Get Mystery Box with random crypto!

ሳያቋርጡ የመስገድ ጥቅም! በሰዉ ልጆች ሕይወቱ ዉስጥ ብዙ ዉጣ ዉረድና ሸክም አለ ቢወራ ከንፈር | ንቁ'የመዳን ቀን ዛሬ ነዉ!

ሳያቋርጡ የመስገድ ጥቅም!


በሰዉ ልጆች ሕይወቱ ዉስጥ ብዙ ዉጣ ዉረድና ሸክም አለ ቢወራ ከንፈር መጦ ዝም ከማለት ዉጪ ምፍትሔ የታጣለት ዉስጥ ባዶ ሆኖ ላይ የጸዳበት የሕሊና ሰላም ተገፎ ደስታ የታጠበት ለብቻ የሚያስቆዝም ሕመም ተሸክሞ ሕይወቱን የሚመራ በዚህ ዘመን ይበዛል ማንም ቢሆን ይሄንን ሸክሙን አራግፎ የሰላም ሕይወትን መምራት የሚጠላ የለም ሁሉም ይፈልጋል ለዚህ ችግር መፍትሔዉ ያለዉ እግዜር ጋር ብቻ ነዉ የስግደት ኀይል ምን ያክል እንደሆነ የምንረዳዉ የሕይወት ዉጣ ዉረድ አስለቺ ሆኖባቸዉ በሰዎችም ዘንድ ተጠልተዉ በራሳቸዉ ተስፋ ቆርጠዉ ከተቀመጡ አይሁዶች መማር እንችላለን። በአይሁድ ዘንድ የለምጽ በሽታን እርኩሰት በመሆኑ ለምጽ የያዘዉን ሰዉ ያገሉታል እንጂ አያቀርቡትም ዘፍ፤13 እና 14 ታዲያ ለዘመናት በለምጽ በሽታ ሲሰቃይና በሰዎች ዘንድ ሲገለል የነበረዉ ሰዉ ከኀጢአት ባርነት ነጻ አዉጥቶ የልጅነት ጸጋ ሊሰጠን የመጣዉን መድሃኒታችንን ባየዉ ጊዜ ወደ እርሱ ቀርቦ ሰገደለትና አቤቱ ብትወድስ ልታነጻኝ ትችላለህ እያለ ለመነዉ መድሃኒቱም እወዳለሁ ንጻ ብሎ ዳሰሰዉ ከዚህም ስቃይ ዳነ ይሄም ሰዉ በስግደትና በጸሎት ኀይል ከሰቆቃ ኑሮ ነጻ ወጥቶ በሰላም ከወገኖቹ ጋር ለመቀላቀል በቃ ሉቃ፤5፤12-13 የስግደት ኀይል በዚህ ብቻ አያበቃም የሥጋ ፈዉስ ካገኘን በኋላ ድምጽ ሳናሰማ ሽል ብለን ወደ ነበርንበት እንዳንመለስ አሥራ ሁለት ዓመት (12) ደም ይፈሳት የነበረችሁ ሴት ምስክር ትሆንናለች ይህቺ ሴት አሥራ ሁለት ዓመት ሙሉ ደም ይፈሳት ነበረ ለዚህ በሽታዋ መፍትሔ ፍለጋ ገንዘቧን ለባለመድሃኒቶች በመስጠት የጨረሰች መፍትሔ ሳታገኝ ባዶዋን የቀረች በበሽታዋ ምክንያት ቤተሰቦቿ ወዳጅ ዘመዶቿ የራቋት ሁሉ ተጸየፏት ብቻዋን የምትሰቃይ ሚስኪን ሴት ናት የወደቁትንና የተገፉት ሊሰብስብ የመጣዉን መድሃኒታችንን ባየችሁ ጊዜ በእምነት የልብሱን ጫፍ ብነካ እድናለዉ ብላ የልብሱን ጫፍ ብትዳስሰዉ ከዚህ ስቃይ ተፈወሰች ከዳነች በኋላ ዝም ብላ ልትሄድ ስትል ወደ እቅፉ ገብተን ዳግም ከእቅፉ እንዳንወጣበት የማይፈልገዉ መድሃኒታችን ማነዉ የነካኝ ሲል ጠየቀ በዚህ ጊዜ ነገሩ እንዳልተሸሸገላት ስታዉቅ ከሰገደችለት በኋላ ምስክርነቷን ሰጠች። ሉቃ፤8፤41-47 ዮሐ፤9፤36፣እና 12 ቅዱሱ መፅሐፍ ላይ እንደተመለከትነዉ ስግደት ከብዙ መከራ ዉስጥ አዉጥቶ ወደ ተሻለ የሕይወት ደረጃ ይወስዳል። በልዩ ልዩ መከራ ዉስጥ ያላችሁ እናንተስ በምን ዓይነት ችግርና ስቃይ ዉስጥ ትገኛላችሁ? በሕይወታችሁ ዉጣ ዉረድ በዝቶ ብቻችሁን የምትሰቃዩ ወገኖቻችን የመድሃኒታችን ድንቅ ሥራ ቅዱሱ መፅሐፍ ላይ ብቻ ታሪክ ሆኖ አልቀረም አንተ አንቺ እናንተ እኛ ሕይወት ዉስጥም ይሰራል ችግራችሁ ምንም ይሁን ምን ከኀጢአት ባርነት ነጻ ትወጡ ዘንድ እርሱ ፊት ወድቁ አሰልቺ የሆነባችሁን ነገር በሙሉ አራግፎ በሰላም እንድትኖሩ ያደርጋችኋል። መከራችሁንና ፈተናችሁን ለሰዉ ብታወሩ ዘላቂ መፍትሄ አታገኙም እግዚአብሔር ዘንድ ግን መፍትሄ የሌለዉ ሕመምና ስቃይ የለም በምንም የኀጢአት አዘቅጥ ዉስጥ ብትወድቁም በማወቅ ሆነ ባለማወቅ አንዴ በድላችኋል ዳግም ላለመበደል ግን ወደ እግዚአብሔር ቀርባችሁ ይቅርታዉን ከልብ ፈልጉ።
( ፩) ሳያቋርጡ የመስገድ ጥቅሙ ሕሊና በኀጢአት ሲቆሽሽ እንስሳዊ ባሕሪዉ ጎልቶ ስለሚወጣ የሰዉ ልጅ ለሚሰራዉ ኀጢአት ጸጸት የማይሰማዉ ፍጥረት ስለሚሆን ስግደት ደግሞ የሥጋ ፈቃዳን ጎስሞ የዲያቢሎስን ትዕቢት ስለሚያዋርድ እግዚአብሔርን እንደበደልነዉ ከልብ የመነጨ ኀዘን አጎናፅፎን ወደ ንስሀ የሚመራ አንዱ ጠላታችንን የምንዋጋበት የጦር ዕቃችን ነዉ። (፪) ዲያቢሎስ በባሕሪዉ አታላይና አስመሳይ ፍጥረት ነዉ ባላጋራ ነዉና የሰዎችን ደካማና ጠንካራ ጎን ስለሚያዉቅ መስገድ በጀመራችሁ ጊዜ ድኛለሁ ብላችሁ ነገር ዓለሙን እንድትተዉ በማድፈጥ የጥፋት መረቡን ሰብስቦ ዝም ይላል በዚህ ጊዜ የሥጋ ፈዉስና በተቸገራችሁበት ነገር መፍትሔ ያገኛችሁ ስለሚመስላችሁ ስግደቱን ስታቋርጡ ጠብቆ ከበፊቱ የባሰ መከራ ሊያጸናባችሁ ይነሳል ማቴ፤12፤43-45 ታዲያ ሳያቋርጡ የመስገድ ጥቅሙ ጠላት እንዳያደፍጥ ስለሚያደርገዉ መሸሸጊያ አሳጥቶት ቀጥቅጦ ከሰዉነት ዉስጥ እንዲወጣ ያደርጋል፤ አስተዉሉ፦መስገድ ያለባችሁ የምትፈልጉት ነገር እስኪሟላላችሁ ሳይሆን ይህቺን ዓለም ተሰናብታችሁ ወደ ተስፋይቱ ምድር እስክትሄዱ ድረስ መሆን አለበት። በዘፈቀድ ዝም ብላችሁ አንድ ቀን ስግደት በሌላ ቀን እረፍት የምታዘዉትሩ ከሆነ አሰልቺ የሆነ ኑሮን ለመምራት ትገደዳላችሁ ስገደትን እያቋረጣችሁ መስገድ የለባችሁም፥ (፫) ሳያቋርጡ የመስገድ ጥቅሙ በሥጋ ፍትወት በዝሙት ፈተና ከመፈተንና ከልዩ ልዩ ፈተናዎች ይታደጋል ።(፬) ሳያቋርጡ የመስገድ ጥቅሙ መገዛትን፤ መታዘዝን፤ ማመስገንን፤ ፍቅርን፤ ትሕትናን፤ ያስተምራልና ሳታቋርጡ ስገዱ!



ሳያቋርጡ የመጸለይ ጥቅም!


