጠፍጣፋና ባለ መስቀል አናት የሚሰጥ ካቻቢቴ መያዝ ይጠበቅብናል፡፡
-የዲሹን ሳህን እግር በሁለት አቅጣጫ ረዘም ካሉ ጣውላዎች ጋር መምቻና የዲሹን ገመዶች በየግድግዳው በኬብል ክሊፕ ለማያያዝና ሌሎች ጠንከር ያለ ሀይል የሚጠይቁ ስራዎችን ለማከናወን የሚጠቅመንን አጠርያለ የፕላስቲክ እጀታ ያለው መዶሻ ያስፈልገናል፡፡
ከላይ የጠቀስናቸው መሳሪያዎች እጅግ መሰረታዊና አስፈላጊ ሲሆኑ ከዚህ በታች የተዘረዘሩት ደግሞ አስፈላጊነታቸው በጣም ብዙም ባይሆን እንኳን መያዛችን ግን ጥቅሙ እጅግ ያመዘነ ይሆናል፡፡
-በማንኛውም ሁኔታ ቢሆን ሊጠቅሙን ስለሚችሉ በርከት ያሉ የ Female connector, Audio Video Splittor Conector ንና ከሁለት ያላነሱ Disqe Switch መያዝ፡፡
-እንደየ ፍላጎታችን የምንሞላውን ሳተላይት መሠረት ያደረጉ የተለያዩ ፊሪክዌንሲዎችና፣ ፖላራይዜሽሮች ዝርዝር በጥንቃቄ ለማወቅ ይረዳን ዘንድ እና አዳዲስ መረጃዎችን በማይረሱ መልኩ ለመፃፍና በአስፈላጊ ጊዜ ዋቢ ለማድረግ ለመፃፊያነት የሚረዱን መጠናቸው እንደየ ግል ፍላጎታችን በሚወሰኑ ማስታወሻ ደብተሮች ላይ ማስፈር፡፡ ለዚህም ይረዳን ዘንድ ለአያያዝ አመቺ የሆኑ ማስታወሻ ደብተሮችን በአቅራቢያችን ከሚገኙ የፅህፈት መሳሪያ መደብሮች ገዝቶ መያዝ፡፡
-የስራው ባህሪ ሆኖ ብዙዎች ተገልጋዮችን የምናገኛቸው በተንቀሳቃሽ ሞባይል ስልኮች ከመሆኑ የተነሳ የኔትወርክ ግኑኝነት በማይኖረበት ቦታ የኔትወርክ ግኑኝነትን አስሰውና ፈልገው የሚያመጡልንን ዘመኑ ኖርማል ሀንድሴት ብሎ የሚጠራቸውን ግን በባትሪ ቆይታቸውና ጣበት ወቅት ከፍተኛ ጥንቃቄዎችን ማድረግ ይገባናል፡፡
-ምንም እንኳን የተቻለንን ጥንቃቄ ብናደርግም በተለያየ የስራ አጋጣሚ ሊደርሱብን የሚችሉ ቀለል ያሉ ጉዳቶች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ በመሆኑም አንድ አነስ ያለች የመጀመሪያ ህክምና እርዳታ መስጫ መሳሪያዎችን የያዘች ሳጥን ቢኖረን እጅግ በጣም ጥሩ ነው፡፡ በውስጧም በርከት ያሉ የቁስል ፕላስተሮች፣ ንፁህ ጥጥ፣ ፋሻ፣ የተጠቀለለ ነጭ የቁስል ፕላስተር፣በፕላስቲክ ጠርሙስ የታሸገ አልኮል (በተለምዶ ጂቢ የምንለው) እና ሌሌችንም የያዘች ብትሆን እጅግ በጣም ተመራጭ ነው፡፡ ያስታውሱ ምንጊዜም ቢሆን ለጥንቃቄ ቅድሚያ መስጠት ይኖርብናል፡፡