የሰዉ ልጅ ቅድሚያ የሚሰጠዉ ከዉጪ ለሚገባዉ አዲስ አሳብ ሳይሆን መጀመሪያ ዉስጡ ተደላድሎ ለተቀመጠዉ አሳብ በመሆኑ አንዳንድ ምዕመናን በጸሎት ጊዜያት የአሳብ መበታተንና ቆሞ ለመጸለይ ችግር ሲያጋጥማቸዉ እግዚአብሔር ፊት ቆሜ እንዴት ክፉ አሳብ አስባለዉ ቁጭ ብዬስ እንዴት እጸልያለሁ ብለዉ አለመጸለይን እንደ መፍትሔ በመዉሰድ ጸሎቱን እርግፍ አድርገዉ ለመተዉ ይወስናሉ ይሄ ፈጽሞ የተሳሳተ መፍትሔ ነዉ፡እንዲህ አይነቱ እርምጃ ለሕመሜ የታዘዘልኝ መድሃኒት ስለማይጣፍጥ በሽታዉ ቢገድለኝ ይሻለኛል እንጂ መድሃኒቱን አልወስድም ብሎ እንደመወሰን ይቆጠራል፡የነፍስ መድሃኒቷ ጸሎት ነዉና ጸሎት ማቋረጥ ተገቢ አይደለም። እንዲህ የሚሆንበት ምክንያት ዲያቢሎስ ሕሊናን ተቆጣጥሮ እግዚአብሔር ፊት ቆሜ እንዴት ክፉ አሳብ አስባለዉ ብላችሁ ጸሎቱን እንድታቋርጡ አንዳች ባዕድ ድምጽ ከሕሊና ዉስጥ ሲያሰማችሁና ቆሞ ለመጸለይ የሰዉነት መዝለፍለፍ እንዲያጋጥማችሁ በማድረግ ስለሚያሸማቅቃችሁ እንጂ ችግሩ ከእናንተ ሆኖ አይደለም፡ ልብ በሉ! ወደ እግዚአብሔር የመቅረባችን ዋናዉ ዓላማ እንዲህ አይነቱንና መሰሎቹን ክፋቶችን ለማራገፍም ጭምር ነዉና የምትጸልዩት ጸሎት ለእናንተ ባይሰማችሁም ዲያቢሎስ በትክክል እየሰማ ነዉና ጸሎቱን ከማቋረጥ በርትታችሁ መጸለይ አለባችሁ በአሳብ ዥዉ ብላችሁ ለመሄድ የምትገደዱት ሕሊና በጠላት ቁጥጥር ስር ስለሚሆን የክፉዉን አሳብ ለማስተናገድ ተገዳችሁ ነዉና ጸሎታችሁ ትክክለኛ ጸሎት ባይመስላችሁም ለጠላት ትክክለኛ ጸሎት ነዉና ከመጸለይ አታፈግፍጉ፡ አትሸወዱ ጸሎት በማድረጋችሁ ለዉጡ ባይታያችሁም ለዉጡን የሚያዉቀዉ ስልት እየቀያየረ ፈተናዉን እንደቀጠለ ነዉ፥ መበርታታችሁን ባይታያችሁም መበርታታችሁን ያወቀዉ ጠላት አቅሙ እየተዳከመ ነዉና ሳታቋርጡ ጸልዩ። ሳያቋርጡ የመጸለይ ጥቅሙ ከሰዎች ጋር ከተቀራረብን በኋላ ከቀን ወደ ቀን ከጊዜ ወደ ጊዜ ወዳጅነታችን ተጠናክሮ የልብ ሚስጢረኛችን እንደምናደርጋቸዉ ሁሉ በጸሎት ምክንያት በየዕለቱ ከእግዚአብሔር ጋር የሚኖረን ቅርርብ ደግሞ ከዚህ በበለጠ መንገድ በየዕለቱ እየጨመረ እየጨመረ ስለሚሄድ እርሱን ብቻ የልብ ወዳጃችን የልብ ሚስጢረኛችን የችግራችን ተካፋይ እንዲሁም ለጉድለታችን መፍትሔ ሰጪ እናደርገዉና የእርሱ ፍቅር ከምንምና ከማንም በላይ ሆኖብን እንድንኖር ያደርገናል፥ ጸሎት ማድረግ እንዲሁ ቀለል አድርገን እንደምናስበዉ አይደለም በጸሎት ምክንያት ከእግዚአብሔር ጋር የሚኖረን ግንኙነት እጹብ ነዉና ጸሎትን በአግባቡ ተጠቀሙበት።